በተረፈ ወርቁ (ዲ/ን)
እንደ መንደርደሪያ፤
የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ባሳለፍነው ሳምንት 22 ኛውን ‹የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባኤ› በስኬት አካሂዷል፡፡ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት- የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባኤ በተለያዩ ሀገራት ተካሂዷል፤
ለአብነትም፤ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባኤ እ.አ.አ. በ1959 በኢጣሊያ/ሮም ሲሆን የተካሄደው ከዛ በኋላም በ1963 በእንግሊዝ /ማንቸስትር ዩናይትድ፣ በፈረንሳይ/ፓሪስ፣ በአሜሪካ/ቺካጎ፣ በሩሲያ/ሞስኮ፣ በጃፓን/ኪዮቶ፣ በእስራኤል/ቴላቪቭ፣ በጀርመን/ሀምቡርግ፣ በፖላንድ/ዋርሶ… በተከታታይ ተካሂዷል፡፡
በሀገራችንም- አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፣ መቀሌ ዩኒቨርሲቲ፣ ድሬዳዋ ዩኒቨርሰቲ ዘንድሮ ደግሞ የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ 22 ኛውን የኢትዮጵያን ጥናት ዓለም አቀፍ ጉባኤ በስኬት አጠናቋል፡፡
የግእዝ ቋንቋ፡- በዓለም አቀፍ ደረጃ የኢትዮጵያ ጥናት መሠረት
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አባትና ሊቅ የነበሩት የአባ ጎርጎርዮስ ዘመካነ ሥላሴ እና የጀርመናዊውን ምሁርና አጥኚ ሂዮብ/ኢዮብ ሉዶልፍ ከ፬፻ ዓመታት ገደማ በፊት በ፲፯ኛው መቶ ክፍለ ዘመን በኢጣሊያዊቷ ጥንታዊትና ታሪካዊት ከተማ በሮም የተገናኙበት ልዩ የታሪክ አጋጣሚ በአውሮፓ ምድር ለኢትዮጵያ ጥናት ጅማሬ ትልቅ መሠረትን ጣለ፡፡
ኢትዮጵያ- ጎንደር/መካነ ሥላሴ፣ ኢጣሊያ- ሮም ከተማ፣ ከዚያም ጀርመን- ኑርምበርግ፡፡ እነዚህ አገሮች በ፲፯ኛው መቶ ክ/ዘ ተጠንስሶ እስከ ዛሬ ድረስ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለዘለቀው ኢትዮጵያ ጥናት መሠረት የኾኑ ሀገራት ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊው ሊቅ አባ ጎርጎርዮስ ዘመካነ ሥላሴ ወደ ኢጣሊያ ሮም ከተማ ማምራታቸው እውቀትን/ጥበብን ፍለጋ ከአገሩ ጀርመን ካመጣው ሂዮብ ሉዶልፍ ጋር በሮም ከተማ እንዲገናኙ ምክንያት ሆነ፡፡ እነዚህ የሁለት አገር ሊቃውንት ቋንቋዎቻቸውን፣ የየአገራቸውን ታሪክ፣ ባህልና ሃይማኖት እርስ በርሳቸው ተማማሩ፡፡
በቆይታቸውም አባ ጎርጎርዮስ ጀርመንኛን፣ ሉዶልፍ ደግሞ ግዕዝን በሚገባ ተካኑ፡፡ የእነዚህ የሁለት አገራት ሊቃውንት ይህ ግንኙነታቸው ውሎ አድሮ ደግሞ ሌላ ውጤትን አሰገኘ፡፡ ይኸውም ጀርመናዊው ሉዶልፍ ወደ አገሩ ተመልሶ በምድረ አውሮፓ የመጀመሪያውን የኢትዮጵያን ጥናት ለመመሥረት በቃ፡፡ ይኼ ግንኙነታቸው መሠረቱ ጠንካራ ስለነበር የኢትዮጵያ ጥናት ግንባታው ዘለቄታን አግኝቶ ይኸው እስከአሁን ዘመን ድረስ ዘልቋል፡፡
