የጦርነት እውነታ የቱ ነው ያለው?

Date:

በህወሓትና በፌደራል መንግሥት መካከል የነበረው ጦርነት ቢቆምም ከጥቂት ወራት ወዲህ ደግሞ ሌላ ጦርነት ተጀምሯል፡፡ ኢትዮጵያ አሁንም እረፍት የላትም፤ ሀገር የሚያወድም ሕይወት የሚቀጥፍ አልፎም ሀገሪቱ ካላት ኢኮኖሚያዊ አቅም አንጻር ጥቂት ሳይኾን ግዙፍ የኾነውን ጦርነት እያካሄደች ትገኛለች፡፡ ልክ እንደሰሜኑ ጦርነት ሁሉ ሟቾቹም ገዳዮቹም ልጆቿ ናቸው፡፡ ይህ ጦርነት ከተጀመረ ከአራት ወራት በላይ ቢኾኑትም ይፋዊነቱ የታወጀውና አስቸኳይ ጊዜ እስከማጽደቅ የደረሰው ግን ከጥቂት ሳምንታት በፊት ነው፡፡ አሁን ላይ በዚህ ጦርነት ዙሪያ ሁለት ሦስት ትርክቶች እየተሰሙ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ትርክቶች ማጠንጠኛቸው ደግሞ እውነትን አበልዞ አንዱ በሌላው ላይ የፕሮፓጋንዳ የበላይነት መጫን ላይ መሠረት ያደረገ ነው፡፡ ከዚህ አንጻር አንዱ “ወንበዴና ወሮበላ እንደተኛሁ አረደኝ” ሲል፤ ሌላው ደግሞ “በቀየዬ መጥቶ ደፈረኝ፣ አሠረኝ፣ ገደለኝ፣ ከዚህ በላይ ምን ላድርግ?” በማለት አቤቱታውን ያቀርባል፡፡

የኾኖ ኾኖ በመንግሥትና በፋኖ መካከል ያለውን ግጭት አስመልክቶ በሁለቱም ወገን የሚጋጩ ሀሳቦች እየታዩ ነው። እንደፋኖ አገላለጽ የፋኖ ትግል ብሶት የወለደውና በአማራ ሕዝብ የሚደገፍ ከፍ ሲልም ከፋኖም በላይ ሕዝብ ራሱ የሚታገለው ትግል ነው። ከሁለት ሳምንታት በፊት ፋኖ ትላልቆቹን የአማራ ከተሞች ከተቆጣጠረ በኋላ ብዙ ሳይቆይ ለመከላከያ ሠራዊት አስረክቦ የወጣው ተሸንፎ ሳይኾን መንግሥት በከባድ መሣሪያ ከተሞቹን እንዳያወድምና ሕዝብ እንዳይጨርስ ከማሰብ የመነጨ ስልታዊ ማፈግፈግ እንደኾነም ይገልጻል። ማፈግፈጉም ስልታዊ በመኾኑ ዳግም ከተሞቹን እንደሚቆጣጠር አልፎም የመጨረሻው የትግል ግቡ ክልሉን ከመከላከያው ነጻ ማድረግና ማስወገድ እንደኾነ ገልጿል። ይህ ካልኾነ የሕዝቡ ጥያቄ መልስ እንደማያገኝ እንደሚያምንም በተደጋጋሚ ጠቁሟል፡፡

