የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት (ICS) ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ለሚያበረክቱ የውጭ አገር ባለሀብቶች የሚሰጥና እስከ 10 ዓመት የሚያገለግለው ‘ጎልደን ቪዛ’ ካርድ በያዝነው የ2019 በጀት ዓመት ለአገልግሎት ዝግጁ እንደሚያደርግ ገልጿል።
ይህ ‘ጎልደን ቪዛ’ ተብሎ የተሰየመው የመኖሪያ ፈቃድ እንደ ተባበሩት አረብ ኤምሬትስ (UAE) ባሉ እና በሌሎችም ሃገራት በካርድ መልክ የሚሰጥና ለውጭ ባለሀብቶች/ኢንቨስተሮች ልዩ መብቶችን (Privileges) የሚያጎናጽፍ መሆኑን ተገልጿል።
የ10 ዓመት የጎልደን ቪዛ ካርድ በዋናነት ከፍተኛ መዋለንዋይ በማፍሰስ ኢትዮጵያ ውስጥ መሥራት ለሚፈልጉ ባለሀብቶችና ለቤተሰቦቻቸው የረጅም ጊዜ ዋስትና ለመስጠት ታስቦ የተዘጋጀ ነው።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ካርዱ “ጎልደን ቪዛ” የተሰኘበትን ምክንያት ሲያስረዳ “ጎልደን” ቪዛ ካርድ ቪዛ የምንልበት ምክንያት ለሰዎቹ የሚሰጠውን ልዩ ጥቅም(Privileges) ለማንሳት ነው” ያለን ሲሆን ሌሎችም ሃገራት እንደሚተገብሩት ያለ አሰራር መሆኑን ገልጾልናል።
አክሎም “ጎልደን ቪዛ ከኢንቨስተር ጋር የተገናኘ ነው አስር አመት በቪዛው መቆየት ይችላሉ ዋና አላማው ኢንቨስተሮች ከፍተኛ መዋለነዋይ አፍስሰው እዚህ ሀገር ላይ ዋስትና ተሰምቷቸው እነሱ እና ቤተሰቦቻቸው ረጅም ጊዜን አስበው ከኢትዮጵያ ጋር ተሳስረው እንዲሰሩ ለማበረታታት ነው”በማለት ተናግሯል።
ካርዱ የሚያስገኘው ጥቅም በተመለከተም “አንድ የውጭ ዜጋ ኢትዮጵያ ላይ ሲኖር ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ ወይም ትውልደ ኢትዮጵያዊ መታወቂያ ሊኖረው ይገባል ከዚያ ውጭ እንደቪዛው አይነት ለአጭር ጊዜ ቆይታ እንጂ መኖር አይችልም ወደ “ጎልደን ቪዛ” ስንመጣ ግን ለምሳሌ 10 ሚሊየን ዶላር እና ከዚያ በላይ ኢንቨስት ያደረገ ከሆነ እና አመልካቾች ከማንኛውም የፀጥታ ስጋት ነፃ መሆናቸው ሲረጋገጥ ካርዱን ይወስዳሉ እሱን ወሰዱ ማለት ኢትዮጵያ ውስጥ ህጋዊ ነዋሪ ናቸው”በማለት አረጋግጧል።
አገልግሎቱን ለመጀመር የሚያስፈልጉ የአዋጅና የደንብ ማሻሻያዎች በሚኒስትሮች ምክር ቤትና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በኩል ጸድቀው መጠናቀቃቸውን አገልግሎቱ አረጋግጧል።
በአሁኑ ወቅት ዝርዝር ማስፈጸሚያ መመሪያዎችን ከፍትህ ሚኒስቴር ጋር የማጠናቀቅ፣ የመሰረተ ልማት ዝርጋታና የካርድ ዝግጅት (Personalization) ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ።
ካርዱን ለማግኘት “10 ሚሊየን ዶላር ወይም ደግሞ 5 ሚሊየን ዶላር ኢንቨስት አድርጎ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል የፈጠረ ከሆነ እና ከሁለት አንዱን መስፈርት ካሟላ ያገኛል” ቢባልም ቀጥሎ በሚወጣው ማስፈጸሚያ መመሪያ :-
• ለበርካታ ኢትዮጵያውያን የስራ እድል የፈጠረ ሲባል ምን ማለት ነው? ቁጥሩስ ምን ያህል ነው ?
• ከደህንነት ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ሲኖሩ እንዴት ይሰረዛል?
• በጣም ፈታኝ በሆነ የስራ መስክ ላይ የተሰማራ የውጭ ባለሃብት እና አነስተኛ ድካም የሚጠይቅ የስራ እድል የፈጠረ ባለሃብትስ እንዴት ይታያል? የሚሉና ሌሎችም ዝርዝር ጉዳዮች የሚወሰን ይሆናል።
አስፈላጊው የሕግና የቴክኖሎጂ ዝግጅቶች ተጠናቀው የጎልደን ቪዛ ካርዱ በ2019 በጀት ዓመት ውስጥ ለባለሀብቶች መሰጠት ይጀምራል ተብሏል።
ባለሀብቶች ይህንን የ10 ዓመት የጎልደን ቪዛ ካርድ ለማግኘት ለመደበኛ አገልግሎት 10,000 የአሜሪካ ዶላር፣ ለአስቸኳይ (Express) አገልግሎት 12,500 የአሜሪካ ዶላር መክፈል የሚጠበቅባቸው ሲሆን፣ በተጨማሪም አገልግሎቱን በቅርበትና ባሉበት ቦታ ለማግኘት የሚያስችል ‘የቤት ለቤት’ (Home service) አማራጭም ተዘጋጅቷል ተብሏል።
@tikvahethiopia