በዘመናችንም በአውሮፓ በሚገኙ ታላላቅ ዩኒቨርስቲዎችና አካዳሚያዎች የኢትዮጵያ ጥናት በዋና ትምህርት ክፍለ ደረጃ፣ ወይም በአፍሪካ ጥናት ሥር አሊያም ደግሞ በምሥራቅ አገሮች (Oriental Studies) ሥር ይሰጣል፡፡
በእርግጥ የኢትዮጵያ ጥናት በአውሮፓ ልደቱ ይበሰር እንጂ ስለ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ጂኦግራፊ፣ ገናና ሥልጣኔ፣ ሃይማኖት፣ ባህል፣ ቅርስ … ወዘተ ጥናት የተጀመረው በ፲፯ኛው ክ/ዘ ጀምሮ ነበር ብሎ መደምደም አይቻልም፡፡ ለዚህም ተጨባጭ መረጃዎችንና የታሪክ ድርሳናትን በዋቢነት መጥቀስ ይቻላል፡፡
ለአብነትም፤ አባ ጎርጎርዮስ ወደ ሮማ ምድር ከመምጣታቸው ከመቶ አምሳ ዓመታት ገደማ በፊት በ፲፭ኛው መቶ ክ/ዘ በኢየሩሳሌም ከሚገኘው ከዴር ሱልጣን ገዳምና ከኢትዮጵያ ተሰደው በሮማ ይኖሩ ከነበሩ ኢትዮጵያውያን መነኮሳት ዘንድ የግዕዝ ቋንቋን የተማሩና እንዲሁም በኢትዮጵያውያን ጥንታዊ ሃይማኖት፣ ታሪክና ባህል ከመገረማቸው የተነሣ ሰፊ ጥናት ያደረጉ አውሮጳውያን ምሁራን፣ የሃይማኖት ሊቃውንትና አሳሾች እንደነበሩ የታሪክ መዛግብት ይመስክራሉ፡፡
እ.አ.አ በ1960 ‹‹An Outline of the Development of Ethiopian Topography in Europe›› በሚል ርእስ ጥናታቸውን ያስነበቡት ሆላንዳዊው ምሁር ኤች. ኤፍ. ዊጂንማን (ዶ/ር) በአውሮፓ ምድር በመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ የግዕዝ ፊደላት በደቻዊው ሠዓሊና ቀራጺ ኤርኸርት ቫን ሪዊች በእንጨት ላይ ተቀርጸው መተዋወቃቸውን በዚህ ጥናታዊ ጽሑፋቸው ላይ ይፋ አድርገዋል፡፡
ዶ/ር ዊጂንማን በዚሁ ጥናታዊ ጽሑፋቸው፤ ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዓፄ ዘርዓ ያዕቆብ ከሙስሊም ተዋጊዎች ዘንድ የገጠመውን ወረራ የሚመክቱበት የጦር መሣሪያ ዕርዳታ እንዲልኩላቸው ወደ አውሮፓ ምድር መልእክተኞችን ልከው ነበር፤ በተመሳሳይም ንጉሥ ዘርዓ ያዕቆብ በዘመነ መንግሥታቸው ከዴር ሱልጣን ገዳም ሁለት ኢትዮጵያውያን መነኮሳትን ልዑክ አድርገው በ፲፬፻፴፪ ዓ.ም. በኢጣሊያ ፍሎረንስ ከተማ በተካኼደው የሃይማኖት ጉባኤ ላይ ይሳተፉ ዘንድ ልከው ነበር፡፡
የዶ/ር ዊንጅማን ጥናት እንደሚያትተው- ኢትዮጵያውያኑ መነኮሳትና በሮማ ቤተ ክርስቲያን በነበረው ግንኙነት የተነሳ ከታላቁ የቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል ጀርባ የሚገኘውን የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያንን ሮማውያኑ ካቶሊኮች ለኢትዮጵያውያን መነኮሳትና የመንፈሳዊ ተጓዦች ቤተ አምልኮና ማረፊያ እንዲሆናቸው በስጦታ ተሠጥቷቸው ነበር፡፡ ይህ የቅዱስ እስጢፋኖስ ቤ/ንም እስከ ፲፰ኛው መቶ ክ/ዘ መገባደጃ ድረስ የኢትዮጵያውያን መነኮሳትና ተጓዦች ማረፊያ እንደሆነ ቆይቷል፡፡
