ዶ/ር ዐቢይ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆነው ከተመረጡ ጀምሮ ከሕወሓት የታየው ፌዴራል መንግሥት ላይ የማያቋርጥ ትንኮሳና አመጽ እንደሆነ ይታወቃል። የትንኮሳውና የእምቢተኝነት ዓላማ በቂ የፖለቲካ አለመረጋጋት በመቀስቀስ ሕወሓትን ወደ ቀድሞው የበላይ ሥልጣን ለመመለስ እንደሆነ ብዙ የፖለቲካ ታዛቢዎችና ተዋናዮች ያምናሉ። ነገር ግን እነዚህ አድራጎቶች ወደ ሙሉ ወታደራዊ ግጭት ይቀየራሉ ብለው በእውነት ያሰቡ ካሉም በጣም ጥቂት ነበሩ። ለዚህም ማስረጃ የሚሆነው የሰላምና የእርቅ ጥሪዎችና ሙከራዎች፣ በተደጋጋሚ ቢከሽፉም፣ ከተለያዩ አካባቢዎች መሰማት መቀጠላቸው ነው። ብዙዎች ግጭቱ በሰላም ይጠናቀቃል ብለው ያመኑት ፌዴራል መንግሥቱም ሆነ ሕወሓት በግድየለሽነት ተጠምደው ጦርነት እስከ መቀስቀስ አይሄዱም ብለው ስለገመቱ ነው። በእነሱ ግምት የጦርነት መቀስቅስ መጨረሻ ውጤት አገሪቷን ከማውደም አልፎ ፍጻሜዋንም ሊያስከትል ይችላል፤ ይህ ደግሞ ማንንም አይጠቅምም።
እነዚህ ሊደርሱ የሚችሉ አስከፊ ክትያዎች ጦርነት ከመቀስቀስ ወያኔን አልገቱትም። ግጭቱ በሰላም እንዲያልቅ የተመኙት ሰዎች የዘነጉት ነገር ቢኖር ወያኔ በወታደራዊ ችሎታው በጣም ስለሚተማመን ጦርነት ከመጀመር ወደኋላ እንደማይል ነው። ምክንያቱም ጦርነቱ ፈጣን በሆነና በማያሻማ መንገድና፣ በአነስተኛ ሰባዊና ቁሳዊ ጥፋት ያልቃልና። እዚህ ላይ መጨመር ያለበት ለትንኮሳዎቹ የፌዴራል መንግሥቱ የሰጣቸው የተለሳለሱ መልሶች የሚያመለክቱት የውስጥ ድክመቱንና ምንኛ የወያኔን ወታደራዊ ኃይል እንደሚፈራ ነው።
የኢትዮጵያ ፈጣን ድል
የሆነው ግን ያልተጠበቀው ነው። የታሰበውን ፈጣንና ግልጽ ድል የተጎናጸፈው የፌዴራል መንግሥቱ ሆኖ ተገኘ። የኢትዮጵያ ጦር ኃይሎች በአንድ ብዛት ያለው፣ በደንብ የታጠቀና የመሸገ አማጺ ኃይል ላይ ያገኙት ድል በሙያቸው የደረሱበትን ከፍተኛ ደረጃና በዘመናዊ ወታደራዊ ቴክኖሎጂ የመጠቀም ብቃታቸውን ያረጋገጣል። እንዲሁም ሥለ ኢትዮጵያ አንድነት ያላቸውን ቆራጥ አቋም ያሳውቃል። በተጨማሪም የአማራ ልዩ ኃይል ከመጀመሪያው በጦርነቱ መሳተፍ ለተገኘው ውጤት ታላቅ አስተዋጽኦ ማድረጉ የሚካድ አይደለም። ለዚህም ነው ከሽንፈት አልፎ ጦርነቱ ወደ ፈጣን ሽሽት የተቀየረው። ፌዴራል መንግሥቱ ላደረጋቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችም አስፈላጊውን እውቅና መስጠት አለብን። ምንም እንኳን የሱዳን መንግስትን በተመለከተ ውጤት ባይገኝም፣ ኤርትራ ለኢትዮጵያ ያላት በጎ አመለካክት ባይኖር ኖሮ የጦርነቱ አካሄድ ይበልጥ አስቸጋሪ በሆነ ነበር።
