Home ምጣኔ ሀብት ገበያ መር የውጪ ምንዛሬ እና የመንግሥት እርምጃዎች በክቡርገና

ገበያ መር የውጪ ምንዛሬ እና የመንግሥት እርምጃዎች በክቡርገና

ገበያ መር የውጪ ምንዛሬ እና የመንግሥት እርምጃዎች በክቡርገና

በርካቶች መንግሥት በቅርቡ ተግባራዊ ያደረገውን የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ ተከትሎ፣ የፖሊሲውን ተጽዕኖዎች እና ውጤቶች አስመልክቶ ከሚሰጡ ሙያዊ ትንታኔዎች እና አስተያየቶች መነሻነት በሚከተሉት ሦስት ማዕቀፎች ውስጥ ሊካተቱ የሚችሉ ጥያቄዎችን ያነሳሉ፡፡ ጥያቄዎቹም የሚከተሉት ናቸው፡-

1. ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተግባራዊ አድርገው ያልተሳካላቸው ሃገራት በምን ምክንያት አልተሳካላቸውም?

2. አሉታዊ ተፅዕኖውን ለመግታት ወይም ለመቀነስ መንግስት እወስዳቸዋለሁ ያላቸው ተያያዥ የፓሊሲ እርምጃዎች እንደ የነዳጅ ድጎማ፣ የደምወዝ ጭማሪ፣ የካፒታል ገበያ ስርዓት መክፈት እና ሌሎች እርምጃዎች በእነኚህ ሃገራትም ተወስደው ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም?

3. የመንግስት የውጭ ምንዛሬ ክምችት የተሟጠጠ ወይም አነስተኛ ከመሆኑ አንፃር፣ መስረታዊ ምርቶች ግብይትን ብቻ የሚመለከት በብሄራዊ ባንክ የሚወሰን አነስተኛ የምንዛሬ ተመን ስርዓትን ለማሳካት መንግስት የገንዘብም ሆነ የፖሊሲ የማስፈፀም አቅም አለው ወይ? የሚሉ ናቸው፡፡

ለእነዚህ ጥያቄዎች እንደሚከተለው ማብራሪያ ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡

***

በአለም ላይ በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአት ተግባራዊ ከአደረጉ በኋላ ያልተሳካላቸው ጥቂት የማይባሉ ሀገሮች አሉ፡፡ ላለመሳካቱ በርካታ ምክንያቶችን መጥቀስ ቢቻልም የሚከተሉት ግን ዋና ዋናዎቹ ናቸው፡፡

የምንዛሪ ተመን መዋዠቅ፡- በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአት የምንዛሪ ዋጋ የሚወሰነው በመንግስት ሳይሆን እንደ አቅርቦትና ፍላጎት ባሉ የገበያ ሀይሎች ነው፡፡ ይህ ሁኔታ በተለይ እንደ ሸቀጦች ዋጋና የካፒታል ኩብለላ ባሉ ውጪያዊ ሀይሎች ተጽዕኖ ስር ለወደቀ ሀገር ኢኮኖሚ ሊተነበይ የማይችል የምንዛሪ ዋጋ መዋዠቅ ያስከትላል፡፡

ሊተነበይ የማይችል የምንዛሪ ዋጋ መዋዘቅ የወደፊት እቅድን አስቸጋሪ በማድረግ በንግድ ስራዎችና በኢንቨስትመንት ላይ ተጽእኖ ያሳድራል፡፡ ያልተረጋጋና ክፉኛ የሚዋዥቅ የምንዛሪ ዋጋ ለአስመጪና ላኪዎች ትርፍና ኪሳራቸውን ለማስላት አዳጋች ስለሚሆንባቸው ንግድና  ኢንቨስትመንትን ያውካል፡፡

በውጭ ሀይሎች ተጽዕኖ ስር መውደቅ፡- እንደ ግብርና ምርቶች፣ እሴት ያልተጨመረባቸው የማእድን ውጤቶችን፣ ያልተጣራ ድፍድፍ ዘይት የመሳሰሉትን ጥሬ ምርቶች ብቻ ወደ ውጭ በመላክ  ላይ ኢኮኖሚያቸው የተመሰረተ ሀገሮች በአለም አቀፍ ደረጃ በሚከሰተው የዋጋ ለውጥ የውጭ ምንዛሪያቸው ክፉኛ ይዋዥቃል፡፡ እነዚህ ሀገራት በተለይም የተወሰኑ ምርቶችን በመላክ ብቻ ጥገኛ ከሆኑና የተለያዩ ምርቶችን መላክ ካልቻሉ የኢኮኖሚያዊ መናጋት ይገጥማቸዋል፡፡

በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአት ለአለም አቀፍ የካፒታል ሽሽት የተጋለጠ ነው፡፡ ለምሳሌ በአለም አቀፍ ደረጃ አለመረጋጋት ሲፈጠር ኢንቨስተሮች ካፒታላቸውን ችግር ከተፈጠረበት ሀገር ወይም ቀጠና ወደ ሌሎች ሀገሮች ሲያሸሹ ችግሩ በተከሰተባቸው ሀገሮች ከፍተኛ የዋጋ ግሽበት ከማስከተሉም በላይ ኢኮኖሚያዊ ቀውስም ሊያስከትል ይችላል፡፡

የዋጋ ንረት ጫና፡- የአንድ ሀገር ገንዘብ የምንዛሪ ተመን በገበያ ላይ በተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአት ምክንያት ሲዳከም ወደ ሀገር ውስጥ የሚገቡ ምርች ዋጋ ይጨምራል፡፡ ይህም በሸቀጥ ምርቶች ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ስለሚያስከትል የዋጋ ንረትን ያስከትላል፡፡ አንዲት ሀገር በከፍተኛ ሁኔታ የገቢ ምርቶች ጥገኛ ከሆነች ይህ የዋጋ ንረት ጫና ኢኮኖሚውን ለማረጋጋ የሚደረገውን ጥረት አዳጋችና ከባድ ያደርገዋል፡፡

የፖሊሲ አማራጮችን መጠቀም አለመቻል፡- በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአት እንደ ውስን የውጭ ምንዛሪ ተመን በብሄራዊ ባንክ አማካኝነት በቀጥታ ጣልቃ በመግባት የውጭ ምንዛሪውን ማረጋጋት አይችልም፡፡ ብሄራዊ ባንኮች እንደ የወለድ ተመን ማስተካካያዎች ባሉ የገንዘብ ፖሊሲዎች በውጭ ምንዛሪ ተመን ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ፡፡ በርግጥ ተጽዕኖዎቹ እንደ የሀገር ውስጥ ብድር ወጪዎች ባሉት ላይ ጫና በመፍጠር በአጠቃላይ ኢኮኖሚው ላይ ተጽዕኖ ያሳርፋል፡፡

ግምታዊ ትንበያና ቡድናዊ ባህሪ፡- በነጻ የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአት ኢንቨስተሮች ባላቸው ቡድናወዊ ባህሪ የምንዛሪ ዋጋን በተመለከተ ግምታዊ ትንበያን ተግባራዊ ስለመሚያደርጉ የውጭ ምንዛሪ ተመኑ በግምታዊ ተጽዕኖ ስር ስለሚወድቅ የገንዘብ ዋጋ በፍጥነት ይዳከማል፡፡ በተለይም ሀገሪቱ በቂ የውጭ ምንዛሪ ክምችት እጥረት ካለባት ወይም በጠንካራ የኢኮኖሚ መሰረት ላይ ካልቆመች ይህ ግምታዊ ትንበያ የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ሊያናጋ ይችላል፡፡

ሌላው የኢንቨስተሮች ቡድናዊ ባህሪ የሚገለጸው በአለም አቀፍ ደረጃ ከሚከሰት ኩነት ጋር የተያያዘ ሲሆን ይህም ድንገተኛ የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ እንዲፈጠር ያደርጋል፡፡ ለምሳሌ በአንድ ሀገር ወይም የአለማችን ክፍል የሚፈጠር ኢኮኖሚያዊም ሆነ ፖለቲካዊ ቀውስ ወደ ሌሎች አካባቢዎችም የመዛመት ባህሪ ስላለው ኢንቨስተሮች ቀውስ በተፈጠረ ቁጥር ሀብት የማሸሽ ባህሪ ስላላቸው ባለሀብቶች ኢንቨስት ካደረጉበት ወደ ውጭ ካፒታል ያሸሻሉ፡፡

