ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም መፈንቅለ መንግሥት ሙከራ የተደረገበት ቀን ሲታወስ

Date:

በሌተናል ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም አስተዳደር ላይ የተሞከረው “የጀኔራሎቹ መፈንቅለ መንግሥት” ሙከራ የተካሄደው ከዛሬ 36 ዓመታት በፊት (ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም) ነበር፡፡

በእርግጥ የመፈንቅለ መንግሥቱ ተግባረዊ ሙከራ የተደረገው በ1981 ዓ.ም ይሁን እንጂ የመፈንቅለ መንግሥት ሃሳቡ ከተወጠነ ቆይቷል፡፡ የድርጊቱ ጠንሳሽና ጀማሪ ከአየር ኃይል አዛዥነት ተሽረው የኢንዱስትሪ ሚኒስትር ሆነው የተሾሙት ሜጀር ጀኔራል ፋንታ በላይ ናቸው፡፡ ግንቦት 8 ቀን 1981 ዓ.ም ሊቀመንበር ሌ/ኮሎኔል መንግሥቱ ኃ/ማርያም ለጉብኝት ወደ ምስራቅ ጀርመን ሄዱ፡፡የዚችን እለት የመጨረሻ የአድማ ስብሰባ ለማድረግ የተመረጠው ቦታ በመከላከያ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ጊቢ ውስጥ የሚገኝና ከሚኒስትሩ ከሜጀር ጄኔራል ኃይለጊዮርጊስ ቢሮ አጠገብ ያለው አነስተኛ የመሰብሰቢያ ክፍል ነው:: በእለቱ ባልተለመደ ሁኔታ ይህ ግቢ የጄኔራሎች መጠራቀሚያ ሆኖ ታዬ፡: እድመኞቹም በቀጠሯቸው መሠረት አንድ በእንድ ወደዚያች ክፍል ገቡ፡፡ በስብሰባው ላይም የተገኙት:-

  1. ሜጀል መርዕድ ንጉሴ – የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም
  2. ሜ/ጄ/ል ኃይሉ ገብረሚካኤል – የምድር ጦር ዋና አዛዥ
  3. ሜ/ጄ/ል አምሃ ደስታ – የአየር ኃይል ዋና አዛዥ
  4. ሪር አድሚራል ተስፋዬ ብርሃኑ- የባህር ኃይል ዋና አዛዥ
  5. ሜ/ጀ/ል አለማየሁ ደስታ – የምድር ጦር ምክትል አዛዥ
  6. ሜ/ጄ/ል ወርቁ ዘውዴ – የፖሊስ ሠራዊት ጠቅላይ አዛዥ
  7. ሜ/ጄ/ል አብዱላሂ ዑመር የመከላካያ ሚ/ር አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ
  8. ሜ/ጄ/ል ፋንታ በላይ – የኢንደስትሪ ሚኒስትር
  9. ሜ/ጄ/ል አበራ አበበ የጦር ኃይሎች ምክትል ኤታማዦር ሹም
  10. ሜ/ጀ/ል ተስፋዬ ትርፌ የአብዮታዊ ዘመቻ መምሪያ ኃላፊ
  11. ብ/ጄ/ል ሰለሞን ጋሻው የአየር ኃይል ኤታማዦር ሹም
  12. ብ/ጄ/ል ደሣለኝ አበበ – የጦር ኃይሎች አካዳሚ አዛዥ
  13. ብጄል እርቅይሁን ባይሳ – የ67ኛው ኮር ዋና አዛዥ
  14. ብ/ጄ/ል ተስፋዬ ደስታ – የአየር ኃይል ዘመቻ መኮንን
  15. ብ/ጀ/ል ነጋሽ ወልደየስ የ608ኛው ኮር ዋና አዛዥ
  16. ብ/ጄ/ል እንግዳ ወልደኣምላክ – የ606ኛው ኮር ዋና አዛዥ
  17. ብ/ጄ/ል ገናናው መንግስቱ – የ6ኛው አየር ምድር አዛዥ
  18. ኮሞዶር ኃይሌ ወልደማርያም – የጦር ኃይሎች ዘመቻ መምሪያ ባልደረባ ናቸው፡፡በስብሰባው የተገኙት እነዚህ ብቻ ይሁኑ እንጂ ከየጦር ክፍሉ የተመለመሉ አዛዦችም የሚሰጣቸውን ትዕዛዝ ለመፈፀም ተዘጋጅተዋል፡፡

