የኤርትራው ፕሬዝደንት ኢሳያስ አፈወርቂ፣ ቅዳሜ ሐምሌ 12 ቀን 2017 ዓ.ም. በኤርትራ ሚዲያዎች በተላለፈው ቃለ መጠይቃቸው ላይ፣ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ “ከእውነታ የራቀና ያልበሰለ” ሲሉ ውድቅ አደረጉ።
ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አህመድ ከዚህ ቀደም “የባህር በር ጥያቄን ማንሳት ነዉር መኾኑ አክትሟል።” ማለታቸው ይታወሳል።
ይህ የፕሬዝዳንቱ ቃለምልልስ፣ በቅርቡ በኢትዮ-ኤርትራ ድንበር አካባቢ ወታደራዊ ውጥረቱ እየጨመረ በመጣበት ወቅት የተሰጠ ሲሆን፣ ኤርትራ በታሪኳ የመስፋፋት አላማ ኖሯት ጦርነት ከፍታ አታውቅም በማለት ሲናገሩ ተደምጠዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በቃለ መጠይቃቸው ላይ፦ “እኛ ጦርነትን ፈጽሞ ፈልገን አናውቅም፤ ወደፊትም አንፈልግም። ነገር ግን ራሳችንን የመከላከል ጉዳይ ሲመጣ፣ ግዴታችን ነው – ታሪክም ይህንን ሁሉ መዝግቦታል” ብለዋል።
ፕሬዝዳንቱ የኢትዮጵያን የባህር በር ጥያቄ በተመለከተ ሲናገሩ፣ “‘እኛ 130 ሚሊዮን ነን፣ ባህር እንፈልጋለን’ የሚለው ሀሳብ ስልት ሳይሆን ‘የልጅነትና የማይረባ ምኞት’ ነው” ብለዋል።
አክለውም “ጤነኛ አእምሮ ያለው ሰው እንዲህ አያስብም” ሲሉ ጥያቄውን ሙሉ በሙሉ አጣጥለውታል። ይህ የኢሳያስ ምላሽ፣ በፖለቲካ ተንታኞች ዘንድ፣ ለጉዳዩ በድርድር መፍትሄ የመፈለግን በር የሚዘጋና የሁለቱን ሀገራት ውጥረት ይበልጥ የሚያባብስ ተደርጎ ተወስዷል።
ኤርትራ የምትወስዳቸው እርምጃዎች በሙሉ “ራስን ለመከላከል” እንደሆኑ መግለጻቸው፣ እንደ ሳዋ ምረቃ እና የቡሬ ተኩስ ያሉትን ወታደራዊ እንቅስቃሴዎች ለማጽደቅ የታለመ ነው ሲሉ ተንታኞቹ ይናገራሉ።
ኢሳያስ በአፍሪካ ጉዳዮች ላይ ያላቸውን አቋምም በዚህ ቃለምልልስ ላይ ያሳዩ ሲሆን፣ ፕሬዝዳንቱ ከውጥረቱ ባሻገር፣ ለዘላቂ እድገትና ስልጣኔ ሀገራት የራሳቸውን ልማት ባለቤት መሆን እንዳለባቸው በማሳሰብ፣ የጠንካራ የአፍሪካ ውህደት አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሳያስ በተለይም በኢትዮጵያ የባህር በር ጥያቄ ላይ የሰጡት ቀጥተኛና አጣማሪ ምላሽ፣ በቀጣይ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው ግንኙነት ምን ሊመስል እንደሚችል አመላካች ተደርጎ ተወስዷል።
ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ ከቀናት በፊት በፓርላማ ቀርበው በባህር በር እና በኤርትራ ጉዳይ ሲናገሩ ” የባህር በር ፍላጎታችን በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ማግኘት እንጂ በኃይል አንፈልግም።
በሰላማዊ መንገድ ነው ሁሉንም ማሳካት የምንፈልገው። ሉዓላዊነታቸውን እናከብራለን። ኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሀገር ናት፤ ይህ ሙሉ እንዲሆን ደግሞ የባህር በር እንድታገኝ ጎረቤቶቻችን በጎ ምላሽ መስጠት አለባቸው። ኢትዮጵያ በትናንሽ ጠጠር አትታወክም፤ ኢትዮጵያ ትልቅ ሀገር ትልቅ ባህር ናት።
ኢትዮጵያ የሚያውካትን ተከላክላ መልማት ትችላለች። ይህንን በደንብ ተገንዝቦ ሰብሰብ ማለት ያስፈልጋል። ኢትዮጵያ ከፍተኛ ኢኮኖሚ፣ የህዝብ ቁጥር፣ የዘመነ ሰራዊት ያላት ሀገር ናት።
ከኤርትራ ጋር የጦርነት ስጋት ለሚያነሱ አካላት በእኛ በኩል ምንም ዓይነት ውጊያ እንደማንፈልግ ማወቅ ይገባል፤ ይህንን በእነሱም በኩል ማድረግ አለባቸው። ባለፉት ሰባት ዓመታት አንድም ግጭት ከጎረቤት ሀገራት ጋር አላደረግንም።
ትብብር አብሮ ማደግ ነው ፍላጎታችን። የማንሰራራት ጉዟችን እንዳይስተጓጎል ከሁሉም ጎረቤቶቻችን ጋር በሰላም መኖር እንፈልጋለን። ” ብለው እንደነበር ይታወሳል፡