ደካማ ኢኮኖሚያዊ መዋቅር፡- ከፍተኛ የእዳ ጫና የሚያናጥርባቸው፣ የተመናመነ የውጭ ምንዛሪ ክምችት ያላቸው፣ ወስን ሸቀጦች ብቻ ወደ ውጭ የሚልኩና በአጠቃላይ ደካማ የኢኮኖሚ መዋቅር ያላቸው ሀገሮች ነጻ የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአት ይበልጥ ለአደጋ ያጋልጣቸዋል፡፡ ደካማ ኢኮኖሚ ላላቸው ሀገሮች የውጭ ምንዛሪ ተመን መዋዠቅ ያለባቸውን ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ይበልጥ ከማባባሱም በላይ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የሚደረገውን ጥረት የዳገት ሩጫ ያደርገዋል፡፡

የፌስ ቡክ ተከታዬን “ገበያ መር የውጭ ምንዛሬ ተግባራዊ አድርገው ያልተሳካላቸው ሃገራት በምን ምክንያት አልተሳካላቸውም?” ለሚለው ጥያቄ ማጠቃለያ ለመስጠት ያህል በገበያ ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአት ስኬት ስርአቱን ተግባራዊ በሚያደርጉ ሀገሮች ኢኮኖሚያዊ አቋምና ጥንካሬ ይወሰናል ማለት ይቻላል፡፡ በተለይም ሀገራቱ ተግባራዊ በሚያደርጉት የገንዘብ ፖሊሲና ለውጫዊ ጫና በሚሰጡት ምላሽ ውጤታማነት የስርአቱ ስኬት ይወሰናል፡፡ በተግባር እንደታየው ግን ውስን ምርቶችን ብቻ ወደ ውጭ የሚልኩ፣ ደካማ መዋቅራዊና ኢኮኖሚያዊ አቋም ያለቸው ሀገሮች ከነጻ የውጭ ምንዛሪ ተመን ጋር ተያይዞ የሚመጣው የምንዛሪ ዋጋ ተመን መዋዠቅና ግምታዊ ትንበያ ኢኮኖሚያቸው እንዳይረጋጋ ፈተና ሆኖባቸው ተስተውሏል፡፡

***

መንግስታት ከውስን የውጭ ምንዛሪ ተመን ወደ በገበያ የሚመራ የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአት  ሽግግር ሲያደርጉ ለውጡ የሚያመጣውን ጫና ለመቀነስና ሽግግሩ ቀና እንዲሆን የተለያዩ እርምጃዎችን ይወስዳሉ፡፡ የኢትዮጵያ መንግስትም የውጭ ምንዛሪ ለውጡን ተከትሎ ተግባራዊ አደርጋቸዋለሁ ያለው እንደ የነዳጅ ድጎማ፣ የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ጭማሪና የአክሲዮን ገበያን የማጠናከር እርምጃዎች ለውጡ የሚያስከትለውን ጫና ለመቀነስና ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት ታሳቢ የተደረጉ ናቸው፡፡ ሆኖም ግን የእነዚህ ከላይ ተጠቀሱት እርምጃዎች ውጤታማነት የሚወሰነው የሀገሪቱን ተጨባጭ ሁኔታ ያገናዘቡ ሌሎች በርካታ ወሳኝ ሁኔታዎች ተግባራዊ ሲደረጉ ጭምር ነው፡፡ 

መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ሽግግር ምሳሌዎች

• የበጀት አስተዳደር፡- በመንግስት ወጪዎች ላይ ጥብቅ ቁጥጥር ማድረግና የበጀት ጉድለትን መቀነስ

• የገንዘብ ፖሊሲ ውጤታማነት፡- የዋጋ ንረትን በመቆጣጠርና የወለድ መጠንን በአግባቡ በመምራት የብሄራዊ ባንክን ሚና ማጠናከር

• መዋቅራዊ ማሻሻያ ፡- ምርታማነትንን ተወዳዳሪነትን ለማሻሻል እንደ ግብርና፣ አምራች እንዱስትሪና አገልግሎት ባሉ ዘርፎች ለውጦችን ተግባራዊ ማድረግ

• ውጫዊ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች፡- እንደ የሸቀጦች ዋጋ፣ የንግድ ፖሊሲና የካፒታል ኩብለላ ያሉ በአለም አቀፍ ደረጃ ተጽዕኖ የሚፈጥሩ መሰረታዊ ጉዳዮችን በአግባቡ መያዝና ማስዳደር

