ይኩኖአምላክ ዝም ብሎ ሹም አልነበረም

Date:

ይኩኖአምላክ መዝገቡን አለማመስገን በፍርድ ቀን ያስፈርድብኛል። የማውቀው ሳይሾም በፊት ነበር፣ ሲሾም ያልተቀየረ ትሁት ኾኖ ቀጠለ። ደግሞ ከመሾሙ በፊት “የተሾመ ለምን ይሄንን አይሰራም?” ሲል ቁጭቱን ሰምቻለሁ። እንደተሾመ በተቆጨበት ላይ ሲዘምት ያየሁ ምስክር ነኝ።

ለመሆኑ ዝም ብሎ ሹም አለ? ትሉኝ ይሆናል። በደንብ ነዋ እላችኋለሁ። ልጆቹን ለማሳደግ የሚሾም። የተሾመበትን ደብዳቤ ያኽል ሲሻር ትርጉም የሌለው። ዳሩ ምን ያደርጋል! ባህል ነው እና ሲሄድ ወይም ሲሞት እንደምንለው የሄደ ሰው ላደንቅ መጣሁ።

ከበደ ሚካኤል፣ ሲልቪያ ፓንክረስት፣ ተክለፃድቅ መኩሪያ እያልን ወመዘክርን የመሩ ባለውለታዎች ስንቆጥር ይኩኖአምላክ መዝገቡ የሚለው ስም በክብር የሚቆጠር፣ ሊዘለል የማይችል እንደሆነ አልጠራጠርም።

ይኮኖአምላክ ወጣት መሪ ነው። ብዙዎች ዘንድ ባልተለመደ መልኩ ወደ ሕይወቱ የመጣው የሹመት ኑሮ፤ ብርቅ ሆኖ አላሳከረውም። ለንባብ ተሾመ፣ ስለ ንባብ ኖረ። ሲመስለኝ ደግሞ ፓርቲና ስብሰባ ይሸሻል።

በግሌ ከየትኛውም የኢትዮጵያ አካባቢ መጻሕፍት ድጋፍ ፍለጋ “እስቲ የሰውዬውን ስልክ” ለሚሉኝ ደረቴን ነፍቼ አቀብላለሁ። “አላነሳ አለ” ካሉ “መልእክት ላኩለት” እላለሁ። ተልኮ ሜዳ የቀረ መልእክት የለም። ይኩኖ ይደውላል-ውጤቱ ደግሞ የኾነ አካባቢ መጻሕፍትን በድጋፍ ማድረስ ይሆናል።

ይኩኖአምላክ አንድ መጽሐፍ ላነበበ ታራሚ፤ ለምን ከእስር ቀኑ አንድ ቀን አይቀነስም ሲል ንቅናቄ የጀመረ ሰው ነው፤ ይኩኖአምላክ ነው መጽሐፍ ለማድረስ ሄዶ ጨንቻ ቀርቀሃ ላይ የሚያድረው፤ በእርግጥም ሰውዬውን አለማድነቅ፣ ማን እንደለቀቀ አለመናገር በፈጣሪ ስም ያስጠይቃል።

ይሄ በግሉ የተደረገለት ሰው ምስክርነት አይደለም። ስለ ሀገር ለተደረገ አበርክቶ የቀረበ እማኝነት ነው። ጎንደር መጻሕፍት ጭነን ሄደናል፣ ቦንጋም እንዲሁ፣ መቀሌ ገብተናል። ሀረርም በተመሳሳይ ደብረ ታቦር ዘልቀናል። ድሬድዋም፤ የት ነው ያልተደረሰው ጅግጅጋ ወይስ ጅንካ? ታርጫ ወይስ ሚዛን አማን፤ ከማርቆስ እስከ ሰመራ ከባህር ዳር እስከ ሮቤ ብቻ በመላ ኢትዮጵያ ተቋሙ ደርሷል። በዚህ ይኩኖአምላክም ሆነ መላው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመጻሕፍት እና ቤተ መዛግብት ኤጀንሲ ሰራተኞች ሊመሰገኑ ይገባል።