እነዚህ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ተሰብስበው የመጀመሪያ ውሣኔ ያደረጉት ሊቀመንበሩን ቀይ ባህር ሲደርሱ ፕሌኑን በሚሳኤል መምታትና ማሰናበት የሚል የነበረ ቢሆንም፤ ከመንግስቱ ውጪ የተሳፈሩ በርካታ ንፁሃን ስቪሎች ስላሉ እነሱንም አብሮ መግደል ተገቢ አይደለም የሚል ሀሳብ ስለተነሳ ውሣኔው ተሻረና፤ ከዚህ ይልቅ በወጡበት ማስቀረት እንደሚሻል ስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ ዋና ሰብሳቢው ሜጀር ጄኔራል ፋንታ በላይ ነበሩ፤ ነገር ግን ወደ ስብሰባው የመጡት ዘግይተው ነበርና የሰብሳቢነቱን ቦታ ማጀር ጄኔራል መርዕድ ንጉሴ ይዘውታል፡፡ ጄኔራል ፋንታ በላይ ወደ ስብሰባው ገብተው ሲያዩ ቦታው ተይዟል፡፡ ጄኔራል መርዕድ ዋና ሰብሳቢው ሲመጡ ቦታውን መልቀቅ ሲገባቸው ፀጥ አሉ፡፡ ቢታይ፣ ቢታይ መርዕድ ለፋንታ ሊለቁ ቀርቶ የመልቀቅ አዝማሚያም ሳያሳዩ ስብሰባውን መምራት ቀጠሉ፡፡ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ የተሰባሰቡት ጄኔራሎች እዚያው በዚያው ሌላ መፈንቅለ መንግስት አደረጉ፡: እናም በዚያች ጠባብ ቢሮ ኩዴታ የተከናወነባቸው ጄኔራል ፋንታ በላይ በሁኔታው ተበሳጭተው ስብሰባውን ጥለው ወጡና በር ላይ እጃቸውን ኪሳቸው ከተው መንጎራደድ ጀመሩ፡፡ይሁን እንጂ የደህንነት ሚኒስትሩ ኮሎኔል ተስፋዬ ወልደሥላሴ በሊቀ መንበሩ ሸኝት ላይ ሳይገኙ የቀሩ የጦር አዛዦች ሁኔታ ስላላማራቸው አዛዦቹን የሚከታተል ቡድን አደራጅተው ድርጊቱን ይከታተሉ ነበር፡፡

ጉዳዩ የመፈንቅለ መንግሥት አድማ መሆኑን ሲያረጋግጡም ነገሩን የሊቀ መንበሩ ቀኝ እጅ ለነበሩት ለሻለቃ መንግሥቱ ገመቹና ለሌተናል ጀኔራል ተስፋዬ ገብረ ኪዳን አሳወቋቸው፡፡ ታቅዶ የነበረው መፈንቅለ መንግሥትም ሳይሳካ ቀረ፡፡

🔹ምንጭ:-የኢትዮጵያ የ5ሺ ዓመት ታሪክ-መጽሐፍ 2-ካልተዘመረለት ልጅ ኢያሱ እስከተዘመረለት ኢህአዴግ (በፍስሃ ያዜ ካሣ)

Ethiopian History and Tourism/የኢትዮጵያ ታሪክና ቱሪዝም

ሁሉ አዲስ በብስራት ኤፍ.ኤም 101.1 እንዳዘጋጀዉ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከ989 ሚሊዮን ብር በላይ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የጉምሩክ ኮሚሽን ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3 ቀን 2018...

“እኔ እስካለሁ ድረስ ኢራን የኑክሌር መሣሪያ ባለቤት አትሆንም!”

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት ሰኔ 5 ቀን...

አገር እንዲህ ዓይንህን ለአፈር ይባላል?

በተጀመረው የአለም ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ በሜክሲኮ መሸነፏን ተከትሎ አፍሪካ...

አሜሪካ እና ኢራን የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት በ24 ሰዓት ውስጥ እንደሚፈራረሙ ፓኪስታን አስታወቀች

ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን በሰላም ድርድሩ ማዕቀፎች ላይ መስማማታቸውን...