
በመፅሐፍህ በተለይ በዴርቶጋዳ ላይ በርካታ የመቼት መፋለስና የሙያዊ ትንታኔ አገላለፅ ጉድለት ይስተዋላል፤ የሂዩስተን ነዋሪ የሆኑ አንድ ፀሐፊ ስለ አሜሪካ በተለይ ተመድ አካባቢ ስላለው ስፍራ የገለፅከው ፈፅሞ ከእውነት የራቀ መሆኑን ተችተው የፃፉትን አንብቤያለሁ፡፡ ስለውትድርና ሙያ የፃፍከውም እንዲሁ፡፡ ከተሰጠህ
ትችት ጥቂቱን ላስታውስ፡- “…ምግብ አብሳይ ሴቶችን አስገድደው የሚደፍሩ የሰንጥቅ ብርጌድ አባላት የሆኑ ወታደሮች ሜሮዳን አስገድደው ለመድፈር ሲሉ ሁለቱ ዶክተር ወታደሮች ይደርሱና ያስጥላሉ፡፡ እንዲያውም ዶክተር ሚራዥ የድምፅ ማፈኛ የተገጠመለት ሽጉጡን በወታደሮቹ ላይ ይመዝዛል፡፡ ሽጉጡን ደግሞ በውጊያ ውስጥ ከሞተ ጄኔራል ላይ መውሰዱን ይነግረናል፡፡ አንድ ጄኔራል በብርጌድ አቋም ከተደራጀ ጦር ውስጥ ምን ይሠራል?… ያ የጄኔራል መኮንን ቦታም አይደለም፡፡ “ይሁን” ቢባል እንኳን አንድ ተራ (ብሔራዊ ወታደር) ከአንድ ጄኔራል ሬሳ ላይ ሽጉጥ የሚፈታበትና መሣሪያውን ደብቆ ይዞ በሠራዊቱ ውስጥ የሚኖርበት ዕድል ሊፈጠር አይችልም፡፡ በዚያን ወቅት፡-
“…ወደ ሱዳን እየተጓዙ ሳለ የደርግ ሄሊኮፕተር በአየር ላይ ይከታተላቸዋል፡፡ እናም ይደርስባቸዋል፡፡ ማምለጫ ባጡበት ሁኔታ ውስጥ እንደገቡም ከፍተኛ የፍንዳታ ድምፅ ሰሙ፡፡ ሄሊኮፕተሩ በጠላት አየር መቃወሚያ ተመትቶ ሲነድ ታያቸው፡፡ አብራሪውም በዣንጥላ (ፓራሹት) ሲወርድ አዩት፡፡ የጦር ሄሊኮፕተር አብራሪ ሄሊኮፕተሩ በአየር ላይ ሲመታበት በፓራሹት እንደሚወርድ ለመጀመሪያ ጊዜ የነገረኝ ይኼ ደራሲ ነው፡፡”
እንደዚህ ዓይነት ስህተት እንዳለበት ተጠቅሷል፤ ስለማታውቀው ቦታና ጉዳይ ስትፅፍ አስቀድመህ መረጃ ማሰባሰብ አይጠበቅህም?
መቶ አለቃ ጠና አደመ (ከሃዋሳ)
ይስማዕከ፡- በዚህ ትችት ላይ ራሱ ግልፅ ስህተት ፈጦ ይታያል፡፡ ሽጉጡን ከሞተ ጄኔራል ላይ የወሰደው ሚራዥ አይደለም፡፡ ሃያሲ ነኝ ባዩ ሰውዬ ለትችት ከመፍጠናቸው በፊት በደንብ ቢያነቡት መልካም ነበር፡፡ ሽጉጡን ደብቆ ይዞት የነበረው ዣንጊዳ እንጂ ሚራዥ አልነበረም፡፡ በዚህች አንዲት አንቀጽ ውስጥ እንኳ ተቺዬ አለመሳሳት አልቻሉም፡፡ ሌላው ጄኔራሎች በመደበኛ ጦርነት ላይ የመታኮስ ኃላፊነት የለባቸውም፡፡ በመደበኛ አውደ ውጊያ (conventional war) ላይ እንደተራ ወታደር በእርግጥ አይፋለሙም፡፡ የአእምሮ ወይም የሂሳብ ጨዎታዎችን የመቀመር ግዴታ ግን አለባቸው፡፡ በድንገተኛ ሁኔታዎች ውስጥ ግን ራሳቸውን አጣብቂኝ ውስጥ ሊያገኙት ይችላሉ፡፡
እንኳንስ አንድ ጄኔራል መንግስቱ ኃ/ማርያም ራሳቸው ግንባር ገብተው የተፋለሙበት ወቅት እንደነበር መመስከራቸው የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ከዚህም በላይ ዣንጊዳ በሰራዊቱ ውስጥ የነበረው ድርሻ አልተገለጸም፡፡ የታሪኩ ፍሰት ወይም ሀዲድ የተዘረጋው ሚራዥ ላይ ስለሆነ የሌሎች ንዑሳን ገፀ ባህርያት የየዕለት ሁኔታ በሰፊው አይተነተንም፡፡ በውስጠ ታዋቂነት ግን ይታወቃል፡፡ ሌላው ከሄሊኮፕተር በፓራሹት መውረድ አይቻልም የሚለው ነው፡፡ በመሠረቱ የዝላዮች ልምምድ ሳይቀር በሄሊኮፕተር ላይ ይደረጋል፡፡ በተገቢ ርቀት እየበረረ ከሆነ በበር በኩል በመዝለል ዣንጥላውን መዘርጋት ይቻላል፡፡ እንኳንስ በጭንቅ ጊዜ! ይህንንም ማንም የሚያውቀው ጉዳይ ነው፡፡ የሂውስተኑ ነዋሪ ተመድን ማየታቸው አጠራጥሮኛል፡፡ በዴርቶጋዳ ለተገለፀው ሁሉ በርካታ ጥናቶች አድርጌያለሁ፡፡ የቪዲዮና ፎቶግራፍ ካርታዎችን እንዲሁም የፅሁፍ መረጃዎችን በመያዝ ነው የሠራሁት፡፡ ለልብወለድ ቀርቶ ለታሪክ እንኳ ሊበቃ የሚችል ጥናት አድርጌ ነው የሠራሁት፡፡ ርቀቶችን ሳይቀር በተለያዩ ዘዴዎች በመስፈር ብዙ ተጨንቄያለሁ፡፡ ስንዝር የምታህል ርቀት እንኳ በቼልተኝነት አልተውኋትም፡፡ ለዛም ነው ዴርቶጋዳ እውነተኛ ታሪክ እንጂ ልብወለድ አይደለም ብለው ብዙዎች የወጠሩኝ፡፡ ለቁጥሮች፣ ለቦታዎችና ለጥቃቅን ኩነቶች ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠ ይህ ያረጋግጣል፡፡ “በርካታ የመቼት መፋለስ” ብሎ እነዚህን ከራስ የእውቀትና የግንዛቤ ማነስ የመነጩ ስህተቶችን ወደ ደራሲው ማምጣት ተገቢ አይደለም፡፡ “ከመዋጥ ማላመጥ” ይላል ያገሬ ሰው፡፡ ለትችት ከመፍጠን ንባብ ቢቀድም ጥሩ ነበር፡፡ አንድ ጊዜ ዋሽንግተን ዲሲ እንደሚኖር አስመስሎ ስራዬን አብጠልጥሎ ጋዜጣ ላይ የፃፈ ግለሰብ አዲስ አበባ ውስጥ አግኝቶኝ ብዙ ምላሾችን ከሰጠሁት በኋላ “እኔ ነኝ በብዕር ስም ዋሽንግተን