በሌላ በኩል መንግሥት በክልሉ እየተካሄደ ያለውን ሕዝባዊ ትግል “የዘራፊዎችና የወሮበሎች” እንቅስቃሴ ሲል ፈርጆታል። ክልሉንም ከሞላ ጎደል ተቆጣጥሮ እያስተዳደረው እንደሚገኝ ይገልጻል፤ በክልሉም ኾነ ከክልል ውጪ ያሉ ማናቸውንም መንግሥት ተቺ ሚዲያዎችን አስወግዶ ኢንተርኔት ዘግቶ ክልሉን ሰላማዊ እንዳደረገው ይናገራል፡፡ በሌላ ወገን ደግሞ የክልሉ በርካታ ዞኖች እና ወረዳዎች የገንዘብ ዝውውራቸው እንዲታገድ አድርጓል፡፡ ክልሉን በመዳፉ ካስገባ የገንዘብ ዝውውርን ማገድ ምን አመጣው? የፌደራል መንግሥቱ በዚህ ብቻ ሳይገታ በርካታ በክልሉም ኾነ ከክልሉ ውጪ ያሉ አማሮች በገፍ እያሰረ ይገኛል፡፡ ይህ በራሱ ትግሉ የጥቂት “ወሮበሎች” ከኾነ ስለምን ያስፈልጋል የሚለውን ጥያቄ ሊመልስ የሚችለው መንግሥትና መንግሥት ብቻ ነው፡፡ ከሰሞኑን ደግሞ መንግሥት በተቆጣጠራቸው የተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በርካታ ሕዝባዊ ውይይቶች እየተካሄዱ ይገኛሉ። ይህ ሕዝባዊ ውይይት ግን በክልሉ ጠብታ ሰላም ማስገኘት አልቻለም፡፡ መንግሥት እንዳለው በክልሉ ያለው ግጭት የጥቂት “ዘራፊና ወሮበሎች” ቢኾን ኖሮ ይህን ያህል ጊዜ ጦርነት ላይ ባልከረመ ነበር፡፡ ጀትና ድሮንም ባልተጠቀመ ነበር፤ በገፍ የሚቆጠር መከላከያ ሠራዊትም ወደ ክልሉ ባላስገባ ነበር፡፡ በርካታ የዓለም ሚዲያዎችም ርዕሰ ጉዳያቸው ባላደረጉት ነበር፡፡ እንደማይካመር ያሉ የአሜሪካ ወኪሎች ጉዳዩ አሳስቧቸው ከአውሮፓና መሰል አሀጉራትና ሀገራት ጋር ባልመከሩበትም ነበር፡፡

ስለዚህ ቀሪው የኢትዮጵያ ሕዝብም እየተካሄደ ስላለው ጦርነት እውነታውን ማወቅ ይኖርበታል፡፡ በትክክል ክልሉ ላይ ያለው ሁኔታ ምንድነው የሚለው በግልጽ መነገር ይገባዋል፡፡ ከዚህ በፊት እንደታየው በጦርነትና ሕዝብን በማፈን ፖለቲካዊ ድል ማምጣትም ኾነ በዘላቂነት ማሸነፍ አይቻልም፡፡ በመኾኑም በክልሉ ያለው ሁኔታ ለመፍታት በቅድሚያ ከክልሉ ወታደራዊው አገዛዝ መውጣት ይኖርበታል፡፡ ከዚያ ደግሞ ለሰላማዊ ውይይት መቀመጥ ይገባል፡፡ ከዚያ ውጭ እንደትግራዩ ጦርነት በርብርቦሽ እና በኃይል ችግሩን ለመፍታት ከተሔደ ከማባባስ ውጪ መልስ አይኖረውም፡፡ ሀገሪቱንም ወደ ተራዘመ አለመረጋጋትና ጦርነት ውስጥ ሊከታት እንደሚችል ግልጽና የታመነ ከዚህ ቀደም የነበረ ልምዳችን የመሰከረው ሀቅ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ጦርነት የገጠመውን ኃይል “ዘራፊ፣ ጽንፈኛ፣ መንጋ፣ ወሮበላ… ወዘተ” እያለ ማንኳሰሱን ትቶ ለንግግር በሩን ክፍት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ እንደሚታየው ከኾነ ነፍጥ አንግቦ እየተዋጋ ያለው ፋኖ ቢኾንም ጥያቄው የሕዝብ ጥያቄ ነው፡፡ ስለዚህ መንግሥት ማድበስበስና ማለባበሱን መግታት ይጠበቅበታል፡፡