የምንዛሪ ለውጥ ስምምነቶች

• አላማ፡- የምንዛሪ ተመን ለውጥ ስምምነቶች የውጭ ምንዛሪ በማስገኘትና የልማት ድጋፍ በማድግ የውጭ ምንዛሪው ለአጭር ጊዜ እንዲረጋጋ ያስችላሉ፡፡

• ውጤታማ ምሳሌ፡- ቻይና የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ በማድረጓ ውጤታማ በሆነ መልኩ የውጭ ምንዛሪ ተመኗን ማረጋጋትና አለም አቀፍ የንግድ ግንኙነቷን ማቀላጠፍ ችላለች፡፡ ቻይና የውጭ ምንዛሪ ተመኗን በመለወጧና ከበርካታ ሀገራት ጋር ያላትን የውጭ ምንዛሪ ተመኗን በማስተካከሏ የአሜሪካ ዶላርን ተጽእኖ መቀነስ የቻለች ሲሆን በኢኮኖሚ ቀውስ ወቅትም የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዳይገጥማት አስችሏታል፡፡

• ያልተሳካ ምሳሌ፡- አርጀንቲና እ.ኤ.አ በ2000 ኢኮኖሚዋን ለማረጋጋት የምንዛሪ ተመን ለውጥ አደርጋ ነበር፡፡ ሆኖም ግን በተፈጠረው መጠነ ሰፊ የማክሮ ኢኮኖሚ ሚዛን መዛባትና በመንግስት ፖሊሲ ላይ እምነት ያለመኖር ለውጡን ውጤታማ እንዳይሆን አድርጎታል፡፡

የነዳጅ ድጎማን በተመለከተ

• አላማ፡- በውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጥ ወቅት የነዳጅ ድጎማ የዋጋ ንርትን በመቆጣጠርና የኑሮ ውድነትን በማለዘብ ሽግግሩ ፖለቲካዊ አለመረጋገትን እንዳስከትል ያግዛል፡፡

• ውጤታማ ምሳሌ፡- ኢንዶኔዢያ እ.ኤ.አ በ1998 የተፈጠረው ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ማህበራዊ አለመረጋጋትን እንዳይፈጥር በነዳጅ ምርቶች ላይ ድጎማ አድርጋ ችግሩን በጊዚያዊነት ማስወገድ ችላለች፡፡ ሆኖም ግን ድጎማውን በዘላቂነት ማስቀጠል ባለመቻሉ እንዲነሳ ተደርጓል፡፡

• ያልተሳካ ምሳሌ፡- ናይጄሪያ በነዳጅ ምርቶች ላይ ድጎማ ስታደርግ ቆይታለች፡፡ ሆኖም ግን ድጎማው የመንግስትን ገንዘብ ከማሟጠጡም በላይ ኢኮኖሚውንም ማረጋጋት ተስኖታል፡፡ ድጎማው ዘላቂ መፍትሄ ከማምጣት ይልቅ ጊዚያዊ ማስተንፈሻ ብቻ ሆኖ ዘልቋል፡፡

የመንግስት ሰራተኞች ደሞዝ ጭማሪን በተመለከተ

• አላማ፡- ለመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ ማድረግ የውጭ ምንዛሪ ተመን ለውጡ የሚያስከትለውን የዋጋ ንረት በማካካስ ማህበራዊ አለመረጋጋት እንዳፈጠር ያግዛል፡፡

• ውጤታማ ምሳሌ፡- እ.ኤ.አ በ2000 ጋና የደረገችውን መጠነ ሰፊ የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተከትሎ ለመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ አድርጋ ኢኮኖሚውን ማረጋጋትና የመንግስት ተቋማትን ምርታማነት ማሳደግ ችላለች፡፡ ሆኖም ግን የደሞዝ ጭማሪውን ዘላቂ ማድረግ ፈተና ሆኖባታል፡፡

• ያልተሳካ ምሳሌ፡- ቬንዚዌላ በሀገሪቱ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ለመቋቋም ለመንግስት ሰራተኞች የደሞዝ ጭማሪ አድርጋ ነበር፡፡ የደሞዝ ጭማሪው በመንግስት ላይ የበጀት ጉድለቱን በማስፋት የዋጋ ንረቱን ይበልጥ ያባበሰው ሲሆን የሀገሪቱ ገንዘብ የመግዛት አቅምም በፍጥነት እየተዳከመ ሊሄድ ችሏል፡፡

