የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ባደረገው የይዘት ክትትልና የኢንስፔክሽን ምልከታ ጄኤፍኤም 106.7 የብሮድካስት አዋጅ ቁጥር 1238/2013 እና የፈቃድ ውል ስምምነቱን አልጠበቀም ሲል አስታውቋል።
ጣቢያው 60% የሚሆነውን ስርጭት ለፈቃድ አካባቢው የማዋል፣ ህዝብን የሚያስተምሩና የሚያዝናኑ ፕሮግራሞችን የማቅረብ፣ እንዲሁም ሀገራዊ እና ህገ-መንግስታዊ እሴቶችን የማጠናከር ግዴታዎቹን አልተወጣም ተብሏል።
ባለሥልጣኑ በተደጋጋሚ የቃልና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም መሻሻል ባለመታየቱ እርምጃው ሊወሰድበት ችሏል።
በዚህም መሠረት የሬዲዮ ጣቢያው ከተሰጡት ማስጠንቀቂያዎች በኋላ አስፈላጊዎቹን ግዴታዎች ሙሉ ለሙሉ አሟልቶ እስኪገኝ ድረስ ከረቡዕ ሐምሌ 01 ቀን ጀምሮ ለቀጣዮቹ 6 ወራት ከስርጭት ሙሉ በሙሉ ታግዷል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ ኮሚዩኒኬሽን ባለሥልጣንም ለጄኤፍኤም የተመደበው 106.7 የሬድዮ ሞገድ እግድ ፀንቶ እስከሚቆይበት ጊዜ ድረስ ፍሪኩዌንሲውን ጥቅም ላይ ማዋል እንደማይቻል ለጣቢያው ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡
