ከዛሬ ጀምሮ የዳሽን ባንክ ደንበኞች በተመረጡ የነዳጅ ማደያዎች ነዳጅ ሲቀዱ ክፍያቸውን በዳሽን ሱፐር አፕ በሶስት ክሊክ ብቻ መፈጸም የሚችሉበት አገልግሎት አቅርቧል፡፡ይህም ደንበኞች አገልግሎቱን በቅፅበት እንዲያገኙ የሚያስችላቸው ነው፡፡በቅርቡም ዳሸን ባንክ ይህንን አገልግሎት በሁሉም ማደያዎች የሚጀምር ይሆናል፡፡
ነዳጅ የሚቀዱ የዳሽን ባንክ ደንበኞች የዳሽን ስፐርአፕ መተግበሪያ ውስጥ በመግባት በሚኒ አፕ መተግበሪያ ውስጥ የሚገኘውን የነዳጅ ክፍያ (Fuel Payment) አማራጭ በመምረጥ የሚላክላቸውን የነዳጅ ክፍያ ኮድ በማስገባት ከፍያቸውን መፈፀም፣ አልያም በአማራጭነት የቀረበውን የኪው አር ኮድ ስካን በማድረግ በቀላሉ ክፍያቸውን ወዲያውኑ መፈፀም ይችላሉ፡፡
በዳሽን ሱፐርአፕ መተግበሪያ የቀረበው አገልግሎት ለአሽከርካሪዎች፤ ለነዳጅ ማደያዎችና ለነዳጅ ተቆጣጣሪ የመንግስት አካላት ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው ሲሆን፣ በተጨማሪም ከዚህ ቀደም የተጀመረውን የነዳጅ ማደያዎች የገንዘብ አከፋፈል ስርዓት ወደ አስተማማኝና ዘመናዊ የዲጂታል ክፍያ ስርዓት የሚቀይርና የፋይናንስ አካታችነትን ይበልጥ የሚያረጋግጥ ይሆናል፡፡
ዳሽን ባንክ ከነዳጅ ማደያ ባለቤቶች ጋር በተለያዩ ዘርፎች በጋራ የሚሰራም ሲሆን ለዚህም ባንኩ ሰፊ ዝግጅት እያደረገ ይገኛል፡፡
በኢትዮጵያ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ አዳዲስ የዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎቶችን በማስተዋወቅ ግንባር ቀደም የሆነው ዳሽን ባንክ፣ በቀጣይም ለደንበኞቹን አዳዲስ አገልግሎቶችን ያቀርባል፡፡
የነዳጅ ግብይቱን ለማዘመን የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ያበለጸገዉን መተግበሪያ ከዳሽን ሱፐር አፕ ጋር በማጣጣም የነዳጅ ክፍያ መፈፅም እንዲያስችል ተደርጎ ተዘጋጅቷል።
