ጥር 5 ቀን 2018 ዓ.ም በስካይ ላይት ሆቴል ከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች እንዲሁም የዳቺ የምግብ ኢንዱስትሪ አክሲዮን ኩባንያ ኃላፊዎች በተገኙበት ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል ።
ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የታሸጉ የባቄላ እናውቃለን ቦሎቄ ምርቶችን በአገር ውስጥ ማምረት ጀምራለች። ይህም ከውጭ ገበያዎች ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርቶችን በሀገር ውስጥ በመተካት (import substitution)) የግብርና ምርቶችን በፋብሪካ ሒደት ውስጥ በማሳለፍ (Agro-Processing) እና የውጭ ገበያ ላይ ባተኮረ የኢንዱስትሪ ልማት (export led manufacturing) ዘርፎች ሀገራችን ትልቅ እመርታ ማሳየቷን የሚያበስር ነው።
የምግብ ማቀነባበርያ አክሲዮን ኩባንያ የሆነው ዳቺ የምግብ ኢንዱስትሪ ከኢትዮጵያ ገበሬዎች የተገኘ ባቄላ፣ አተር እና ቦሎቄ በመጠቀም ስድስት ዓይነት የታሽጉ ምግቦችን ሙሉ በሙሉ በሀገር ውስጥ በማምረት መጀመሩን በዛሬው ዕለት በይፋ አስታውቋል።
እነዚህ የታሸጉ የባቄላ እና ቦሎቄ ምርቶች ቀይ ቦሎቄን፣ ነጭ ቦሎቄን፣ ጥቁር ቦሎቄን፡ ፉልን፡ አተርን እና ጣፋጭ በቆሎን (Sweet Corn) ያካትታሉ።
ምርቶቹ በ400 ግራም መጠን የታሸጉ ሲሆኑ በጥቂት ወራት ውስጥ 3 ኪሎ ግራም መጠን ያላቸው እሽጎችም ለገበያ እንደሚቀርቡ ይጠበቃል። እነዚህ ምርቶች ተመጣጣኝ ዋጋ ያላቸው ናቸው።
እነዚህ ምርቶች ለሀገር ውስጥ ገበያ ብቻ ሳይሆን በቅርቡ ዱባይን ጨምሮ ወደ ዓለም አቀፍ ገበያዎችም የሚላኩ ይሆናል።
ይህ መነሻ ኢትዮጵያን ከጥሬ ዕቃዎች ላኪነት ወደ ከፍተኛ እሴት ያላቸው ዓለም አቀፍ የጥራትና የደህንነት መመዘኛዎችን የሚያሟሉ የተጠናቀቁ የምግብ ምርቶች ላኪነት የሚያሽጋግር ሒደት ነው።
“አዳዲሶቹ ምርቶች ኢትዮጵያ በዓለም የምግብ አቅርቦት ሰንሰለት ውስጥ ያላት ሚና እየተቀየረ መሔዱን አብሳሪ ናቸው” ሲሉ ቢኒያም ዮሐንስ፡ የዳቺ ዋና የንግድ ኃላፊ (CCO) ተናግረዋል። “ለብዙ ዓመታት ጥሬ ባቄላ እንልክ ነበር፣ የታሸጉ ምርቶችን ግን እንገዛ ነበር።
በዚህ ኢንቨስትመንት ገበሬዎች, ሠራተኞችና አምራቾች ከእርሻ እስከ ዓለም አቀፍ መደብሮች ድረስ በሙሉ የእሴት ሰንሰለቱ አካል ሆነዋል።”
የሀገር ውስጥ አቅርቦት ሰንሰለትን ማጠናከር
የታሸጉ ምርቶቹን ለማምረት የምንጠቀማቸው ጥራጥሬዎች በሙሉ በተለያዩ ቦታዎች ከሚገኙ ኢትዮጵያውያን ገበሬዎች ጋር ባለን የአቅርቦት ስምምነቶች የሚመጡ ናቸው። በዚህም ገበሬዎች ለምርታቸው ጥሩ ዋጋ እና ቀጣይነት ያለው ገበያ ያገኛሉ።
የማቀነባበሪያ ፋብሪካው ዘመናዊ የማሸጊያ ቴክኖሎጂ፣ የጥራት ቁጥጥር ስርዓቶች እና ከዓለም አቀፍ ገበያ መስፈርቶች ጋር የተጣጣሙ የምግብ ደህንነት መመዘኛዎችን ይጠቀማል። ይህም “Made in Ethiopia” በሚል መለያ የታሸጉ ምግቦች በዓለም አቀፍ ገበያ እንዲወዳደሩ ያስችላል።
ምርቶቹ በእገር ውስጥ ገበያም ለሽያጭ ቀርበዋል።
ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተፅዕኖ
ይህ የምርት ሒደት የሚከተሉት ጥቅሞች አሉት፦
ከውጭ ሀገር የሚገቡ የታሽጉ የምግብ ምርቶች ላይ ያለንን ጥገኝነት መቀነስ
የውጭ ምንዛሬ ቁጠባ እና ከውጭ ንግድ የሚገኝ የውጭ ምንዛሬ
የሥራ ፈጠራ
ለኢትዮጵያ ገበሬዎች አስተማማኝ ገበያ
በምግብ ኢንዱስትሪ ውስጥ የክህሎት ማስተላለፊያና ቴክኖሎጂ ሽግግር
ኩባንያው የገበያ ፍላጎት እየጨመረ ሲሔድ የምርት አቅምን ለማሳደግና ከገበሬዎች የሚሰበሰብ ምርትን ለማስፋፋት ዕቅድ አለው።
ዳቺ የምግብ ኢንዱስትሪ አራት ፋብሪካዎችን የሚያስተዳድር የአክሲዮን ኩባንያ ነው። እነሱም የታሽገ ምግብ ፋብሪካ፣ የቲማቲም ፔስት ፋብሪካ፣ የፍራፍሬ ኮርዲያል፣ ጃምና ማዮኔዝ ፋብሪካ እና የኮንዲመንት ፋብሪካ ናቸው። የኮንዲመንት ፋብሪካው ኬችአፕ፣ ሶይ ሶስ፣ መስታርድ፣ የምግብ ቀለም እና ቫኒላን ጨምሮ 26 ዓይነት ምርቶችን ያመርታል።
ኩባንያው ከ36 በላይ ምርቶችን የሚያቀርብ ሲሆን በቅርብ ጊዜ የምርቶቹ ቁጥር ከ100 በላይእንደሚደርስ ይጠበቃል።