እንደሚኖር አስመስዬ የፃፉኩብህ፤ አሁን ጥያቄዎቼን ስትመልስልኝ ይህን እውነት እንዳጋልጥ ተገድጃለሁ” ሲል ይቅርታ ጠይቆኛል፡፡ ይህ ሰው ከአዲስ አበባ ውጪ ወጥቶ አያውቅም፡፡ እንኳን ዋሽንግተን ዲሲ ኢትዮጵያ ውስጥ ደብረዘይት ድረስ እንኳ ተጉዞ አያውቅም፡፡ በስነ ፅሁፍ ላይ ይህን ያህል ደባ ለመፈፀም ህሊናው እንዴት እንደፈቀደለት፣ ለምን ጥቅም ሲልስ ይህን እንዳደረገው ሊገባኝ አልቻለም፡፡ ብዕር የሚጨብጡ እጆች ከስሜትና ከሌላ ጥቅም ሲፀዱ ሙያዊ ሂሶች ስነ ፅሁፋችንን ያሳድጉታል፡፡ የኢትዮጵያን ስነ ፅሁፍ ያቆረቆዘውና እያስረጀ የሚጥለው የሙያዊ ሂስ አለመዳበር ነው፡፡ በተራ ስሜትና በግል ጥላቻ ተነሳስተው ቆንጨራ ይዘው በሚወጡ የስድብ መሀንዲሶችና ለሥነ-ፅሁፍ ተቆርቁረው የአንባቢውን ስነ ፅሁፋዊ እይታ በሚያሰፉ ሀያስያን መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡
የልጅነት አስተዳደግህ ምን ይመስላል? የአብነት ትምህርት ቤት ቆይታህን ጨምረህ ብታብራረልኝ…
መስፍን አዲሱ (ከባሕር ዳር)
ይስማዕከ፡- ያደግኩት በአብነት ትምህርት ቤት ውስጥ ነው፡፡ ገና አራት አመት ሳይሞላኝ ጀምሬ ከቤተሰቦቼ ተነጥዬ እዛው ነው ያደግኩት፡፡ እግዚአብሔር አእምሮዬን ከፍቶልኝ በልጅነቴ ብዙዎች ረጅም አመታት የሚፈጅባቸውን ትምህርት በአጭር ጊዜ አቀላጥፌያለሁ፡፡ ከሁሉም በላይ ቅኔ መማሬ በህይወቴ ትልቁ ምዕራፍ ነው፡፡ አሁን ላለሁበት ሁኔታ ያበቃኝ እሱ ነው፡፡ ወደ ዘመናዊው የአስኳላ ትምህርት ቤት የገባሁት ግን ዘግይቼ ነው፡፡ አስኳላ ትምህርቱንም በተርም (በደብል) እያለፍኩ ዩኒቨርስቲ የገባሁት በአጭር ጊዜ ውስጥ ነው፡፡
በዩኒቨርሲቲ የሕክምና ትምህርት ትከታተል እንደነበረ ይታወቃል፤ ትምህርቱን ከምን አደረስከው? ወደፊት በሕክምና ሙያ የመቀጠል ሃሳብ አለህ ወይስ በድርሰት ብቻ?
ክፍሌ ወጂ (ከመርካቶ)
ይስማዕከ፡- ይህ አመት የዩኒቨርስቲ ትምህርቴን አጠናቅቄ የምመረቅበት አመት ነው፡፡ ከወራት በኋላ እመረቃለሁ፡፡ በጤናው ዘርፍ ልስራ አልስራ አላወቅኩም፡፡ ነፍሴ ሌጣ ወረቀትና ብዕር ያምራታል፡፡ ተቀጣሪ ከሆንኩ ደግሞ ጊዜ አግኝቼ የምወደውን የድርሰት ሥራዬን ለመሥራት እንከን ይሆንብኛል፡፡ በነገራችን ላይ ጤናን የተማርኩት ለመቀጠር
ሳይሆን ለእውቀት ነው፡፡ ስለዚህ በድርሰቱ ነው መቀጠል የምፈልግ፡፡
የድርሰት ስራዎችህ ከሚታዩና ሊሆን ከሚችሉ ጉዳዮች ይልቅ በምናብ ብቻ በሚብሰለሰሉ ጉዳዮች ዙሪያ ያተኩራሉ፡፡ ራስህን የፋንታዚ ድርሰት ፀሐፊ ነኝ ትላለህ ወይስ የሳይንስ ፊክሽን (ሳይንሳዊ ልቦለድ) አድርገህ ትወስዳለህ?
ሀብታሟ ታሪኩ (ከልደታ)
ይስማዕከ፡- ፋንታዚ ድርሰቶች እኮ ለድርጊቶች ምክንያት አያቀርቡም፡፡ በኔ ሥራዎች ውስጥ ግን ሊሆን የማይችል ነገር አላየሁም፡፡ ብዙዎቹ ሀሳቦቼ ከፃፍኳቸው በኋላ በአለም ዙሪያ ተሰርተዋል፡፡ ከዴር 33 እስከ ቀያዮቹ ወፎች መጽሀፎቼ ከወጡ በኋላ ተሰርተው በተለያዩ ሚዲያዎች እንደ አስገራሚ ዜና ሆነው ቀርበዋል፡፡ ሊሆን የማይችል ነገር ከፃፍኩት ውስጥ የለም፡፡ ለሁኔታዎች ሁሉ አመክንዮ የሚያቀርብ…(cause-effect) ያለው ልቦለድ ፋንታዚ ሲባል ስሞቼ አላውቅም፡፡ ለምናባዊ ፈጠራዎችም ምክንያት ከቀረበላቸው ፋንታዚ አይደሉም፡፡ ሳይንሳዊ ትንታኔ የቀረበባቸው ምናባዊ ፈጠራዎች እንዲህ ሲባሉ ስምቼም አላውቅም፡፡ የሀያስያን ሙያም እንደዚህ አይነቶችን ሁኔታዎች በማብራራት አንባቢውን አንድ ርምጃ ወደፊት መውሰድ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ቅድም እንደተናገርኩት መጽሀፎቼ እንደእውነተኛ ታሪክ ተቆጥረው ልቦለድ አይደሉም የተባሉበት ምክንያት ለእያንዳንዷ ድርጊት ተጠየቃዊ ትንታኔ ስለሚያቀርቡ አይደለም? ፋንታዚን ምን አመጣው?
ስሜትህን በደንብ ገልጬያለሁ የምትለው በግጥምህ ወይስ በልብ ወለድ?
