ፍርድ ቤቱ የአቶ ታዬ ደንዳአን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ አደረገ

Date:

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ታህሳስ 23 ቀን 2018 ዓ.ም በዋለው ችሎት የቀድሞው የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንዳአ ያቀረቡትን የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ማድረጉን ጠበቃቸው ገለጸዋል።

የአቶ ታዬ ደንዳአ ጠበቃ አበራ ንጉሥ፤ ፍርድ ቤቱ በዋለው ችሎት የተከሳሽን የዋስትና ጥያቄ ዉድቅ በማድረግ፣ ዓቃቤ ሕግ በህዳር 24 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ መልክ ያቀረበውን ክስ መርምሮ ውሳኔ አስተላልፏል ብለዋል።

ፍርድ ቤቱ የዋስትና ጥያቄውን “ተከሳሹ በዋስ ቢለቀቁ ተጨማሪ ወንጀሎችን ሊፈጽሙ ይችላሉ” በሚል ምክንያት ውድቅ ማድረጉን አቶ አበራ አስረድተዋል።

በተጨማሪም ፍርድ ቤቱ ዓቃቤ ሕግ ህዳር 24 ቀን 2018 ዓ.ም በአቶ ታዬ ላይ ካቀረባቸው ክሶች መካከል የመጀመሪያው፣ መንግሥት “ሸኔ” ብሎ የሚጠራውን የኦሮሞ ነፃነት ጦር እና ፋኖን የሚደግፉ ፕሮፓጋንዳ ማሰራጨት እንዲሁም ሕገ-መንግሥቱን እና ሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱን ለመናድ መሞከር በሚል በወንጀል ሕግ አንቀጽ 257 (ሀ) እና (ረ) ላይ ተመስርቶ የቀረበውን ክስ ዓቃቤ ሕግ እንዲያሻሽል ማዘዙን ገልጸዋል።

የፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ አንደኛ የፀረ-ሽብር እና የሕገ-መንግሥታዊ ጉዳዮች ችሎት፣ ዓቃቤ ሕግ አሻሽሎ የሚያቀርበውን ክስ ለመስማት ለጥር 21 ቀን 2018 ዓ.ም ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱን አቶ አበራ ንጉስ ተናግረዋል።

ጠበቃ አቶ አበራ ንጉሥ፤ ደንበኛቸው አቶ ታዬ ቀደም ሲል በነበራቸው የመጀመሪያ የክስ መዝገብ ላይ በነበረባቸው የጤና ችግር ምክንያት በካቴና እንዳይታሰሩ ፍርድ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ እንደነበር አስታውሰው፣ በሀገሪቱ ሕግ መሠረት አንድ ተከሳሽ ካቴና ታስሮ ፍርድ ቤት የሚቀርበው “ለማምለጥ የሚሞክር ወይም በፀጥታ ኃይሎች ላይ የኃይል እርምጃ ለመውሰድ የሚሞክር ከሆነ ብቻ ነው” ብለዋል።

አቶ ታዬ በእድሜ የገፉ እና እንዲህ ያለ ጸባይ የሌላቸው ቢሆንም፤ ፖሊስ ይህንን ግምት ውስጥ ሳያስገባ ታህሳስ 23 ቀን 2018 ዓ.ም እጃቸውን በካቴና አስሮ ማቅረቡን ጠበቃው ገልጸዋል።

ደንበኛቸው በታኅሳስ 22 ቀን 2018 ዓ.ም በነበረው ቀጠሮ ያልቀረቡትም “በካቴና ታስሬ ፍርድ ቤት አልቀርብም” በሚል ባሳዩት ተቃውሞ መሆኑን ጠቁመው፣ ዳኛው አቶ ታዬ ከዚህ በኋላ በካቴና ሳይታሰሩ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ውሳኔ ማስተላለፋቸውን አቶ አበራ ገልጸዋል።

ለአዲስ ስታንዳርድ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ አዲስ አበባ ገቡ

ጠቅላይ ሚኒስትሯ ቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርሱ ጠቅላይ...

የቴሌኮም ኦፕሬተሮች የ5 በመቶ የአደጋ ሥጋት ምላሽ ፈንድ ክፍያን ተግባራዊ ማድረግ ጀመሩ

በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱት ሁለቱም የቴሌኮም ኦፕሬተሮች ማለትም ኢትዮ ቴሌኮም እና...

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዚዳንት ለኢራን ህዝብ – “እኛ ከእናንተ ጋር ነን”

የአውሮፓ ፓርላማ ፕሬዝዳንት ሮቤርታ ሜትሶላ፥ የኢራን መንግስት በተቃዋሚዎች ላይ...

አፍሪካ በፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ ውክልና ሊኖራት ይገባል

በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት አፍሪካ ቋሚ ውክልና...