ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ህወሓት የአፍሪካ ህብረት በሰሜን ኢትዮጵያው ትግራይ ክልል እየከፋ ለመጣው ውጥረት ትኩረት ሰጥቶ እልባት እንዲያበጅ ጠየቀ፡፡ ህወሓት ሓሙስ የካቲት 05 ቀን 2018 ዓ.ም. ለህብረቱ ሊቀመንበርና አባላቱ በላከው ግልጽ ደብዳቤ የፕሪቶሪያው ስምምነት በአስቸኳይ እንዲተገበር ጠይቋል፡፡
ሕወሃት ለአፍሪቃ ሕብረት የላከው ደብዳቤ ምን ያህል ትኩረት ያገኝ ይኾን?
ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) የአፍሪካ ህብረት በሰሜን ኢትዮጵያው ትግራይ ክልል እየከፋ ለመጣው ውጥረት ትኩረት ሰጥቶ እልባት እንዲያበጅ ጠየቀ፡፡
የደብዳቤው ይዘትና መልእክቱ
ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፤ ሓሙስ የካቲት 05 ቀን 2018 ዓ.ም. ደግሞ አዲስ አበባ ውስጥ 39ኛውን መደበኛ ጉባኤ መቀመጥ ለጀመረው ለአፍሪካ ህብረት በላከው ደብዳቤ በትግራይ ክልል እየተጋጋለ ለመጣው ውጥረት ትኩረት ሰጥቶ እንዲመክርበት ጠይቋል፡፡
ይህ የሕወሓት ጥሪ በሰሜን ኢትዮጵያ ደም አፋሳሹግጭት ዳግም ሊነሳ ይችላል በሚል በርካቶችን ባሰጋበትና ዓለማቀፉ ማህበረሰብና የሰብዓዊ ተቋማት የማስጠንቀቂያ መልእክት እያስተላለፉ በሚገኙበት ባሁን ወቅት ነው፡፡ ምንም እንኳን የፌዴራል መንግስት ምላሽ ባይሰማም፤ ህወሓት የፌዴራል መንግስት ሌላኛውን ዙር አስከፊ ጦርነት ለመክፈት የጦር መሳሪያ እና ሎጂስቲክሱን ወደ ክልሉ እያስጠጋ ነው በማለት ክሱን ያሰማውም በዚሁ ጊዜ ነው።
ደብዳቤው የህብረቱን ትኩረት ይወስድ ይኾን?
ህወሓት አሁን ላይ ለአፍሪካ ህብረት በላከውም ይፋዊ ባለው ደብዳቤም በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ በፕሪቶሪያው የግጭት ማቆም ስምምነት የተቋጨው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት አሁንም አፈጻጸሙ ላይ ተግዳሮት ስለገጠመው ትኩረት እንዳይነፈግ የሚጠይቅ ነው የሚሉት የአከባቢውን ፖለቲካዊ ሁኔታ በቅርበት የሚከታተሉት የዓለማቀፍ ህግ ባለሙያ አቶ ዓወት ልጃለም፤ ይህ የአጉሪቱ ሰላምና ፀጥታን የማስጠበቅ ሁኔታ የህብረቱ ቁልፍ ዓላማ እንደሆነም አስገንዝበዋል፡፡
“ህብረቱ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ስጀመር ከምዕራባውያን ሃያላን አገራት ባነሰ መልኩ ደካማ ሚና ነበረው” የሚሉት ባለሙያው በኋላ ላይ ግን በኃያላኑ አገራት ጫናም ቢሆን በተጫወተው ቁልፍ ሚና በህብረቱ ማዕቀፍ ስር የተደረገው የፕሪቶሪያ ስምምነት ግጭቱን ማቆሙ ቀላል ስራ እንዳልነበር አስታውሰዋል፡፡ አሁንም ህወሓት የጻፈለት ደብዳቤ ህብረቱ ያፈራረመውን ስምምነት ሙሉ በሙሉ እንዲያስተገብር የሚጠይቅም ጭምር ነው ብለዋል፡፡
ችግሩ እንዳይባባስ የቀረበው ማሳሰቢያ
የህወሓት ደብዳቤ ከዚህ በፊት በሰሜን ኢትዮጵያ ደም ያፋሰሰው ግጭት አሁን እንዳይባባስ የሚያሳስብ ነው የሚሉት የህግ ባለሙያው አቶ ዓወት፤ ህብረቱ ለጥያቄው ትኩረት ሰጥቶ እንደሚመክርበት እምነት አላቸው፡፡ “የአፍሪካ ህብረት ጉዳዩን ችላ ይልዋል ብዬ አልጠብቅም፤ ትኩረት ይሰጠዋል” በማለትም፤ አሁንም ግን ሁለቱን ተደራዳሪ አካላት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ መንግስት እና ሕወሓትን አንድ ላይ አምጥቶ ጫና በማሳደር እልባት ማስቀመጥ ላይ ጥርጣሬ መኖሩን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ እንደ መንግስት በህብረቱ ላይ የምታሳድረው ተጽእኖ ቀላል እንዳልሆነ ያስገነዘቡት ባለሙያው ህብረቱ ይህን ጫና ተቋቁሞ ለደብዳቤው አፋጣን ምላሽ ይሰጠዋል የሚል ጠንካራ እምነት ባይኖርም ግን ቢያንስ ትኩረት ይነፍገዋል ተብሎ ግን እንደማይጠበቅ አስረድተዋል፡፡
ከሀገር ያለፈው ቀጣናዊ ስጋት
የኢትዮጵያ መንግስት ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ ጥር 30 ቀን 2018 ዓ.ም. የኤርትራ መንግስትን ኢትዮጵያ ውስጥ አማጺያንን በመደገፍ ከሶ ወታደራዊ እንቅስቃሴዋን እንዲታስወጣ የጠየቀበት ደብዳቤም ይዘቱ በሰሜን ኢትዮጵያ እየተወሳሰበ ከመጣው ጉዳይ አይርቅም የሚሉት የዓለማቀፍ ህግ ባለሙያው፤ የአፍሪካ ህብረት ከህወሓቱ ደብዳቤ ባሻገር ይህንንም እንደ ቀጣናው ማየቱ አይቀሬ ነው ብለዋል፡፡
“ይህ የኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ብቻ ሳይሆን ሱዳን እና ኤርትራን የሚያቅፍ ቀጣናዊ ጉዳይ ስለሚሆን ህብረቱ አንስቶ እንደሚመክርበት ይጠበቃልም” በማለት፤ የህብረቱ አስቀድሞ ግጭትን የመከላከል ጠንካራ ውሳኔ ያን ያህል ባይጠበቅም ብያንስ ጉዳዩ የህብረቱ አጀንዳ ላይ እንደሚሆን ይጠበቃልም ሲሉ አስተያየታቸውን ሰትተዋል፡፡
ባሳለፍነው ሰኞ የካቲት 02 ቀን 2018 ዓ.ም. ባወጣው ይፋዊ መግለጫ የፌዴራል መንግስት ትግራይ ክልል ውስጥ ጦርነት ለመክፈት ከፍተኛ ዝግጅት እያደረገ ነው ሲል ያመለከተው ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት)፤ ምንም እንኳን የፌዴራል መንግስት ምላሽ ባይሰማም፤ የፌዴራል መንግስት ሌላኛውን ዙር አስከፊ ጦርነት ለመክፈት የጦር መሳሪያ እና ሎጂስቲክሱን ወደ ክልሉ እያስጠጋ ነው በማለት ክሱን ማሰማቱም ይታወሳል፡፡
DW Amharic