አለሜ ይቻልሃል (ከጋምቤላ)
ይስማዕከ፡- በሁለቱም ዘርፎች የገለጥኩት ይመስለኛል፡፡ በግጥሞቼ በኩል መቅረብ ያለበትን ሀሳብ በነሱ በልቦለዶቼም እንደዛው፡፡ ለግጥም የሚሆን ሀሳብ አለ፤ ለልቦለድ የሚሆን ሀሳብ አለ፤ ለቴአትር የሚሆን ሀሳብ አለ፡፡ በጥንቃቄ መመረጥ አለበት፡፡ ለዘፈን የሚሆነውን ግጥም ለማስለቀሻ ከማድረግ መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡
ዴርቶጋዳ መፅሐፍህ በሁለት የተለያዩ ሽፋኖች የታተሙት በምን ምክንያት ነው? የሁለቱ ሽፋኖች ትርጓሜስ ምንድነው?
ደቻሳ ደሜ (ከአምቦ)
የመጀመሪያው ሽፋን በወጣ በሳምንቱ አንዳንድ አሉታዊ ነገሮች ወደ እኔ መጡ፡፡ መጽሀፉን ሳያነቡት ገና ሽፋኑን አይተው ፈረዱበት፡፡ ከሃይማኖት ጋር ሊያያይዙት ከጀላቸው፡፡ ወዲያው ጀርባውን የሰጠ ሰው ያለበት ሽፋን ይዤ ወደ አሳታሚዬ ሂጄ አስቀየርኩት፡፡ ጀርባውን የሰጠው ሽፋን ፊቷን ከሰጠችው ሽፋን የተሻለ ሆኖ ተገኘ፡፡ተበሳጭቼ ነበር ጀርባውን እንዲሰጥ ያደረግኩት፡፡ በኋላ የበለጠ ሆኖ ተገኘ፡፡ ለካስ ለበጎ ነበር ያጉረመረሙብኝ፡፡ ጀርባውን የሰጠው ጎልማሳ ምስጢሩን ከፊትለፊቱ ላለው ሲደብቅ ባንጠለጠለው ባለጉጥ መስቀል በኩል እኛ እንድናየው ሆነ፡፡ አሁን ላይ ሆኜ ሳስበው እንኳንም የመጀመሪያውን ሽፋን ተቃወሙኝ፡፡ የተሻለ እንዲሆን ነበር ለካ፡፡ በነገራችን ላይ በዴርቶጋዳ ላይ ያለውን ባለጉጥ መስቀል ወርቅና ብር አንጣሪዎች በዛው ቅርፅ እየቀረጹ ሲሸጡት አይቻለሁ፡፡ በወህኒ ቤት (በተለይም በሀዋሳ ወህኒ ቤት) ህይወታቸውን የሚገፉ እስረኞች ደግሞ በእንጨት እየቀረፁ በመሸጥ መተዳደሪያ ሲያደርጉት አይቼ ተደንቄያለሁ፡፡
መፅሐፍቶችህን በተመለከተ ከተሰጡህ አስተያየቶች በጣም አስገራሚ ናቸው የምትላቸውን ብትጠቅስልኝ? በጋዜጦችና መፅሔቶች የሚቀርቡ ሂሶችንስ እንዴት ትመለከታቸዋለህ?
ሳምሶን ፍፁም (ከተክለሃይማኖት)
ይስማዕከ፡- አንድ ማንም የሚረዳው ጉዳይ አለ፡፡ ስንቱ ፅፎ ሳይነበብለት የቀረ አለ? ስድብ አንኳ የናፈቀው ስንት አለ! በየትኛውም ጎራ በእኔ ላይ የሚሰነዘሩ ሂሶች ሊያስደስቱኝ ይገባል፡፡ ያስደስቱኛልም፡፡ ለእኔ ሥራ ትኩረት ሰጥተው የተቹኝንም ያመሰግኑኝንም ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፡፡ እኔን በዓለማችን ላይ ካሉ ድንቅ ድንቅ ፀሐፍት ጋር አመሳስለው የወረፉኝ ራሳቸው ሳያውቁት ለእኔ ቦታ ሰጥተውኛል፡፡ እኔን ረስተው መጽሀፎቼን ብቻ ሲመለከቱ ግን ከእኔ ከወጡ በኋላ ሥራዎቼ የታሪካችን አካል መሆናቸውን ይገነዘባሉ፡፡ የሀገራችን ስነ-ፅሁፍ ከሌሎች ሀገራት የሚያንስበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ ከሌሎች ሀገራት ቀድመን ስነ ፅሁፍን የጀመርንና የበለፀገ የጽሁፍ ታረክም ያለን ሕዝቦች ነን፡፡ ገና ገና ያልተፃፈባቸው ጉዳዮች፣ ባህሎች፣ አፈታሪኮች… አሉን፡፡ ሀገሪቷ የፀሀፊ እንጂ የሚፃፍ ሀሳብ እጦት የለባትም፡፡ ምዕራባውያን ደራስያን በዚህ ሰዓት የሚጽፉበት ጭብጥ አጥተው የሁሉም ደራስያን ስራዎች ማለት ይቻላል ተመሳሳይ እስከመሆን ዘልቀዋል፡፡ እነሱ እንጂ እኛ ሀሳብ ለቀማ ወደ እነሱ አንሄድም፡፡ ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ ይሏል ይህ ነው፡፡ ራሳችን አሳንሰን ማየት የለብንም፡፡ እኔ
በበኩሌ ይህ አባዜ የለብኝም፡፡ ከዚህ አኳያ ራሱን አሳንሶ የሚያይ ሥራዎቼን በከንቱ ጭቃ ሲቀባቸው ዝም ማለት የለብኝም ነበር፡፡ ነገር ግን ምላሹ በሌሎች ያምራል ብዬ ትቼዋለሁ፡፡ ቃለ መጠይቅ እንኳ ተቆጥቤያለሁ፡፡ ይህ የእኔ ስራ አይደለም፡፡ ሀገራችን በጣት የሚቆጠሩ ይሁኑ እንጂ ጥሩ ጥሩ ሀያስያን አሏት፡፡ እንደነ የሻው ተሰማ፣ አስፋው ዳምጤ፣ አለማየሁ ገላጋይ፣ ገዛኸኝ ፀ. በሩቅ ይሁን እንጂ አብደላ እዝራን ወዘተ መጥቀስ ይቻላል፡፡ ለመጪው ትውልድም መኖር መለማመድ አለብን፡፡ ያልተወለደው ደራሲም እንዲፅፍ ልንተወው ይገባል፡፡ ከዚህ በቀር በእኔ ላይ የሚሰነዝሩ ሂሶችን በፀጋ እቀበላለሁ፡፡ ጠቃሚም ነው፡፡ ነገር ግን በተራ ስድቦች አንባቢ ለመበተን የሚተጉትን ለሀገራችን ስነጽሁፍ ስንል ልንታገሳቸው አይገባም፡፡ ለእኔ የሚወረውሩት ድንጋይ የሌሎችንም አንባቢ ያስበረግጋል፡፡ ደህና ብቅ ያለውን አንባቢ ወደነበረበት ለሚመልሱና አብዮቱን ለመቀልበስ ቀይ ውዥንብር የሚነዙትን በነጭ ውሽንፍር እንመልሳቸው ዘንድ የአብዮቱ አደራ አለብን፡፡ (…ቀጭን ሳቅ) …ይህን ስል ግን
ጠቃሚ ጠቃሚውን ገንቢ ሂስ ከመቀበል አልቆጠብም፡፡ ሥራዬንም እንደ 97ቱ ምርጫ እንከን የለሽ ብዬ ልመፃደቅበት አልከጅልም፡፡ የጥበብ ሥራ መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡
“ተልሚድ” የተሰኘ ድርሰትህ አቀባበሉ እንዴት ነበር? ሰሞኑን ለሕትመት የበቃው “ተከርቸም” መጽሐፍሕ ከቀድሞዎቹ ድርሰቶችህ በምን ይመሳሰላል? የጭብጥ መመሳሰል የሚንፀባረቅ አይመስልም?
