የቀድሞው የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ለገሠ ወልዴ በህይወት በነበሩበት ወቅት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ዕውቅና ይሆን ዘንድ ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በሐዋሳ ከተማ እያስገነባ ባለው ሆስፒታል የሚገኘውን የህክምና መስጫ ማዕከል በሰማቸው እንዲሰየም ወሰነ፤
ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ በአሁኑ ወቅት እንደ ሐገር ከፍተኛ የሆነ የአገልግሎት ተደራሽነት ችግር የሚስተዋልበትን የኩላሊት ዕጥበት አገልግሎት ለማስፋት በሐዋሳ ከተማ የከፈተው የሐዋሳ ኩላሊት ዕጥበት ህክምና ክሊኒክ የፌዴራልና የተለያዩ ክልሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች ፣አርቲስቶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በሲዳማ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ክቡር አቶ ደስታ ሌዳሞ እና በኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ክብርት ዶ/ር መቅደስ ዳባ ተመርቆ ስራ ጀምሯል።
በኩላሊት ዕጥበት ህክምና ማዕከሉ ምርቃት ፕሮግራም ላይ ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ባለፉት 33 አመታት ወላጅ አጥ ሆነው በማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር ጎዳና የወጡ ህፃናትንና አረጋዊያንን በመርዳት ለሰራቸው ውጤታማ የበጎ አድራጎት ስራዎች እንዲሁም ለሐዋሳ ኩላሊት ዕጥበት ህክምና ማዕከል መከፈት የላቀ አስተዋጽኦ ለነበራቸው አካላት የምስጋናና የዕውቅና መርሐግብር መካሄዱን የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ መስራችና ዋና ስራ አስኪያጅ ሲ/ር ዘቢደር ዘውዴ ገልፀዋል። በዚሁ መሠረት የቀድሞው የሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪነትን ጨምሮ በተለያዩ የመንግስት የስራ ኃላፊነት ቦታዎች ያገለገሉትና የመጀመሪያው የሐዋሳ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ የነበሩት አቶ ለገሠ ወልዴ በህይወት በነበሩበት ወቅት በኃላፊነት ዘመናቸው ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ላከናወናቸው የልማትና የበጎ አድራጎት ስራዎች ስኬታማነት ላበረከቱት አስተዋጽኦ ሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ ጎዳና ለወጡ ህፃናትና አረጋዊያን አገልግሎት እንዲሰጥ በሐዋሳ ከተማ እያስገነባ በሚገኘው ሆስፒታል ውስጥ የሚገኘው አንዱን የህክምና መስጫ ማዕከል በአቶ ለገሠ ወልዴ ስም መሰየሙን ሲ/ር ዘብደር ዘውዴ ገልፀዋል።
ከዚህ በተጨማሪ የቀድሞው የሐዋሳ ከንቲባ ልጅ የሆኑትና በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ የመድኃኒት አቅራቢ አገልግሎት የደቡብ ኢትዮጵያ ክላስተር አስተባባሪና የሐዋሳ ቅርንጫፍ ስራ አስኪያጅ እና የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ አምባሳደር የሆኑት አቶ ዘመን ለገሠ የአባታቸውን ፈለግ በመከተል የሜሪ ጆይ ኢትዮጵያ የሐዋሳ ኩላሊት ዕጥበት ማዕከል እንዲከፈት ከፍተኛ ሚና በመጫወት የላቀ አስተዋጽኦ የነበራቸው በመሆኑ የምስጋናና የዕውቅና ሽልማት እንደተሰጣቸው ሲ/ር ዘብደር አሳውቀው የኩላሊት ዕጥበት ህክምና ማዕከሉ እንዲከፈት አስተዋጽኦ ለነበራቸው አካላት በሙሉ ምስጋና አቅርበዋል።
የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በስራ ዘመናቸው በአገልጋይነት ሰሜት ለህዝብና ለሐገር የሚጠቅም መልካም ስራ ከሰሩ እነሱ ቢያልፉም በሰሩት ውጤታማ የልማት ሰራ እየታወሱ እንደሚኖሩ የገለፁት ሲ/ር ዘብደር የመጀመሪያው የሐዋሳ ከተማ ከንቲባ ለነበሩት ለአቶ ለገሠ ወልዴ የተሰጠው ዕውቅናም የዚህ ማሳያ ነው ብለዋል።