ዋና ከተማ ብቻ የሚፏልል አይደለም፤ ያ ቢሆን ጋሞ ኤዞ ቤተመጻሕፍት ባልደረሰ፤ እንፍራንዝ ባልገባ፣ ስልጤ ገርቢበር ባልሄደ፣ ይርጋጨፌ ታንብብ ብሎ ባልወሰነ፣

ደግሞ ይኩኖአምላክ ተጀምሮ ቆመ ሲሉት የማይወድ ሰው ነው። ለምሳሌ የግዕዝ ጉባዔ በባህል ሚኒስቴር መሪነት እንደ ሀገር ጀመርን ውሎ አድሮ አመላችን ተነሳበትና ሰው ሲቀየር ይቁም ተባለ። ይኩኖአምላክ ምን ሲደረግ ብሎ ቀጠለው። እነኛ ያስቆሙት ዛሬ በስልጣን ቦታቸው የሉም፣ ይኩኖአምላክም እንዲሁ፤ ታሪካቸው ግን “ማስቆም” እና “ማስቀጠል” ተብሎ እየወገኑ ቆሞ ይኖራል።

እርግጥ ነው ይኩኖአምላክ መዝገቡ የቤተክህነትም ሰው ነው፤ የቤተመንግሥት ሰው ሲኾን ግዕዝ ጉባኤ ብሎ ወደ ጉዳዩ የገባ እንዳይመስለን፤ እንደ ሀገር የመንዙማ ኩነትን የደገሰ ልዩ ሰው ነው። ደግሞ እንደ ብራናው ለኪታቡ ልቡ የደነገጠ፤ ለዚህ ዘቢሞላ ምስክሬ ናት።

ይኩኖአምላክ በትብብር ስራ ያምናል። የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ከብሔራዊ ቤተመዛግብት እና ቤተ መጻሕፍት ጋር በመተባበር የሚል ዜና ብርቅ አይደለም። ይኩኖአምላክ በማስቀጠል ያምናል፤ የተቋሙን ህንፃ ግንባታ ጨምሮ ከእሱ ቀደም የተጀመሩትን ሁሉ አስፍቶ አስቀጥሏቸዋል።
ደግሞም በመጀመር ያምናል “የወር ወንበር” በሚል በየወሩ በቤተ መጻሕፍቱ የሚካሄደው መደበኛ ጉባኤ በእሱ የጀመረ ነው። ወመዘክር 24 ሰዓት እንዲሰራ ያስጀመረ ባለ አሻራ። አንብቡ ሲል አንብቦ፤ ስለ ንባብ ሲያወራ ተሰጥቶ ነው።

ይኩኖአምላክ መዝገቡ በወመዘክር ታሪክ መጣ ሄደ የሚባል ሰው አይደለም። ይሄ ሰው ሰኔ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰርፀ ፍሬስብሐት ተተክቷል። እንዲህ ያለ ህያው ታሪክ ለተካው ሹመኛም እመኝለታለሁ።

(ተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም – ለድሬ ቲዩብ)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ሃይንከን በአልኮል መጠኑ ጠንከር ያለ ቢራ ለኢትዮጵያ ገበያ አስተዋወቀ

ሃይንከን ኢትዮጵያ በእለም አቀፍ ደረጃ ዝነኛ የሆነውን ዴሰፔራዶስ (Desperados)...

ኢራን ድርድር ውስጥ ከገባች “እጇ ከቃታው ላይ” አይነሳም

ኢራን ከአሜሪካ ጋር ድርድር የምታደርግ ከሆነ ንግግር ውስጥ የምትገባው...

ለቅርስ ጥበቃና ምርምር የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም

የቅርስ ጥበቃና የምርምር ዘርፍ ውስጥ የዲጂታል ቴክኖሎጂ አጠቃቀም አስፈላጊ...