ልዑል ሐድጉ (ከተክለ ሃይማኖት)
ይስማዕከ፡- ለተልሚድ ጥሩ አቀባበል ተደርጎለታል፡፡ አንድ ሃያሲ የፃፉት ፅሁፍ አስገርሞኛል፡፡ ተልሚድንና ሚራዥን እያነፃፀሩ የፃፉበት እይታ የሚገርም ነው፡፡ በህይወት ጥልቀት ተልሚድ ከሚራዥ እንደሚልቅ ፅፈዋል፡፡ ሰፊ ምርምር አድርገው ሳይቸኩሉ ላደረጉት ጥረት እይታቸውን ሳላደንቅ አላልፍም፡፡
ተከርቸም ገና ሰሞኑን መውጣቱ ነው፡፡ በኢሜል በምን ያገኘኋቸው አስተያየቶች መልካም ናቸው፡፡ እንደ መጀመሪያ ስራነቱ ለሰዎች አይመጥንም፤ ቢሆንም አንባቢዎቼ ስለኔ አጀማመር ያውቁ ዘንድ እንዲያነቡት እድል መስጠት አለብኝ ስል ነበር ያሳተምኩት፡፡ ነገር ግን ካሰብኩት በተቃራኒ ሆኖ አንባቢዎቼ ወደውታል፡፡ ከሌሎቹ ልቦለዶቼ የሚለየው ነጠላ ታሪክ እንጂ ውስብስብ ታሪክ ስለሌለው ነው፡፡ የሚፈትን ሴራም የለውም፡፡ ….ተከርቸምን እንደ አንድ ልቦለድ ከራሱና ከተነሳበት ጭብጥ ጋር ሲያነፃፅሩት በቂ ሆኖ አግኝተውታል፡፡ ለማንኛውም እኔ በዚህ ሰዓት ትኩረቴ በቁጥር ሶስት ዴርቶጋዳ ላይ ነው፡፡ የጭብጥ መመሳሰል የተባለው ከምን የተነሳ እንደሆነ አልገባኝም፡፡ ሁለቱ ተከታታዮች ማለትም ዴርቶጋዳና ራማቶሓራ ተከታታይ እንደመሆናቸው መጠን በአቢዩ ጭብጥ የመመሰሳሰል ግዴታ አለባቸው፡፡ ንኡሳን ጭብጦቻቸው ግን ይለያያሉ፡፡ ተልሚድና ተከርቸም ግን ከሌሎቹ በተለየ ጭብጥ አንስተዋል፡፡ እነዚህን ጭብጦች ለማመሳሰል ከተሞከረ የኢያን ራንድን ስራዎች ምን ልንላቸው ነው?
በሕይወትህ ሞክረህ ያልተሳካልህ ወይም ተስፋ የቆረጥክበት ጊዜ ነበር?
በሕሪያ ኑሩ (ከአዲስ አበባ)
ይስማዕከ፡- ገና ለአቅመ ተስፋ መቁረጥ አልደረስኩም፡፡ የተመኘሁት ሁሉ ይሆናል ብዬ የማምን ሞኝ አይደለሁም፡፡ የሞከርኩት ሁሉ ይሳካል ብዬም አልጃጃልም፡፡ ተስፋ የምቆርጥበት ጊዜም አልደረሰም፡፡ ገና በሃያዎቹ የምገኝ ወጣት ነኝ፡፡ ብዙ ለመሞከር እንጂ ለአቅመ ተስፋ መቁረጥ አልደረስኩም፡፡ በመሠረቱ በመሳካቱ ብቻ ሳይሆን በመሞከሬ የምደሰት ሰው ነኝ፡፡ ተሸናፊ መንፈስ የለኝም፡፡ ተሸናፊዎች ስልቹዎች ናቸው፡፡ ደስ የሚለኝ የኮሎምበስ ንግግር አለ፡፡ በአንድ ገጣሚ እንዲህ ተገልጦአል፡፡ “በሚያስገመግም ድምፅ በሚስፈራ ቃሉ
አላቸው ኮለምበስ ቀጥሉ ቀጥሉ
……… አሁንም ቀጥሉ”
ሰላማዊ ውቅያኖስን ለማቋረጥ ሲሞክር መርከበኞቹ እንመለስ እያሉ ሲያስቸግሩት የሚመልስላቸው ነው፡፡
የሕይወት ፍልስፍናህ ምንድነው?
የሺሃረግ ታዬ (ከአዲስ አበባ)
ይስማዕከ፡- “እያሻሻሉ መግፋት እየተሻሉም ወደፊት! ለተሻለ ህይወት” የሚል ነው፡፡ በየቀኑ መወለድ በየዕለቱ ማደግ፡፡ የንጋቷን ጮራ በደስታ መቀበል – የምሽቷን ጀምበር በሀሴት መሸኘት፡፡ በራስ ደስተኛ መሆን፡፡
“አበሻ ቅንድቡ ነው እኮ ሰማዩ
አብረው ይጠልቃሉ ዓይኑና ፀሐዩ” የሚል ግጥም አለህ፤ ምን ማለት ፈልገህ ነው?
ክንፈ አጋ (ከላፍቶ)
ይስማዕከ፡- እኛ ኢትዮጵያውያን ፀሐይ ስትገባ በራችንን መቀርቀር የለብንም፡፡ እንደ ሌሎች አለም ነዋሪዎች የሥራ ባህላችንን ማጠንከር አለብን፡፡ ቀኑን በአሉባልታ ሌቱን በመኝታ ማሳለፍ የለብንም፡፡ 24 ሰዓት የሚሰሩ ድርጅቶች ስንት ናቸው? ከመሸታ ቤቶች በቀር እዚህ ሀገር ከፀሀይ ግባት በኋላ ምን ክፍት በር ይገኛል? ዓይኖቻችንና
ፀሐያችን እኩል እያንቀላፉ እንዴት ነው ከሌሎች ሀገራት ጋር የሚነፃፀር እድገት ሊኖረን የሚችል? ለዛ ነው፡፡
በዴርቶጋዳ መፅሐፍ ውስጥ ኢትዮጵያዊ/ት ያልሆኑ ለምሳሌ ሻጊዝ፣ ሚራዥ፣ ዣንጊዳ፣ ሜሮዳ የመሳሰሉ ስሞችን አብዝተሕ መጠቀም ለምን ፈለግህ?
ኢያሱ አ. (ከማይጨው)
ይስማዕከ፡- ኢትዮጵያዊ ስም ሲባል የትኛው ነው? አበበ… በቀለ ወዘተ… ማለት ነው እንዴ? ከሰማኒያ በላይ ብሔረሰቦች ባሉበት ሀገር ነው የምንኖር፡፡ ብዙ አስገራሚ ስሞች አሉ፡፡ አልተጠቀምናቸውም፡፡ ስሞች ብሔርን ስለሚገልጹ በዴርቶጋዳ ውስጥ መጠቀም አልፈለግኩም፡፡ “አበበ” ብለው አማራ ሊባል ነው፡፡ “ቢቂላ” ብለው ኦሮሞ ሊባል ነው፡፡ ከዚህ ሁሉ ጣጣ ለገዛ ገጸ ባህርዬ የራሴን ስም ባወጣ አይሻለኝም? ወስከምቢያ ሙሉ ፍትፍት አይጠይቀኝ? ከመጽሀፉ አጠቃላይ ይዘት ጋርም አይሄድም፡፡ አንድነትን በሚሰብክ መጽሀፍ ውስጥ ሊያውም ከመላው ኢትዮጵያ ተሰባስበው ኢትዮጵያን ለመታደግ በተጠራሩ ጀግኖች መካከል በስም የዘር ልዩነታቸውን ማጉላት አስፈላጊ አይመስለኝም፡፡ በራማቶሓራ ውስጥ ግን ለጭብጡ ጠቀሜታ ሲባል በስሙ የተጠራ ገጸባህርይ አለኝ፡፡ እሱም ማርዬ ዋቆ ማርዬ ነው፡፡ ይኸውም በታሪካዊቷ ጎንደር ከተማ ውስጥ ለሚኖሩ ኦሮሞዎች ብቻ ሳይሆን ሌሎች ኢትዮጵያውንም በየትኛውም ቦታ ተዘዋውረው መኖርም ሆነ መስራት እንደሚችሉ ለመግለጥ ነው፡፡ አባይ ዳር ቤቱን ከወንዙ ዳር ሰርቶ በአበባ ባጌጠ ግቢ ውስጥ መኖር ለአማራ ብቻ የተፈቀደ ሳይሆን ለማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንደሆነ ለማስገንዘብም ነው፡፡ ከዚህ በተረፈ እነዚህ ስሞች የፈረንጅ ስሞችም አይደሉም፡፡ ስማቸውን ከውስጣዊ ባህርያቸው ጋር እንዲሄድ አድርጌ ወደ ቁጥር ቀይሬ በቀመር ነው ያወጣሁላቸው፡፡ አንባቢ ግዴታ ይህን ሁሉ ያውቅ ዘንድ አይገደድም፡፡ ኮድ ነው፡፡
ራማቶሐራ መፅሐፍ ላይ ዩኒቨርስቲ እግር እንጂ ጭንቅላት አያስፈልገውም ብለሀል፡፡ አንተ ይህን ልትሆን ትችላለህ ወይስ ትደግፈዋለህ ወይ?
ታዴዎስ መለስ (አ.አበባ)
ይስማዕከ፡- ባያቸው አስገራሚ ዝቅጠቶች የተነሳ ወልደ ህይወት የሚባለው ገፀ ባህርይ እንዲህ ሲል በዲያሪው ላይ ፅፏል፡፡ ሁኔታዎችን ላየ አያስብልም አይባልም፡፡ ወደ ዩኒቨርስቲ በእግሩ እንጂ በጭንቅላቱ ያልገባ ሞልቷል፡፡ ሀቅ ነው፤ ግን ይጎረብጣል፡፡ የእያንዳንዱ ገፅ ባህርይ አስተሳሰብ የደራሲው አስተሳሰብ ነው ማለት አይደለም፡፡ አንተ ይህን ልትሆን ትችላለህ? ወይስ ትደግፈዋለህ? የሚለው ጥያቄ ግን ፈገግ የሚያሰኝ ነው፡፡ እንዴት ልደግፈው እችላለሁ? እኔስ በእግር የገባሁ እመስላለሁ? (…ረጅም ሳቅ)፡፡
በዴርቶጋዳ መፅሐፍሕ አንድ ለማኝ ስለ መለስና ስለ መንግስቱ ስም የሚለምንበት ቦታ አለ፡፡ አንተ ራስህ ፖለቲከኛ ነህ? የፖለቲካ መፅሐፍትን ታነባለህ? ከሙዚቃ የማንን ነው የምትሰማው?
እኔ ፖለቲከኛ አይደለሁም፡፡ መጽሀፍ ከሆነ ግን እንኳን ስለ ፖለቲካ ስለ ማስቲካም ቢሆን ጠራርጌ አነባለሁ፡፡ እንደ አንድ ዜጋ ስለ መብትና ግዴታዬ እታገላለሁ፡፡ ለተደራጀ የፖለቲካ ኃይልም ሆነ ለአንድ ተራ ግለሰብ በክብሬ ላይ አልደራደርም፡፡ በኢትዮጵያዊነቴ ማግኘት ያለብኝን የሰብአዊም ሆነ ዲሞክራሲያዊ መብት እስከመጨረሻው እጠይቃለሁ፡፡ ሌሎቹም ለፍትሐዊነትና ለሙሉ ነፃነታቸው ይታገሉ ዘንድ እጽፋለሁ፡፡ ሀገራዊ ግዴታቸውን እንዳይዘነጉትም አስገነዝባለሁ፡፡ ይህ ፖለቲከኛ ቢያስብል አያስጨንቀኝም፡፡ ገፀ ባህሪዬን ስቀርፀው ሰው ሰው ይሸት ዘንድ ቁመናውና አካላዊ ገጽታውን ብቻ ሳይሆን አመለከካቱና አዕምሮው የተሠራበትን ማህበራዊ፣ ሃይማኖታዊና ፖለቲካዊ አካባቢውንም እጽፋለሁ፡፡ አለበለዚያማ በምኑ እኔን ይመስለኛል? ምን ቁመቱ ለግላጋ ቢሆን የሚወክለውን ማህበረሰብ ይገልፃል? ወደድንም ጠላንም ስነ ልቦናችን የተሠራው ፍልስፍናችን የተበጀው ከምንኖርበት ሀገርና በውስጡ ከያዛቸው ማህበረሰቦች ኃይማኖታዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ አመለካከት ጭማቂ ነው፡፡
ብዙ ገዳማትና ታሪካዊ ቦታዎች በመፅሐፉ ውስጥ ይጠቀሳሉ፡፡ ቦታዎቹ ድረስ ሄደህ አይተህ ነው ወይስ መፅሐፎች አንብበህ ነው የገለፅካቸው?
ሚካኤል ድንበሩ (ከአሰላ)
ይስማዕከ፡- ከሰሜን እስከ ደቡብ ጫፍ ከምዕራብ እስከ ምስራቅ ጽንፍ ሀገሬን ዞሬያታለሁ፡፡ ከመጽሀፎቼ ያገኛሁትን ገንዘብ በአብዘኛው ያዋልኩት ለጥናት ነው፡፡ ያልሄድኩት ኤርትራ ብቻ ነው፡፡ በዴርቶጋዳና በራማቶሐራ ውስጥ ያሉትን ገዳማት፣ ሸለቆዎች፤ ተራራዎች፣ መንገዶችና ከተማዎች ብቻ ሳይሆን ተልሚድን ስጽፍ በምስራቅ እስከ ጂቡቲ ተጉዤ በየስርጉዋጉጡ ባዝኛለሁ፡፡ እኛ ሀገር በጽሁፍ የተቀመጠ አጥጋቢ መረጃ ከወዴት ተገኝቶ?
ያንተ ማስተር ፒስ የትኛው ድርሰትህ ነው?