የአክሲዎን ገበያን ተግባራዊ ማድረግን በተመለከተ

• አላማ፡- የአክሲዎን ገበያን ተግባራዊ ማድረግ ኢንቨስትመንትን ይስባል፣ ኢኮኖሚውን ዘርፈ ብዙ ያደርገዋል አንዲሁም ለንግድ ስራዎች አማራጭ የፋይናስ ምንጭ እድሎችን ያስገኛል፡፡

• ውጤታማ ምሳሌ፡- ቬትናም እ.ኤ.አ በ2000 መጀመሪያ ላይ የኢኮኖሚ ማሸሻሻያ አካል አድርጋ የአክሲዎን ገበያን ተግባራዊ ያደረገች ሲሆን ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የፋይናንስ ስርአቷ አካል አድረጋ ቀጥላበት የውጭ ኢንቨስትመንት መሳብ ችላለች፡፡

• ያልተሳካ ምሳሌ፡- ዛምቢያ እ.ኤ.አ በ1990 ዎቹ የአክሲዮን ገበያ ተግባራዊ ብታደርግም አክሲዮኑ በኢንቨስተሮች ዘንድ እምነት የተነፈገው በመሆኑ፣ ደካማ የደንብና መመሪያ አተገባባር በመኖሩና ኢኮኖሚው ያልተረጋጋ በመሆኑ ኢንቨስትመንትን ለማቀላጠፍ ፈተና ሆኖባታል፡፡

ማጠቃለያ

የጠያቂያችንን ሁለተኛ ጥያቄ ማለትም “አሉታዊ ተፅዕኖውን ለመግታት ወይም ለመቀነስ መንግስት እወስዳቸዋለሁ ያላቸው ተያያዥ የፓሊሲ እርምጃዎች እንደ የነዳጅ ድጎማ፣ የደምወዝ ጭማሪ፣ የካፒታል ገበያ ስርዓት መክፈት እና ሌሎች እርምጃዎች በእነኚህ ሃገራትም ተወስደው ውጤታማ ሊሆኑ አልቻሉም?” ለሚለው የማጠቃላያ ማብራሪያ ለመስጠት ያህል  ውጤቱ በሚወሰደው እርምጃ አተገባበር ላይ የተመሰረተ መሆኑን ልገልጽ እወዳለሁ፡፡

ከውስን የውጭ ምንዛሪ ተመን ወደ በገበያ የሚወሰን የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአት ሽግግር ሲደረግ ሽግግሩን ልዝብ ለማድረግ የሚወሰዱት እንደ የነዳጅ ድጎማ፣ የደምወዝ ጭማሪ፣ የካፒታል ገበያ ስርዓት መክፈት እና ሌሎች እርምጃዎች ውጤታማ የሚሆኑት ከላይ በምሳሌነት የተጠቀሱትም አገሮች ልምድ የሚያሳየው መጠነ ሰፊ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻዎች ሲታከሉበትና መንግስት የፖሊሲ ውሳኔዎችን የማስፈጸም አቅምና ቁርጠኝነት ሲኖረው ነው፡፡ በገበያ የሚወሰን የውጭ ምንዛሪ ተመን ስርአት ተግባራዊ ማድረግ በብድርም ሆነ በእርዳታ የውጭ ምንዛሪ ሊያስገኝ ይችላል፤ ነገር ግን የኢኮኖሚ መዛባትን በዘላቂነት አይፈታም፡፡ የነዳጅ ድጎማ የዋጋ ንረትን በጊዚያዊነት ሊቆጣጠር ይችላል፤ ሆኖ ግን በመንግስት በጀት ላይ ከፍተኛ ጫና ይፈጥራል፡፡ ለመንግስት ሰራተኞች የሚደረገው የደሞዝ ጭማሪ ማህበራዊ አለመረጋጋትን ያስታግስ ይሆናል ይህ ሊሆን የሚችለው ግን የደሞዝ ጭማሪው ዘላቂ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ የአክሲዎን ገበያ ተግባራዊ መደረጉ ኢንቨስትመንትን ሊስብ ይችላል፤ ይህ የሚሳካው ግን በሀገሪቱ የተረጋጋ የማክሮ ኢኮኖሚ ምህዳር ሲኖር ነው፡፡