የፌዴራል መንግሥቱ ወታደራዊ በላይነት ምንም የማያሻማ ቢሆንም ድሉ የወያኔን ፍጻሜ ያበስራል ብዬ ለመናገር አልደፍርም። ከድሉ በኋላ ኢትዮጵያ ድህረ ወያኔ ዘመን ውስጥ ትገኛለች ለማለትም አልፈልግም። ለዚህም አንዱ ምክንያት ወያኔ ወደ ሽምቅ ውጊያ ተመልሶ ሊገባ መቻሉ ሲሆን፣ ይህ ደግሞ ለፌዴራል መንግሥቱ የማያቋርጥ ፈተና ሊሆን ይችላል። እርግጥ ነው፥ ስኬታማ ሊሆን የሚችለው የትግራይ ሕዝብንና የጎረቤት አገሮች ድጋፍ ሲያገኝ ነው። አሁን እንደሚታየው ከሆነ ድጋፉ የተረጋገጠ አይደለም። በተጨማሪም ስኬታማነቱን የሚወስነው የድህረ ጦርነቱን ሁኔታ በተመለከተ ዶ/ር ዐቢይ በትግራይና በቀረው ኢትዮጵያ በሚያሳዩት ብስለትና ጥብቅነት ነው።
የግጭቱ ፍጻሜ ኢትዮጵያ አዲስ፣ ድህረ ወያኔ ዘመን ውስጥ ገብታለች ብሎ መናገር የማይቻልበት ሌላው ከባዱ ምክንያት፣ ወታደራዊ ሽንፈት የወያኔን ፖለቲካዊና ርዮተዓለማዊ ውድቀት በግድ የሚያስከትል ባለመሆኑ ነው። አሁን ያሉት ገዢ ልሂቃን የወያኔን ፖለቲካዊ መዋቅርና አስተሳሰብ እስተከተሉ ደረስ፣ እውነታው የበፊቱን ቀጣይ እንጂ አዲስ ሥርዓት አይሆንም።
ያጭር ጊዜ ክትያዎች
የማህበረሰብ ለውጥ አካሄዶችን ለመተንበይ መሞከር ያለው አደጋ እንደተጠበቀ ሆኖ ለአጭሩ ጊዜ የሚከተለውን ማለት ይቻላል። አንድ፣ የወያኔ መሸነፍ የፌዴራል መንግሥቱንና የገዢውን ፓርቲ ፖለቲካዊ ክብደት ያጠናክራል፤ ይህ ደግሞ መጪው ብሄራዊ ምርጫ ላይ ተጽዕኖ ይኖረዋል። በተለይም የዶ/ር ዐቢይን ሥልጣንንና ቅቡልነት ከፍ በማድረግ እቅዳቸውን ለማስፈጸም ያስችላቸውል። ሁለት፣ ወያኔ ፌዴራል መንግሥቱ ላይ የነበረውን የመጫንና እቅድን የማወክ ኃይል ስላጣ የሌሎች እንደ ኦነግ የመሳሰሉት የዘውግ ብሄረተኝነትን የሚያራምዱ እንቅስቃሴዎች መዳከምን ያስከትላል። ካለ ወያኔ የገንዘብ፣ ወታደራዊና ፖለቲካዊ ድጋፍ የእነዚህ እንቅስቃሴዎች ለፌዴራል መንግሥቱ አስጊ የመሆን ኃይላቸው መመንመኑ አይቀርም።
ሊሆኑ የሚችሉ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ክትያዎች
የመካከለኛና የረጅም ጊዜ ክትያዎች ስል አይቀሬ ወይም በቅድሚያ የተወሰኑ ውጤቶች ማለቴ አይደለም። የሚሆነው በብዙ የሚወሰነው ሕዝቦችና ተጽዕኖ አድራጊ ልሂቃን በሚያደርጓቸው ምርጫዎች ነው፣ በተለይም የድህረ ጦርነት ሁኔታውን በተመለከተ። ክትያዎች ሊሆኑ የሚችሉ አቅጣጫዎች ብቻ ስለሆኑ እውን የሚሆኑት በእርግጥ በሚደረጉ ምርጫዎች ነው።
አንድ ሊደርስ የሚችል ክትያ የፌዴራል መንግሥቱ ወደ ሥልጣን አጥባቂነት ማዘንበል ሊሆን ይችላል። የዶ/ር ዐቢይ ድል አድራጊነት የዴሞክራሲያዊ ለውጦችን ተስፋ በማጨለም ሥልጣንን በሙሉ የመያዝ ፍላጎት መፍጠሩ የማይቀር ነው። ወደ መንግሥታዊ ሥልጣን አጥባቂነት ማዘንበሉ መልካም አማራጭ ነው በሎ መከራከርም ይቻላል። በአገሪቱ ውስጥ የሚታዩትን በርካታ አጥፊ ኃይሎች ለመርታት አንዱ መፍትሔ የማዕከላዊ መንግሥትን ሥልጣን ማጎልበት ሊሆን ይችላል። በመሆኑም የሚቀርበው ጥያቄ ግልጽ ነው፣ ዶ/ር ዐቢይ የሚከተሉት አቅጣጫ የትኛው ሊሆን ይችላል?
ሁለተኛው እውን ሊሆን የሚችለው አቅጣጫ በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ የሚታዩት የዘውግ ብሔረተኝነት ዝንባሌዎች ገንፍለው የመውጣት ሁኔታ ነው። ከኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ታሪክ አንጻር ሲታይ ይህ ሂደት የሚጠበቅ ነው። ኢትዮጵያ ውስጥ አንድ ችግር ሲፈታ ወዲያው የተደበቀው ችግር አፍጦ ይወጣል። ለማስታወስ ያህል፣ የንጉሥ ኃይለሥላሴ መወገድ ያስከተለው የደርግን አምባገነን መንግሥት ነው፤ በተራው የደርግ ውድቀት ያመጣው የወያኔን አምባገነንነትና የዘውግ ፌዴራሊዝም ነው። ከወያኔ ውድቀት በኋላስ ምን መቅሠፍት ሊከሰት ይችላል?
አንድ ሊከሰት የሚችል ችግር በኦሮሞ ብልጽግና ውስጥ የሚታየው የበላይነት ፍለጋ አፍጦ የመውጣት ጉዳይ ነው። ከቅርብ ሲታይ የወያኔ ወታደርዊ ሽንፈት የፌዴራል መንግሥቱን ለመቆጣጠር በሚደረገው ፉክክር ውስጥ የአንድ ተቀናቃኝ መወገድ አይደለምን? በገዢው ፓርቲ ውስጥ በኢትዮጵያ የኦሮሞን የበላይነት ለማምጣት ለሚታገሉ ሁሉ ወያኔ አንድ ተቀናቃኝ ነበር። እንዲሁም ሌሎች የዘውግ ብሔረተኝነትን የሚያራምድ ሁሉ እንደ ኦነግና እንደ የፖለቲካ አራማጁ ጃዋር መሐመድ የሚመደቡት ተፎካካሪዎች ውስጥ ነው። ልዩነቱ፣ በነበረው ወታደራዊ ኃይልና የትግራይን ክልል ሙሉ ቁጥጥር ሕወሓትን ማስወገድ በጣም አስቸጋሪ ነበር። አሁን ግን ይህ የመጨረሻ እንቅፋት በመነሳቱ ለኦሮሞ የበላይነት የሚደረገው ግፊት ተጠናክሮ መቀጠል ይችላል።
አንድ የማይካድ ሃቅ የገዢው ፓርቲ ኦሮሞ ክፍለ አካል ውስጥ የበላይነት ምኞት መኖሩ ነው። በተለያየ መንገድ ይገለጻል። የአዲስ አበባን ከተማ በኦሮሚያ ውስጥ የማጠቃለል ፍላጎት አንዱ ማስረጃ ነው። የኦሮሚያ ፕሬዚደንት ሺመልስ አብዲሳ የፓርቲያቸው ግልጽ ዓላማ የበላይነትን ማግኘት እንደሆነ በይፋ ማመናቸው ሌላው ማስረጃ ነው። የበላይነት ፍላጎትን የሚገልጸው ሌላ ምልክት የአማራን ማንሰራራት ያስከትላል ተብሎ የሚገመተውን ሁሉ የመቃወም አባዜ ነው። ለምሳሌ የኦሮሞ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ ባለ ሥልጣን የሆኑት ታዬ ደንደአ በወያኔ በኃይል የተነጠቁትን የአማራ መሬቶችን የማስመለስ ጥያቄን “የመስፋፋት” ጥያቄ ነው ከማለት አልተቆጠቡም። የበላይነት እቅድ ሲኖር ብቻ ነው ጥያቄው መስፋፋት ነው ሊባል የሚችለው። እንዲሁም የዘውግ ፌዴራሊዝም ለማሻሻል የሚቀርበውን ማንኛውንም ሃሳብ በአሃዳዊ መንግስት አማካይነት የአማራን የበላይነት የመመለስ ጥረት ነው በሎ እንዳለ መጣል ሌላው ማረጋገጫ ነው።
ኢትዮጵያ ወዴት?