አሕመድ ሁሴን (ከመድሃኔዓለም)
ይስማዕከ፡- የሰራሁት ሁሉ ማስተር ፒስ ይሆናል የሚል ከንቱ እምነት የለኝም፡፡ ቢሆንም በዚህ ሰዓት የኔ ማስተር ፒስ ይኸኛው ነው ለማለት አልደፍርም፡፡ ገና መጻፍ የጀመርኩ ሁሉ አይመስለኝም፡፡ ሀቁን ዱብ ለማድረግ የኔ ማስተር ፒስ የተፃፈ አይመለስለኝም፡፡ አዕምሮዬ ውስጥ አልቀው ጊዜና ቦታ የሚጠብቁ ሥራዎች አሉኝ፡፡ የኔ ማስተር ፒስ ድርሰት ገና ከምጽፋቸው ውስጥ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡
በአንድ ወቅት በዩኒቨርሲቲ የመጽሐፍ ኤግዚቢሽን ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ አንተም በዚያ ዝግጅት ተገኝተህ ለምትጠየቀው ጥያቄ መልስ ትሰጣለህ ተብሎ ነበር፤ ግን ቀረህ፤ ምክንያትህ ምን ነበር? ብዙዎች ፈርቶ ነው አሉ? እውነት ነው?
ይስማዕከ፡- ቢሉ አይፈረድባቸውም፡፡ ፈሪ ብሆን ኖሮ ሀገር ጥዬ እንድወጣ አያሌ ተለማማጮች ነበሩኝ፡፡ ብዙ እንድጽፍ የሚፈልጉና በውጪ ሀገር ያሉ አንባቢዎቼና ወዳጆቼ በወቅቱ ከበቂ በላይ ወትውተውኛል፡፡ ሀገሬን እነማን እንዲኖሩባት? አንድ ጸሀፊ ከሀገሩ ወጣ ማለት ሞተ ማለት ነው፡፡ የብዕሩ ቀብርም ተፈፅሟል፡፡ ስንቱ ብዕረኛ
በስደት ጨንግፎአል! እነ ገሞራው… እነ አብደላ እዝራ… ስንቱ፡፡ …አንዳንዶቹ በእርግጥ ቋጥረውት የሄዱት ስንቅ እስኪያልቅ ይፅፉ ይሆናል፡፡ ግን አንድ ቀን ጥይት ይጨርሳሉ፡፡ ፈሪ ለእናቱ ያገለግላል በሚለው የፈሪዎች መፈክር አላምንም፡፡ ላመኑበት ነገር መሞት ጀግንነት ነው፡፡ በእርግጥ በወቅቱ የእኔ ጉዳይ ቋፍ ላይ ደርሶ ነበር፡፡ ስሜታዊነት ጠንቶ ነበር፡፡ እኔ ስለ እኔ ከፈራሁት ፍርሃት የላቀ ወዳጆቼና አንባቢዎቼ ስለ እኔ ፈርተው ተጨንቀውም ነበር፡፡ አንዳንድ ስሜታዊና እንደ ዝንብ ወተት በማያገባቸው ጥልቅ የሚሉ ቀሊል ሰዎች አንድ ስህተት ቢሠሩ ብዙ ህልሞቼ እንዳይዳፈኑ ብዘዎች ስጋታቸው ነበር፡፡ በተለይ ተከታታይ መጽሀፍ ተጀምሮ ሳያልቅ አንድ ነገር መሆን ቀላል አይደለም፡፡ ዴርቶጋዳ በቁጥር ሶስት ባይጠናቀቅ ብዙ ህልም ብዙ ቅስም ይሰበራል፡፡ መጠንቀቄ ከፍርሃት የመነጨ ሳይሆን ከአላማ የፈለቀ ነበር፡፡ ተጠንቅቄም አልሆነም፡፡ በመጠኑም ቢሆን እኔን ለማሸማቀቅ ጥረት ተድርጓል፡፡ ከግለሰብ ከመነጨ ይሁን ከድርጅት የታጨ መሆኑ ሳይታወቅ ረቂቄን ተነጥቄአለሁ፡፡ ምን ይደረግ ይህ ሴራ እስካሁን ግልፅ አልሆነም፡፡ ችግር ብዙ ያስተምራልና ቁጥር ሶስት ግን ብርቱ ጥንቃቄ ተደርጎለታል፡፡ የራማቶሓራን እጣ ፋንታ መቅመስ አይችልም፡፡
የሆነው ሆኖ አዲስ አበባ ዪኒቨርስቲ በዴርቶጋዳ ዙሪያ በተደረገው ውይይት ላይ ለመገኘት ከሀዋሳ ተነስቼ ወደ አዲስ አበባ በእለቱለት ስጓዝ በገጠመኝ የትራንስፖርት መደናቀፍ አዲስ አበባ የገባሁት ፕሮግራሙ ተጠናቅቆ ሰው ሲበተን ነበር፡፡ የፕሮግራሙ መሪዎችና ጋሽ ደረጀ ገብሬም የደረስኩበትን እያንዳንዱን ከተማ በስልክ ይከታተሉኝ ነበር፡፡ ሆኖም ጥረቴ አልሰመረም፡፡ በወቅቱ እኔ መገኘት እፈልግ ነበር፡፡ ለምን ቢባል አባዛኞቹ ስለ እኔ ይወሩ የነበሩት አሉባልታዎች መልስ ያስፈልጋቸው ነበር፡፡ ስለ እኛ ካልተናገርን አሉባልታዎች ክፍተቱን ይሞሉታል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ከፍተኛ ተከፋይ ነህ ይባላል፤ ለድርሰትህ የሚከፈልህ ዋጋ ይመጥንሃል?
ይስማዕከ፡- ከፍተኛ ተካፋይ የሆንኩት ሥራዎቼ በብዛት በመታተማቸው ነው፡፡ ሆኖም በገንዘብ ካገኘሁት የላቀ ክፍያ ተከፍሎኛል፡፡ ሳይገባኝ ተከብሬያለሁ፡፡ ሳይገባኝ ፍቅር ተሰጥቶኛል፡፡ በገንዘብ የማይተመን ሞገስ አግኝቼያለሁ፡፡ ይህን በገንዘብ አልሸጠውም፤ አልለውጠውም፡፡ ሥራዎቼ ዩኒቨርሲቲ ሆነው አስተምረውኛል፡፡ ከአለም ዙሪያ የመጣልኝ አስተያየት ቁጭ አድርጎ አስተምሮኛል፡፡ ጥያቄው ገንዘብን በተመለከተ ከሆነ ለገንዘብ ያለኝ አመለካከት ትንሽ ነው፡፡ ገንዘብን እንደተረፈ ምርት እንጂ እንደ ምርት ማየት የለብንም፡፡ ገንዘብ የማይገዛቸውን አያሌ መክሊቶች አግኝቼያለሁ፡፡ በእርግጥ ለጥበብ የሚገባ ክፍያ የለም፡፡ ጥበብን በገንዘብ ለመሸጥ የሚጠበብ ያለም አይመስለኝም፡፡ ነገር ግን የሽያጩ ብዛት ተነባቢነትን ለመመዘን ሳያገለግል አይቀርም፡፡
ዕንቁ፡- ከቀድሞ ደራሲያን… በድህነት ተቆራምደው ቤተሰባቸውን በትነው መቀበሪያ አጥተው የሞቱ አሉ፡፡ እናንተ ደግሞ በሥራችሁ ጥሩ ተከፋይ ናችሁ እድል ነው ወይስ ጊዜ? ወይስ የሥራችሁ ደረጃ መበላለጥ?