በ፲፯ኛው መቶ ክ/ዘ አባ ጎርጎርዮስና ጀርመናዊው ሂዮብ ሉዶልፍ በሮማ ከተማ ከመገናኘታቸው አስቀድሞ በሮማ በሚገኘው በቅዱስ እስጢፋኖስ በነበሩ የኢትዮጵያ ቤ/ን መነኮሳትና መናኒያን ጋር ተገናኝቶ ስለግዕዝ ቋንቋ ለማወቅ ጥልቅ ፍላጎትን ያሳየው በሮም ከተማ ይኖር የነበረው ጀርመናዊው ቄስ ጆን ፖትከን ነበር፡፡
ይህ ሰው በ፲፭፻፲፩ ዓ.ም. በኢየሩሳሌም በነበረው ቆይታው በዴር ሱልጣን ገዳም ከኢትዮጵያውያን መነኮሳትና ሊቃውንት ጋር ተገናኝቶ እንደነበር በጉዞ ማስታወሻው ላይ ጠቅሶታል፡፡ ጀርመናዊ ቄስ ፖትከን በሮም ቆይታው ከዴር ሱልጣን ገዳም መጥተው በሮም ይኖሩ ከነበሩት አባ ቶማስ ወልደ ሳሙኤል ከተባሉ መናኒ መነኩሴ የግዕዝን ቋንቋ በሚገባ ማጥናት ችሎ ነበር፡፡
ከአባ ቶማስ ዘንድ የግዕዝን ቋንቋ ያጠናው ቄስ ፖትከን በ፲፭፻፲፫ ዓ.ም. በአውሮፓ ምድር በግዕዝ ቋንቋ የመጀመሪያውን መዝሙረ ዳዊትን ከመኃልየ መኀልይ ዘሰለሞን ጋር በአንድነት አድርጎ አሳትሞ እንደነበር ካፒቴን ማሪዮ ዳ. ሌኦኔሳ የተባለ ምሁር በ፲፱፻፳፩ ዓ.ም. በኢጣሊያንኛ ቋንቋ ባሳተመው ‹‹ሳንቶ እስቴፋኖ ማጊዮሬ ዴግሊ አቢሲኒያ ኤ ለ ሬላዚዮኒ ሮማኖ ኢትዮጲቼ›› በሚለው መጽሐፉ ገልጾታል፡፡
በኋላም በጀርመን ኮለኝ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤ/ን አገልጋይ የሆነው ቄስ ፖትከን ከሮም ወደ አገሩ ጀርመን ከተመለሰ በኋላም መዝሙረ ዳዊትን በግዕዝ፣ በሂብሪው፣ በላቲንና በግሪክ ቋንቋ በአንድነት አድርጎ አሳትሞት ነበር፡፡
ይህ ሰው ፲፭፻፳፬ ዓ.ም. ሲሞት በእርሱ እግር በመተካት የግዕዝን ቋንቋ ጥናት በአውሮፓ ምድር እንዲቀጥል ካደረጉት መካከል ዕውቁ ሂዩማኒስት ጆናስ ሬዩችሊን እና ጆናስ ትሪቴሚዩስ ይጠቅሳሉ፡፡
እንግዲህ በአውሮፓ ምድር የግዕዝን ቋንቋ፣ የኢትዮጵያን ታሪክ፣ ባህልና ቅርስና እንዲሁም የኢትዮጵያን ቤ/ን ታሪክ፣ ዶግማና ቀኖና በማጥናት ረገድ ከጀርመናዊው ሂዮብ ሉዶልፍና አባ ጎርጎርዮስ አስቀድሞ የተጀመረ መሆኑን ልብ ይሏል፡፡ ምንም እንኳን የኢትዮጵያን ጥናት በተደራጀና በተቋም ደረጃ በማስጀመር ረገድ ስማቸው ቀድሞ የሚነሳው አባ ጎርጎርዮስ ዘመካነ ሥላሴና ሂዮብ ሉዶልፍ ቢሆንም፡፡
ከዚሁ የኢትዮጵያ ጥናት ጅማሬና መስፋፋት ጋር ተያይዞም በአውሮፓ ምድር ‹‹የካህኑና ንጉሡ ዮሐንስ አገር›› ተብላ ለረጅም ዓመታት በምናባቸው የቆየችውን ኢትዮጵያ በአውሮፓ ምድር በሚገባ እንድትታወቅና እንድትጠና በማድረግ ረገድ ፖርቹጋላውያን ትልቅ ሚና ነበራቸው ማለት ይቻላል፡፡ ፖርቹጋላውያን አሳሾችና የሃይማኖት ሰባኪዎችና ሊቃውንቶች ኢትዮጵያን በማወቅና በማስተዋወቅ ረገድ የነበራቸውን ቀዳሚ ሚና በተመለከተ አንድ ሁለት የታሪክ ማስረጃዎችን ልጥቀስ፡፡
በ፲፭፻፴፪ ዓ.ም. ኢትዮጵያዊው ንጉሥ ዓፄ ልብነ ድንግል የአዳል ገዢና የጦር አዝማች ከሆነውና ከኢብን ኢብራሂም አልጋዚ (በተለምዶ ግራኝ አሕመድ) እየተባለ ከሚጠራው የጦር ኃይል ጋር በገቡበት ጦርነት ዕርዳታን ፈልገው ወደ ፖርቹጋል ንጉሥ መልእክተኛን ልከው ነበር፡፡ ጸጋ ዘአብ ከተባለው ሊቅና ከንጉሡ መልእክተኛ ጋር በሊዝበን ከተማ የተገናኘው ታዋቂው ሂዩማኒስትና ሚሽነሪ ዳሚያኑስ ጆኤስ ከጸጋ ዘአብ ጋር ያደረጉትን ሃይማኖታዊ ውይይት በተመለከተ ያሳተመው መጽሐፍም በአውሮፓ በነበሩ በተሐድሶ አራማጆችና በአናባፕቲስቶች ዘንድ ትልቅ ዕውቅናን እና ዝናን ለማትረፍ ችሎ ነበር፡፡
ከሁለት ዓመት በኋላም ፍራንስሲኮ አልቫሬዝ በ፲፭፻፲፫-፲፭፻፳ ዓ.ም. በኢትዮጵያ የነበረውን ቆይታውን በተመለከተ በ፲፭፻፴፪ ዓ.ም በሊዝበን ከተማ ‹‹የካህኑና የንጉሡ ዮሐንስ አገር ኢትዮጵያ›› በሚል ርእስ በፖርቹጊዝ ቋንቋ ያሳተመው ዳጎስ ያለ የጉዞ ማስታወሻ መጽሐፍ በአውሮፓ ምድር ስለ ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ውበትና ሀብት፣ ስለ ሕዝቦቿም ታሪክ፣ ቋንቋ፣ ሃይማኖት፣ ቅርስ… ወዘተ. በሰፊው ለማወቅ ለሚፈልጉ ምዕራባውያን ሁሉ ትልቅ ጉጉትንና መነቃቃትን የፈጠረ ነበር ማለት ይቻላል፡፡
በዚህ ሁሉ ረጅሙ የአገራችን የታሪክ ጉዞ ውስጥ እጅግ በጥቂቱ ለመጥቀስ የሞከርኳቸው የታሪክ ማስረጃዎችና ዋቢዎች አንድ የሚነግሩን እውነታ አለ፡፡ ይኸውም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያን ለተቀረው ዓለም በማሳወቅና እንዲሁም በምዕራቡ ዓለም የኢትዮጵያ ጥናት ልደት እንዲበስር በማድረግ ረገድ- ግእዝ ቋንቋ፤ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንና ሊቃውንቶቿ ሊዘነጉ የማይገባቸው ታላቅ ባለ ውለታ መሆናቸው ነው፡፡
የኢትዮጵያ ጥናት እና ምርምር ተቋምን በጨረፍታ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ/የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በአገራችን አለ የሚባል አንጋፋና ከፍተኛ የምርምርና የጥናት ተቋም ነው፡፡ የምርምርና የጥናት ተቋሙ እንደ ስሙ ሁሉ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ለማወቅና ለማጥናት ለሚልጉ ሁሉ ተቀዳሚና ተመራጭ የምርምርና የጥናት ተቋም መሆኑም አሌ የማይባል ሐቅ ነው፡፡
ተቋሙ ባለፉት 70 ዓመታት ባደረገው ጉዞ በሥሩ ያሉት ቤተ መጻሕፍቱ፣ የኢትኖግራፊክ ቤተ-መዘክሩ (Ethnographic/Anthropological Museum)፣ የምርምርና የጥናት ማዕከሉና ከዚሁ ጋር በተቀዳሚነት አብሮ የሚነሣው የኢትዮጵያ ጥናት ወዳጆች ማኅበር/SOFIES ለተቋሙ ትልቅ ክብርና ሞገሱ ናቸው፡፡ በተጨማሪም ደግሞ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ያለበት የቀድሞው የገነተ ልዑል ቤተ መንግሥት ሕንፃ ለተቋሙ ትልቅ ታሪክን፣ ልዩ ውበትንና ግርማን አጎናጽፎታል፡፡
