‹‹ኳ! ኳ! ኳ!›› በማለዳ የቤቴ በር እየተደበደበ ነው፤ ‹‹ኳ! ኳ! ኳ!››
‹‹ማን ነው?›› በርግጌ ተነሳሁ።
‹‹ልጄ እኔ ነኝ ክፈት!›› ቤት አከራዬ ናቸው።
‹‹ደህና አደሩ አባባ? …በሰላም ነው?››
‹‹በሰላም ነው፤ …በሰላም ነው፤ …አንዴ ክፈትማ!››
ጥቂት አሰላሁ። የቤት ኪራይ የመክፈያ ቀኔ አልደረሰም።
‹‹ክፈትማ አንተ ብርድ ላይ ነኝ!›› ተነስቼ ከፈትኩ።
‹‹ደህና አደራችሁ!?›› አሉ አከራዬ፣ እንደገቡ ዐይናቸውን ወደ አልጋዬ እየወረወሩ፤ ‹‹ጎሽ! …ብቻህን ነህ!›› ፈገግ እያሉ፡፡
‹‹እ… አዎ! …ደህና አደሩ!?››
‹‹ይመስገነው! …አንተስ ልጄ?››
‹‹እግዜር ይመስገን!›› አልኩ ከብርድ ልብስ ውስጥ ወጥቼ፣ በቢጃማ እንዳለሁ አልጋዬ ጫፍ እንደመቀመጥ እያልኩ።
‹‹እግዚኦ!›› አሉ አከራዬ ጉንጫቸውን በመዳፋቸው ደግፈው፤ ‹‹እግዚኦ!››
‹‹ምነው አባባ?››
‹‹እንዲህ ኩርምት ብለህ ፀበልተኛ መስለህ ላየህ ማታ ትልብዥን ላይ አምሮብህ የታየህ አትመስልም!››
ፈገግ አልኩ። የምሠራበት ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማ ማታ ታይቶ ነበር። ‹‹ይቺን ለመናገር ይሆን የመጡት?››
‹‹ልጄ!››
‹‹አቤት አባባ!››
‹‹ያፈሳል እንዴ!?›› ጣራውን ሽቀብ እያዩ ጠየቁኝ፡፡
‹‹ኧረ እኔ እንጃ አባባ! አሁን ወቅቱ እኮ የዝናብ አይደለም!›› አልኳቸው ግራ በመጋባት፡፡
‹‹ኮርኒሱን ታዲያ እንዲህ ምን አበላሸው ብዬ እኮ ነው፤ …አይዞህ ሰሞኑን ቆርቆሮውን አስቀይረዋለሁ! ግድግዳውንም አስቀባዋለሁ!››
‹‹እሺ!››
‹‹ወለሉም እየተፈረፈረ ነው፤ በደንብ ሊሾ አስደርገዋለሁ!›› መሬቱን በዱላቸው እየቆረቆሩ፡፡
‹‹እውነት ነው፤ …እሺ!››
‹‹ምነው ልጄ!? አንዲት ተመላላሽ ሠራተኛም ቅጠር እንጂ!›› ዙሪያቸውን በዐይናቸው እየሰለሉ፤ ‹‹ቤቱ ቅጥ አጣ እኮ! ምግብ ታብስልልህ! ልብስህንም ታለቅልቅልህ!››
ተምታታሁ፤ ይኼ ደግነት ከየት መጣ? ‹‹መብራት አስቆጠራችሁ፤ ውኃ አባከናችሁ! ግቢ አቆሸሻችሁ!›› ብለው ተከራይን ቁም ስቅል የሚያሳዩ ዋናው የንትርክ አባት ዛሬ ምን እንዲህ አሳቢ አደረጋቸው? …እውነት ትናንት ማታ በቴሌቪዥን ስላዩኝ ብቻ!?
‹‹የውጪውን በር ቁልፍ እስካሁን አልሰጠኹኽም አይደል ልጄ!?››
‹‹እ… አዎ አባባ!›› ዋናውን ችግሬን ስላነሱት ደስ አለኝ፡፡ በግቢው በር ቁልፍ እጦት ምክንያት ለሥራም ሆነ ለሌላ አጋጣሚ ማምሸት ባለመቻሌ ደጋግሜ ጠይቄ መልስ ስላጣኹ ነበር የተውኩት፡፡
‹‹ችግር የለውም ልጄ! ነገ ከነገ ወዲያ ታገኛለህ፤ ከእንግዲህ እኮ አንተ ቤተሰብ ነህ!››
‹‹አመሠግናለሁ አባባ!››
‹‹የውጪውም ግድግዳ ቀለም ሽው ሽው ቢደረግ አይከፋም ልጄ፤ እስኪ ሰሞኑን ጥቂት ገንዘብ እጄ ይግባና እ…!››
‹‹እ… እሺ! …የቤት ኪራዩን ዋጋ ሊጭኑብኝ አስበው ይሆን?›› ለራሴ አጉረመረምኩ፡፡
‹‹ላንተማ ተዚህም በላይ ይገባኻል ልጄ፤ ማታ በትልብዥን ሳይህ ምንኛ እንደኮራኹ ብታውቅ!››
‹‹አመሠግናለሁ አባባ፤ …በጣም አመሠግናለሁ!››
‹‹በርታልኝ ልጄ! …በርታ!››
‹‹እሺ አባቴ! እሺ!››