ይስማዕከ፡- እናንተ የሚለው አይመለከተኝም፡፡ አንተ በሚል ይቀየርልኝ፡፡ ሌሎች ስለራሳቸው ይናገሩ፡፡ በረሃብ ተቆራምደው የሞቱት የተባሉት ደራስያን ቀስቅሰን ብንጠይቃቸው ምን እንደሚሉ አላውቅም፡፡ እኔ በበኩሌ ሥራዎቼን ከሞቱትም ሆነ ካሉት ደራስያን ጋር በማነፃፀር ጊዜዬን አላጠፋም፡፡ የራሴን ሥራ በአግባቡ መሥራት እና ነፍሴ በመራችኝ እና ውስጤ ባስመለከተኝ እጓዛለሁ እንጂ እንደ አድያም የሌሎቹን መነጽር ማድረግ አልፈልግም፡፡ እድል በሚባለው ከንቱ ሀሳብ ብዙ ሰዎች ይጃጃላሉ፡፡ እንዲያውም የስድሳዎቹና የሰባዎቹ ትውልድ አንባቢ ነበር፡፡ በዛ ወቅት ጠብሰቅ ያለ ሥራ የሠሩ ጠንካራ ደራስያን እስካሁን ይነበባሉ፡፡ ዘመን የራሱን አሻራ ይመርጣል፡፡ አልፎት ለሄደው የመጨነቅ ግዴታ የለብኝም፡፡ አድምተው የፃፉት ተነቦላቸዋል፡፡ ከትውልድ ጋርም ተሸጋግረዋል፡፡ እንዲያውም የመነበብ ፈተና ያለበት ይኸኛው ትውልድ ነው፡፡ ኢንተርኔቱ፣ ሙዚቃው፣ ሲኒማው፣ ጫጫታው፣ ኳኳታው…. ብዙ ነው፡፡ ከዚህ መሀል አንድን አንባቢ ነጥሎ ለማስቀመጥና ለማስነበብ ብርቱ ጉልበት ይጠይቃል፡፡ ጠርምሶ የሚገባ ሃሳብና ብዕር ያስፈልጋል፡፡ ፊደል የቆጠረው ጥቂት ይሁን እንጂ በነሱ ዘመን ምን ሌላ ሳንካ ነበር? ቴሌቪዥን እንኳ በአንድ ቀበሌ ውስጥ አንድ አይገኝም ነበር፡፡ ሬዲዮና ሰዓት ብርቅ ነበር፡፡ አሁን አንድ አንባቢ አንድ ገጽ ሳያነብ ሞባይሉ አስሬ ይጠራል፡፡ ጀሮው በአስገራሚ ነፋስ አመጣሽ ድምፆች ይደቃል፡፡ ዓይኖቹን የሚይዙ ትዕይንቶች በየደቂቃው ይፈራረቃሉ፡፡ በዛኛው ዘመን ከማንበብ በቀር ምን አማራጭ ነበር? ትውልዱን ያለመቀበል አባዜ ካልሆነ በቀር ይህኛው ትውልድም የተጋፈጣቸው የንባብ ሳንካዎች አሉ፡፡ የመፃህፍትን ብዛት ስናይስ? በዛኛው ዘመን በአንድ ወር ውስጥ ስንት መጽሀፍ ይታተም ነበር? ስንት መጽሀፍ ወደ ሀገር ቤት ይገባ ነበር? ዛሬስ? መልሱን ይህኛውንም ያኛውንም ትውልድ ያየ ይመልሰው፡፡
ተልሚድ መፅሐፍ ከሌሎች በምን ይለያል?
ሳምራዊት አድማሱ (ከቤላ)
ይስማዕከ፡- ተልሚድ የተከታታዮቹ ዴርቶጋዳና ራማቶሓራ አካል አይደለም፡፡ የራሱ ጭብጥ፣ ይዘትና ፍልስፍና ያለው ነው፡፡ መቼቱም ምስራቅ ኢትዮጵያን የሚያስቃኝ ነው፡፡ ሀገሪቱን እንደ መዥገር የሚጠቧትን ሸፍጠኞችና ሴረኞችን ዠንመረቂ በሚባል ገፀ ባህርይ ወክሎ የሚያሳይ ልቦለድ ነው፡፡ ተልሚድ የተባለው ገጸ ባህርይ ይህን ሸፍጥ
የምንታዘብበት የታሪኩ ሀዲድ ነው፡፡
በቅርቡ ለሕትመት ከበቃው “ተከርቸም” መፅሐፍ ምን አስተያየት አገኘህበት? ተልሚድ ከታተመ ከ3 ወር በኋላ መውጣቱ ለምን አስፈለገ?
ናዖድ በኩረጽዮን (ከአዲስ አበባ)
ይስማዕከ፡- ተከርቸም የወጠው ገና በቅርቡ ነው፡፡ አንባብያን ገና አላጣጣሙትም፡፡ ቢሆንም ያነበቡት ሰዎች ቋንቋውንና አቀራረቡን ወደውታል፡፡ ይህን ያህል አንባብያን ይወዱታል ብዬ አልጠበቅኩም ነበር፡፡ እንደሌሎቹ ልቦለዶቼ ውስብስብ ሴራም ሆነ አእምሮን የሚፈትን ታሪክ የለውም፡፡ ታሪኩ ነጠላ በመሆኑ ከሌሎች ሥራዎቼ ጋር
አይነፃፀርም፡፡ ሆኖም የመጀመሪያ ሥራዬ እንደመሆኑ መነሻዬን አንባብያን ያውቁ ዘንድ ያቀረብኩት ነው፡፡ እንዲያም ሆኖ ጥሩ ጥሩ አስተያየቶች እየመጡልኝ ነው፡፡ ያልጠበቅኩት ነው፡፡ ተልሚድ ከወጣ ከ3 ወራት በኋላ ለምን ወጣ ለተባለው፤ እኔ ሥራዬን መሥራትን እንጂ በየስንት ወሩ ይውጣ፣ በየስንት አመቱ ይታተም በሚለው እንደ እርጉዝ ቀን እየቆጠርኩ አልጨነቅም፡፡
ዕንቁ፡- በ“ተከርቸም” መፅሃፍ ላይ የአንድ አካባቢ ቀበሌኛ ቋንቋዎችን አብዝተህ መጠቀም ያስፈለገህ ለምንድነው?… የከተማ ሠው ብዙዎችን ቃላት ሳያውቅ ቢቀር ምን ትጠቀማለህ?