ተቋሙ ከሚገኝበት ታሪካዊ ሕንፃው ጀምሮ በውስጡ በዋጋ ሊተመኑ የማይችሉ ብርቅዬ/Rare Collections ሊባሉ የሚችሉ መጽሐፎችን፣ ታሪካዊ ሰነዶችና መዛግብቶች፣ የምስልና የድምፅ መረጃዎች፣ ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ሊወክሉ የሚችሉ የተለያዩ ቅርሶችን፣ ከመጀመሪያ ድግሪ እስከ ሦስተኛ ድግሪ ማሟያ የቀረቡ የጥናት ርሳናት፣ ጆርናሎች፣ ሰነዶች፣ ረጅም ዕድሜን ያስቆጠሩ በግእዝና በዐረቢኛ ቋንቋዎች የተጻፉ የብራና መጻሕፍትን በውስጡ የያዘ ኢትዮጵያውያንም ሆኑ የኢትዮጵያ ወዳጆች የሚኮሩበት አንጋፋና ልዩ ተቋም ነው፡፡
የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም በዩኒቨርሲቲው እጅግ የተከበሩና በእውቀታቸው አንቱታን ያተረፉ ምሁራን የመሩት ተቋም ነው፤ ለአብነትም ህል ለመጥቀስም፤ ፕ/ር ሪቻርድ ፓንክርስት፣ ፕ/ር ታደሰ ታምራት፣ ፕ/ር ባሕሩ ዘውዴ፣ ፕ/ር ባዬ ይማም፣ ፕ/ር ገብሩ ታረቀ፣ ዶ/ር አሕመድ ሀሰን፣ በቅርቡ በሞት የተለየችን ዶ/ር ኤልሳቤጥ ወ/ጊዮርጊስ የመሳሰሉ ምሁራን በዳይሬክተርነት የመሩት ታላቅና አንጋፋ ተቋም ነው፡፡
እንደ መውጫ፤
ዘንድሮ ለ 22ኛ ጊዜ በሐዋሳ ዩኒቨርሲቲተ የተካሄደውን ዓለም አቀፉን የኢትዮጵያን ጥናት ጉባኤ አስመልክቶ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ እና በጀርመን ሀምቡርግ ዩኒቨርሲቲ መምህርና ተመራማሪ የሆኑት መርሻ አለኸኝ (ዶ/ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ባሰፈሩት ሐሳብ ጽሑፌን ለመቋጨት ወደድኹ፡፡
… በቀደሙ የኢትዮጵያ ሊቃውንት በግእዝ ተደርሰው ወይም ወደ ግእዝ ተመልሰው ከእኛ የደረሱት የግእዝ መጻሕፍት፤ በዛሬዎቹ ሊቃውንት ልጆቻቸው ከነንባባቸው ወደ አማርኛ ወይም ሌሎች የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ተተርጉመው የሕትመት ብርሃን እያዩ ያሉበትን ሒደት የሚዳስስ ዐውደ ጥናት በሐዋሳ ዩኒቨርስቲ ስናከናውን ሰነበትን፤ ፈፀምንም፡፡
ዐውደ ጥናታችን በስመ ጥሩው ዓለም ዐቀፍ የኢትዮጵያ ጥናት ኻያ ኹለተኛው ጉባኤ ጥላ ስር የተከናወነ ነው። በእጅ ተጽፈው የቆዩን የግእዝ መጻሕፍት በኮምፒዩተር ተተይበው፣ እንደየሊቃውንቱ ብቃት ተተርጉመውና ተተንትነው የሕትመት ብርሃን ሲያዩ ምን ጨመሩ? ምንስ ቀነሱ? በምን ዓይነት ኢትዮጵያዊ ሥልትና ዘዴ ተዘጋጅተው ከሕትመት ደረሱ? ተርጓሚዎቹስ እነማን ናቸው?
የሀገራችን የግእዝ መጻሕፍት ሕትመት ታሪክስ ምን ይመስላል? በዘርፉ የሌሎች ባለሥነ ጽሑፍ ሀገራት ልምድስ ምን ይመስላል? ወዘተ— የሚሉ ጥያቄዎችን የመለሱ ፲፪ የጥናት ሥራዎች በኢትዮጵያውያንና አውሮጳውያን የሥራ ባልደረቦቼ ቀርበው ጥልቅ ውይይት አድርገናል፡፡
“Ethiopian Gǝʿǝz Literary Heritage: Contemporary Pathways from Manuscript to Print” በሚል ርእስ ባዘጋጀሁትና በመራሁት ዐውደ ጥናት ዘርፉ የበለጠ ይጠና ዘንድ ዐይን ከፋች የኾኑ ጥናቶቻቸውን ያቀረቡ ባልንጀሮቼን አመሰግናቸዋለሁ፡፡
ዓለም ዐቀፍ ጉባኤውን በግሩም ሁኔታ በማዘጋጀት ሲያስተናግደን የነበረውን የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲንም እናመሰግናለን፡፡
ሰላም!!
