በወንድማችሁ መከራ አንድ_ የምትሆኑ ታዩ ዘንድ ኑ
💠ቃል ቀዳማዊ ነው ። ያ ቃል የእግዚአብሔር ቃል ነው ። ያ ቃል ሥጋ ሆነ በእኛም አደረ ከእኛም ሠወረው ።
💠የሚጠፋ ሥጋን ለበሰ የማይጠፋም አደረገው በዚህች ሥጋ የማይገረፍ አምላክ ተገረፈ።
💠በወንድማችሁ መከራ አንድ የምትሆኑ የወዳጆቻችሁንም መከራ የምትቀበሉ ይህን ግርፋት ታዩ ዘንድ ኑ ። በዓይን ለሚያየው ዕፁብ ነው በጆሮው ለሚሰማው ድንቅ ነው ።
💠 ከባርያ የፊቱን መጸፋትና በሊቃነ ካህናቱም ሸንጎ ራስን በዘንግ መመታቱን ታዩ ዘንድ ኑ ።
💠ዓለማትን ሁሉ የሚያድን ጌታን ያቀዳጁትን የእሾህ ዘውድ ታዩ ዘንድ ኑ ።
ለርሱ ብቻ እንሰግድ ዘንድ ኑ ።
💠በአየር ላይ የምትወጡ ሁላችሁ የመላእክት ሠራዊት ወደ ፀሓይና ወደ ጨረቃ ወደ ከዋክብትም የምትላኩ ወደ ባሕርና ወደ ቀላያትም የምትወጡ ። የአምላክችን የፊቱን መጸፋት ባየች ጊዜ ባሕር ተንቀጠቀጠች ማየ ተከዚም ሸሸች ። ፀሐይ ጨለመ ጨረቃም ደም ሆነ ከዋክብትም ከብዙ ብርሃናቸው ተራቆቱ።
💠ሞት ፈራ ዲያብሎስም ወደቀ ሲኦልም ግሩም የሆነ አምላክን ለመቀበል ከወገኖችዋ ጋራ ባንድነት ሄደች ።
💠የካህናት አለቃ ወደ መጋረጃ ውስጥ በገባ ጊዜ በጸሎት ቤት የተደረገውን ድንቅ ነገር ታዩ ዘንድ ኑ ።
💠ሁሉም መለኮትን የምትሸሽግ ሕሊናትንም ሁሉ የምትሠውር ናት ይሏታል የአጋዕዝትና የመናፍስት ጌታ በተዋረደ አህያ ግልገል ተቀምጦ ወደርስዋ ገባ ።
💠በእግዚአብሔር ስም የሚመጣ ቡሩክ ነው አንተም የአማልክት አምላክ የእስራኤልም ንጉሥ እግዚአብሔር ቡሩክ ነህ እያሉ ለሚያመሰግኑ ሕፃናት ጌትነቱን አሳየ ።
ሁሉ የሆሣዕናን ዑደት ለነርሱ ለደቀ መዛሙርቱ አሳየ ቡሩክ እርሱ በታላቅ ቃል እየጮሃችሁ ሆሣዕና በአርያም በሉ አላቸው ።
💠ሆሣዕና በአርያም
ሆሣዕና በአርያም
ሆሣዕና በአርያም ።
👉 ከመድኃኒትነቱ የተነሣ ከዚህ አስቀድሞ ያልተደረገ ከዚህም በኋላ የማይደረግ ተኣምራትና መንክራትን አሳየ ።
💠ሆሣዕና በአርያም
ሆሣዕና በአርያም
ሆሣዕና በአርያም ።
👉ከመድኃኒትነቱ የተነሣ ከቤቱ መሠረት ሳይናወጥ ከልዑል መንበሩ ወርዶ ጸጋንና
ኃይልን ሰጠ ።
💠ሆሥዕና በአርያም
ሆሣዕና በአር ያም
ሆሣዕና በአርያም ።
👉ከመድኃኒትነቱ የተነሣ ለኃጥኣን የዕንባ ምንጭ ሰጠ ።
የበደሉትን ያጻድቃቸው ዘንድ የረከሱትን ያነጻቸው ዘንድ የሳቱትን ይመልሳቸው ዘንድ ።
💠ሆሣዕና በአርያም
ሆሣዕና በአርያም
ሆሣዕና በአርያም ።
👉ከመድኃኒትነቱ የተነሣ ለዕዉራን ዳግመኛ የማይጠፋ ዓለም ሊቀበለው የማይቻለው ብርሃንን ሰጣቸው ።
ከሕሊና አስቀድሞ ያውቃል ከአሳብም በፊት ይመራመራል የሚሠወረውም የለም ።
ቅዳሴ ዘጎርጎርዮስ ኤጲስ ቆጶስ ዘኑሲስ
እንኳን ለበዓለ ሆሳዕና እና ለጥንተ ስቅለት አደረሳችሁ።