ይስማዕከ፡- የፃፍኩትን አካባቢ ማህበረሰብ ቋንቋ መጠቀሜ ያንን ማህበረሰብ ከማጥናቴ በመነጨ መሆኑ መታወቅ አለበት፡፡ ይህም የሚበረታታ ነገር እንጂ የሚነቀፍ አይመስለኝም፡፡ እንደ ለማኝ ቆሎ የቆላው ከደጋ የተቀላቀለ አማርኛን በተከርቸም ውስጥ አልተጠቀምኩም፡፡፡ ይህም ውበቱን ያጐድለዋል ብዬ አምኜበት ነው፡፡ የከተማ ሰው የማያውቀውን ቢያውቅ ምን ይሆናል (ጥቂት ሳቅ)….. እንዲያውም ደስ ይሰኝበታል ብዬ አምናለሁ፡፡ ማንም ሰው ጊዜውን አጥፍቶ ሲያነብ የሚያውቀውን ለመከለስ አይመስለኝም፡፡ ትውልዱ የጠፋ ማንነቱን ፍለጋ ላይ ነው፡፡ ቃላት ደግሞ አስተሳሰብም ናቸው፡፡ ሳይቀበሩ ማስቀረት አለብን፡፡ እንግሊዝኛን ከመቀላቀል የማያድኑ አያሌ ወርቃማና ጣፋጭ ቃላት አሉን፡፡ እገሌ ወደደው እገሌ ጠላው ብዬ አልብሰለሰልም፡፡ ያማረኝን እጽፋለሁ፡፡ ማንም በዚህ የማንነት ፍለጋ ላይ እጄን እንዲጠመዝዘኝ አልፈቅድም፡፡ ከተሜ ራሱን መርሳት ማንነቱን መዘንጋት የለበትም፡፡
ዕንቁ፡- የ“ተከርቸም” ታሪክ ፍሠትና የሴራ ውስብስብነት ከነዴርቶጋዳ አንፃር ሲታይ በጣም የተዳከመ አይሆንም? አፃፃፉስ በኃይለስላሴ ዘመን ከሚወጡ የድሮ መፅሃፍት ጋር የሚቀራረብ አይመስልም?
ይስማዕከ፡- ብያለሁ እኮ፡፡ ትርክቱ በነጠላ ታሪክ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ሁሉም መጽሀፎቼ አንድ አይነት እንዲሆኑ ይፈለጋል? የተለየ ነገር ከሌለኝ በአንድ መጽሐፍ ማቆም አለብኝ፡፡ ሰዎች ግራ የሚጋቡት ቀድመው በገመቱት ስለማያገኙኝ ነው፡፡ እንዲያውም በአዲስ ሙከራ ብቅ እንድል ሊፀልዩልኝ ይገባል፡፡ አዎ! ተከርቸም ከተልሚድ ጋር መነፃፀር የለበትም፡፡ ልቦለዶቼ በፃፍኩባቸው ዘመን እንጂ በታተሙበት ዘመን መደርደር የለባቸውም፡፡ በቅደም ተከተል ላስቀምጥ፡- ተከርቸም፣ ተልሚድ፣ ዴርቶጋዳ፣ ራማቶሓራ…..፡፡ ተከርቸም የመጀመሪያ እንደመሆኑ ከብኩርናው
አንፃር መታየት አለበት እንጂ አሁን እኔ ያለኝን የስነጽሁፍ እርከን መስፈሪያ መሆን አይቻለውም፡፡ የኃይለ ስለሴን ዘመን ቋንቋ ይመስላል ተብሏል፡፡ ሊሆንም ይገባዋል፡፡ በመባሉም ደስተኛ ነኝ፡፡ ተከርቸምን የፃፍኩት በዘመናዊው ቋንቋ ሳልበረዝ ገና ከገዳም ከመውጣቴ ነው፡፡ ቋንቋዬን የከተማ ቋንቋ ሳይበርዘው፡፡ አንደበቴ በከተማው አማርኛ ሳይቆለፍ፡፡ ገና እንደወረድኩ ነው የጻፍኩት፡፡ ለዛም ነው ታሪኬን ያሳይ ዘንድ በተግባር
ያሳተምኩት፡፡ ትዝታዬ ነው፡፡ አሁን ባለኝ አቅም ለማስተካከል ያልደፈርኩት ጣዕምና ለዛውን እንዳላሳጣው በማለት ነው፡፡
በአዲሱ “ተከርቸም” መፅሃፍህ መግቢያ ላይ በመገበያያ ሳንቲሞች ላይ የሠፈረውን የቁጥርና የአሃዝ መለያየት ያቀረብክበት መንገድ በጣም አስገርሞኛል፤ ነገር ግን “ሺህ” በሚለው ቁጥራችን ላይ ከማስረጃ ይልቅ ይሆናል ብለህ ያመንክበትን የተቀበልክ ነው የመሠለው፤ የተሻለ ማረጋገጫ ልትሠጠን ትችላለህ? እግረ መንገድህን
የራሳችን በሆኑ ፊደላትና ቁጥሮች ላይ ያለህ አመለካከት ምን ይመስላል?
ክብረ ሙላቱ (ከአዴት)
ይስማዕከ፡- እልፍ በምንለው ቁጥር ላይ ያሉትን መወዛገቦች አስቀምጫለሁ፡፡ በተቻለኝ መጠን ከጥንት ጀምሮ በቀረቡ ፅሁፎች ላይ ያሉትን የአተረጓጐም ህፀፆችን ተንትኛለሁ፡፡ ለእኔ በቂ ማስረጃ ነው፡፡ ይሆናል ብዬ ብቀበል ያን ሁሉ ማስረጃ ማቅረብ አይጠበቅብኝም ነበር፡፡ ጥናታዊ ፅሁፍ ባለመሆኑ ያላካተትኳቸው አያሌ ማረጋገጫዎች አሉ፡፡ ግን ለማሳመን በቂ የሆኑትን አቅርቤያለሁ፡፡ በሌላ ጊዜ በጥናት መልክ ስለቁጥሮቻችንና ስለፊደሎቻችን ምስጢር ለማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ ፊደሎቻችንና ቁጥሮቻችን በዘፈቀደ የተቀመጡ አይደሉም፡፡
ዕንቁ፡- በመጨረሻ ለአንባቢዎች ምን መልዕክት ታስተላልፋለህ?
ይስማዕከ፡- ይህን እድል ስላገኘሁ አመሰግናለሁ፡፡ አንባቢዎቼ የሁለቱም ትውልድ አባላት ስለሆኑ ለየብቻ ባመሰግናቸውና በመጨረሻም ሁለቱንም እኩል ባመሰግን እመርጣለሁ፡፡ ለዚያኛው ትውልድ አንባቢዎቼ! የእናንተን መከራም ሆነ ፍስሃ ያልቀመሰ የዚህ ትውልድ አባል የሆነውን ሰው ሥራ አንብባችሁ ከዚህ ትውልድ ጋር በመጨባበጣችሁ አመስግናችኋለሁ፡፡ ፀጋውንና እድሜውን ያብዛላችሁ፡፡ ይህኛውን ትውልድ ከመናቅ መነቅነቅ ይበጃል ብላችሁ እውቀታችሁን በመጽሐፍ መልክም ሆነ በሌላ መንገድ ለማካፈል ለሞከራችሁት ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡ የዚህኛው ትውልድ አንባቢዎቼ ሆይ የዘመኑ ግርግር ሳይበግራችሁ በአባቶቻችን ልብ ውስጥ እና በአያቶቻችን ባድማ ተቀብሮ የቀረውን እውቀትና ፍልስፍና ፍለጋ የአቅሜን ደክሜ ያበረከትኳቸውን መፃህፍት ስላነበባችሁልኝ ምስጋናዬ የላቀ ነው፡፡ ተባረኩ! አሜን በሉ፤ የልጅ ምርቃት ይደርሳል፡፡ ዕንቁ፡- አሜን፤ እናመሰግናለን፡፡