ሕዝበ ሙስሊሙ ለመጅሊሱ ምርጫ ከነገ ጀምሮ ለ12 ቀናት የመራጭነት ካርድ እንዲወስድ ኮሚቴው ጥሪ አስተላለፈ።
ሕዝበ ሙስሊሙ ለኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት (ለመጅሊስ) ምርጫ ለማድረግ፣ ከነገ ጀምሮ በአቅራቢያው በሚገኝ የወረዳው መስጅድ የመራጭነት ካርድ እንዲወስድ፣ የጠቅላይ ምክር ቤቱ የምርጫ አስፈፃሚ ቦርድ ጥሪ ማድረጉን ኢፕድ ዘግቧል።
የቦርዱ ምክትል ሰብሳቢ ዶ/ር አብዱልዋሲዕ ዩሱፍ ዓሊ እንዳሉት፤ ላለፉት 5 ወራት ዝግጅት ሲያደርግ የቆየው ቦርዱ፣ በ2017 ዓ.ም ለሚካሄደው የመጅሊስ ምርጫ ዝግጅቱን አጠናቅቋል። በነገው ዕለትም ምዝገባ ይጀምራል ብለዋል።
ምርጫ ቦርዱ ምርጫውን አሳታፊና አካታች በሆነ መልኩ ለማካሄድ አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን ገልጿል፡፡
በመሆኑም ሕዝበ ሙስሊሙ መታወቂያውን በመያዝ፣ ከነገ ጀምሮ ለ12 ቀናት በየመስጅዱ በሚደረገው የመራጮች ምዝገባ ተመዝግቦ የመራጭነት ካርድ እንዲወስድ ቦርዱ ጥሪ አቅርቧል።
በምዝገባው ሂደት ለሚያጋጥሙ ቅሬታዎች አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በየመስጅዱ የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ መቋቋሙም በመግለጫው መጠቆሙን ኢፕድ በዘገባው አመልክቷል፡፡