‹‹እ! …አሁን የመጣሁት… ›› አሉ ወደ እኔ ጠጋ እያሉና እጃቸውን ወደለበሱት ካፖርት ኪስ እየሰደዱ።
‹‹እ!… ›› አልኳቸው ዐይኔ ከእጃቸው ጋር ወደ ኪሳቸው እየሔደ።
‹‹አንዲት የፍርድ ቤት ቀጠሮ ነበረቺኝ!›› አሉ የተጣጠፈች ወረቀት እያቀበሉኝ።
‹‹እና?›› ግራ ተጋባሁ፡፡
‹‹ምን እና አለው ልጄ!? …ምን እና አለው? እንደምታውቀው መከራ እንበላለን እንጂ ፍትሕ የለም!›› ፊታቸው በብስጭት ተለዋወጠ፤ ‹‹ፍትህ እንደሆነች ከፈረስ ጭራም ቀጥናለች፡፡ ብንወጣ፣ ብንወርድ በየት በኩል ተገኝታ!?››
ግራ ተጋባሁ፡፡ ወረቀቱን አየሁት፤ የፍርድ ቤት ቀጠሮ ነው፡፡ ለእሳቸው የተጻፈ፡፡
‹‹ማረሚያ ቤቱ ሙዚየም ሆነ የሚሉት ለካ የእኔ ብጤውን አረጋዊ መቀመጫ ሊያደርጉት ነው፡፡ ሆሆሆሆ!… ደግሞ እስቃለሁ፤ ጥርሴ ይርገፍ አቦ! ሆሆሆሆሆ… ›› እየተርገፈገፉ ሳቁ፤ ‹‹ለነገሩ ለምን ጥርሴ ይርገፍ! ማን ደስ እንዲለው ይርገፍ!?››
‹‹አባቴ ይቅርታ ቁጭ ይበሉና… ›› አልኩ ሰውነታቸው በንዴት ሲንቀጠቀጥ አሳዝነውኝ፡፡
‹‹አይ ልጄ መች የሚያስቀምጥ ጉዳይ ይዤ መጣሁና! …ይልቅስ ቀጠሮዋ መቼ ትላለች እያት እስኪ!?›› ወረቀቱን አየሁት።
‹‹አንድ ሣምንት ይቀርዎታል!›› መልሼ ልሰጣቸው እጄን ዘረጋሁ።
‹‹እኮ አንድ ነገር በለኛ!››
‹‹እንዴ! ምን ልበልዎ?›› ግራ ተጋባሁ።
‹‹እህ ምክር ስጠኛ፤ ፍርድ ቤት ስቀርብ ምን ማለት እንዳለብኝ ንገረኛ!››
ሳቄ መጣ። ጠዋት ባይሆን፣ በዚያ ላይ አከራዬ ባይሆኑ ከት ብዬ በሳቅኩ ነበር።
‹‹ልጄ እኔማ… !›› አሉ ድምፃቸውን ዝግ አድርገው ወደ ጆሮዬ እየተጠጉ!››
‹‹እ!›› ለአፋቸው ጆሮዬን እየሰጠኹ፡፡
‹‹መቼም ጊዜው ተበላሽቷል፡፡ ፍትሕን ሞግቶ ማግኘት በዚህ ጊዜ የማይቻል ነው፡፡ በዚህ እድሜዬ ከምወጣ ከምወርድ በእጅ መንሻም ቢሆን ጉዳዩ ቢዘጋ ብዬ እያሰብኩ ነበር፡፡››
‹‹ውይ አባባ እኔ እኮ ስለፍርድ ቤት ጉዳይ ምንም አላውቅም!›› አልኳቸው እየፈራኹ፡፡
‹‹እንዴት?›› ተቆጡ አከራዬ፤ ‹‹ምን ማለት ነው?›› ፍንጥር ብለው ተነሱ፡፡
‹‹ማለቴማ ፍርድ ቤት አይደለም የምሠራው! …ስለጉዳዩም እውቀት የለኝም!››
‹‹ኣ! …ምንም ሳታውቅ ነው እንዴ ትልብዥን ላይ የምትሠራው!?››
‹‹አባቴ እኔ እኮ ተዋናይ ነኝ!››
‹‹ተዋናይ ማለት!?››
‹‹ድራማ ሠሪ ነኝ!›› ሳቅ እንዳያመልጠኝ እየታገልኩ ነው።
‹‹እንዴ ድራማስ ቢሆን ጠበቃ ሁነህም አይደል እንዴ ያየኹኽ? …ተው እንጂ ልጄ!››
‹‹ይኸውልዎ፤ አልገባዎትም አባባ!›› አቋረጡኝ።
‹‹ነው ወይስ…›› ንግግራቸውን ጎርደው እንደመሳቅ አሉ፤ ‹‹ነው ወይስ ትልብዥኑ ውስጥ ስትቀበል እንደማየው ከእኔም እጅ መንሻ ፈለግክ! እ? አንተ! ታባትህ እጅ መንሻ!? እ!?››
‹‹ይኸውልዎ አባባ!… ››
‹‹አባባ አትበለኝ! …አትበለኝ! …ተው እንጂ ልጄ ተው!›› በብስጭት እየተመናቀሩ በሩን በላዬ ላይ ዘግተውት ወጡ፡፡
አሁን አልቻልኩም። ከትከት ብዬ ሳቅኩ።ብዙ የመድረክ ላይ ቴአትሮችን፣ የሬዲዮ እና የቴሌቪዥን ተከታታይ ድራማዎችን፤ እንዲሁም ጥቂት የማይባሉ ፊልሞችን የሠራው የቅርብ ወዳጄ፤ ተከራይቶ በሚኖርበት ቤት ውስጥ የገጠመውን ነገር ያጫወተኝ ነው፡፡