ከላይ እንደተገለጸው እነዚህ ሊደርሱ የሚችሉ አቅጣጫዎች እውን የመሆን ጉዳይ የሚወሰነው በአንድ መንስኤ ነው፤ እሱም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ምርጫዎች ነው። የወታደራዊው ድል ወደ ሥልጣን አጥባቂነት የማምራቱን አዝማሚያ ልናውቅ የምንችለው ዶ/ር ዐቢይ በአሸናፊነት ያደሱትን ሥልጣንና ቅቡልነት እንዴት እንደሚይዙት ስናይ ነው። እንዲሁም በገዢ ፓርቲ ውስጥ ያለውን የኦሮሞ የበላይነት አዝማሚያ የማዳከምና ነቅሎ የማውጣት ሥራ የሚያርፈው በዶ/ር ዐቢይ ትከሻ ላይ ነው።
ዶ/ር ዐቢይ ላይ ከባድ የኦሮሞ ልሂቃንን ጫና ስለሚያሳድር ሥራው እጅግ አስቸጋሪ እንደሚሆን አምናለሁ። ሥልጣን የማጥበቅ አማራጭ የኦሮሞ ልሂቃንን የበላይነት ዝንባሌ ለማቆምና የአገሩን አንድነት ለመጠበቅ አስፈላጊ መንገድ ሊሆን ይችላል እስከ ማለት ድረስም እሄዳለሁ። አንድ ነገር ግን ግልጽ ነው፥ ዶ/ር ዐቢይ መወሰን ያለባቸው ደረጃ ላይ አሁን ነገሮች ደርሰዋል። ወይ ማንኛውም የበላይነት ምኞት፣ ከየትኛው የገዢው ፓርቲ ክፍለ አካል ይምጣ፣ ለመንቀል ቆራጥ እርምጃ ይወስዳሉ ወይም ወያኔ በተከተለው መንገድ በመሄድ ስህተቶቹን መልሰው ይደግማሉ። የመጀመሪያው ምርጫ በከባድ ችግሮች አለበት። ቢሆንም ለሰላምና ለብልጽግና አስፈላጊ የሆኑትን የተጀመሩ ለውጦች ለመቀጠልና ጥልቀት ለመስጠት አንድ አገር ገንቢ መሪ መከተል ያለበት የኢትዮጵያን አንድነት መንገድ ነው። ብዙ ጊዜ እንዳልኩት፣ ያለው ሕገ መንግሥት፣ አንዳንድ አስፈላጊ እርምቶች ከተደረጉበት፣ ያቋቋማቸው ዘውጋዊ ክልሎች የአገሪቱን አንድነት አይጻረርም። ግልጽ መሆን ያለበት ግን አንድነቱ ከበላይነት ክጀላዎች ጋራ አብሮ እንደማይሄድ ነው። ከየትም መጣ የአንድ ዘውግ በላይነት ሰፊና ደም የሚያስፈስሱ ግጭቶች ውስጥ ኢትዮጵያን የሚነክር መሆኑ የማይካድ ነው። ግጭቶች ሁለቱን ዋና ዘውጎች፣ ማለት አማራንና ኦሮሞን፣ ካካተቱ የኢትዮጵያ መበታተን የማይቀር ይሆናል። የበላይነትን የሚከላከል ሥርዐት ከተቀመጠ ግን የሰላምንና የብልጽግናን መንገድ ይከፍታል። ምክንያቱም ዘውጋዊ ግጭቶች ባይቆሙም ትግሉ አክራሪ አናሳ ቡድኖችን ከመግታትና ከማሸነፍ ስለማያልፍ አስጊ የሆኑት የዋና ዘውጎች ግጭቶችን ያስቀራል።