ይህ ፋኖ የተሰኘው ታጣቂ ኃይል ምን ያህል አቅም እንዳለው ደግሞ መንግሥት ሳይረዳው አይቀርም፤ ምክንያቱም በዚህ ጦርነት ከወራት በላይ ከርሞ ከውድመት ውጪ ጠብ ያለ ነገር አልታየም፡፡ “ወሮበላ” የተሰኘው ኃይል በተፈለገው ልክ ሲደመሰስ አልታየም፤ ወይም አልተሰማም፡፡ ከዚህ አንጻር መንግሥት ከቀድሞው ስህተት መማር ይኖርበታል፡፡ በትግራይ ያ ሁሉ ደም አፋሳሽ ውጊያ ከተካሄደ በኋላ ፍጻሜው ንግግር ነው የኾነው፡፡ አሁነኛውን ጦርነትም ከብዙ ውድመት በኋላ ወደሰላም ለመምጣት ከመጣር ይልቅ ሀብት ንብረት ሳይወድም በርካታ ሕይወት ሳይቀጠፍ ወደ ውይይት መምጣት ይገባል፡፡ ያለበለዚያ ግን መንግሥት መሥራት የሚገባውን ሥራ ሳይሠራ ያለስጋት ሀገር ለመምራት መሞከር አሁን ካለው ሁኔታ አንጻር “በቡሃ ላይ ቆረቆር” እንደማለት ነው፡፡ በኃይልና በማደናገር ሊያልፈው የሻው የፖለቲካ ጨዋታ የፍጻሜ ፍልሚያን እንዳያስከትል ሀገርንም ወደባሰ አረንቋ እንዳይከት ኃላፊነት ያለበት መንግሥት ግጭቱን በሰላማዊ መንገድ እልባት ሊሰጠው ይገባል፡፡ ምድር ላይ ያለውን ሀቅ በመካድና ጦርነቱን አያዎ በማድረግ የሚፈታ ችግር አይኖርም፡፡ ሀገሪቱ እንኳን ከዚህ የባሰ ሌላ ቀውስ አስተናግዳ ይቅርና እነዲሁም ከብዷታል፡፡ ሁኔታዎች በዚሁ የሚቀጥሉ ከኾነ የሚቀጥሉት ወራት ከፍ ሲልም ዓመታት ለኢትዮጵያውያን የሰቆቃ ዘመናት መኾናቸው አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ሦስትና አራት ወር ውስጥ እንኳን አንድ ኩንታል ጤፍ ከሰባትና ስምንት ሺህ ብር ተነስቶ አሥራ አራትና አሥራ አምስት ሺህ ብር ደርሷል፡፡ በቅርቡ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የቴክኒክ ኮሚቴ አስተባባሪ ዶክተር አደፍርስ ወርቁ እንደተናገሩት ደግሞ አሁን ባለው ሁኔታ ከኢትዮጵያ አጠቃላይ የቆዳ ስፋት ግማሽ ያህሉ መሬት ወይም  54 ሚሊየን ሄክታር የሚኾነው መሬት ለምነቱ የተጎዳ ነው፡፡ ከዚህ ከግማሽ ያህሉ ደግሞ ከፊሉ በሀገሪቱ በሁሉም አቅጣጫ ባለው ግጭት ሳቢያና እንዲሁም በማዳበሪያ እጥረት በምርት ሳይሸፈን ቀርቷል፤ ወይም ጦም አድሯል፡፡ በተለይ ደግሞ የሀገሪቱን አንድሦስተኛውን የሚሸፍነው የአማራ ክልል ለምነቱን ካጣውና ጦም ካደሩ መሬቶች ውስጥ ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ በጥቅሉ ይህ ሁሉ ችግር ባለበት ሁኔታ ይህን መሰል ጦርነት ማድረግ ኪሣራው የሀገር መኾኑ እሙን ነው፡፡ ከዚህ አንጻር በዋናነት መንግሥት ወደ ቀልቡ መመለስ ይኖርበታል፡፡ የሚያስተዳድራት ሀገር ከፈረሰች መንግሥት ኾኖ የሚቀጥልበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ከወዲሁ በአማራ ክልል ብቻ ሳይኾን በሁሉም አቅጣጫ የሚያደርጋቸውን ውጊያዎች ማቆም ይጠበቅበታል፡፡ በአፋጣኝ ወደፖለቲካዊ መፍትሔ በመግባት ችግሮችን ማርገብም ይገባል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

እንኳን ለብርሃነ ጥምቀቱ አደረሳችሁ፤ አደረሰን

ሰማያት ተከፈቱ ፣ ምስጢርም ተገለጠ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘመዷ ቅድስት...

አባቴ ለእኔ አባት ብቻ አልነበረም፤ ለእናቴ ታማኝ ባል፣ ለሁላችንም ደግሞ የደስታ ምንጭ ነበር

"አባዬ… ዛሬ ላለሁበት ማንነት መሰረት የሆንከኝ አንተ ነህ!" ​የአርቲስት...

የአንበሶቹ ትንሳኤ፦ የዳካር እንባ እና የቴራንጋ ድል

​በዳካር ሰማይ ስር ዛሬ ጨረቃ አልወጣችም፤ ይልቁንም በሚሊዮን የሚቆጠሩ...

የጥምቀት በዓል በመላ ሀገሪቱ በድምቀት እየተከበረ ነው

የጥምቀት በዓል በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን እና በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት...