ቅንጅቱ እስከ ህዳር ወር መጨረሻ ሳምንት ምርጫውን በተመለከተ “ እርምጃ ለመውሰድ ቀነ ገደብ ” አስቀመጠ

Date:

ቅንጅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከአንድ ሳምንት በፊት በጎንደር ያስተላለፉት መልዕክት ስለሀገሪቱ የሰላም ሁኔታ ምስክር ይሆናል ሲልም ተናገሯል፡፡

ኢሕአፓ፣ መኢአድ፣ እናት፣ አኢዴፓና አግን የመሰረቱት ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት የተሰኘው ቅንጅቱ “ ምርጫ የዴሞክራሲያዊ ሂደት ማሳለጫ እንጂ የይስሙላመርሐ ግብር ማሟያ ሊኾን አይገባም!  ”  ሲል ሰይሞ በዛሬው ዕለት ያወጣውን መግለጫ ለአዲስ ማለዳ ልኮላታል፡፡

ቅንጅቱ በመግለጫው ለምርጫ ክንውን መሠረታዊ ተብለው ከሚጠቀሱት ግንባር ቀደም ጉዳዮች ውስጥ የአገራችን ሰላምና ፀጥታ የተረጋጋ አለመኾኑና አገራችን ለተከታታይ ዓመታት በእርስ በርስ ጦርነት ውስጥ መቀጠሏ የምርጫውን በአግባቡ መከናወን መቻል ከፍተኛ ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነው ብሏል።

የቅንጅቱ አባል ፓርቲዎች “ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች እየተካሄዱ ላሉ ጦርነቶች ሰላማዊ የፖለቲካ መፍትሔ ሊበጅላቸው ይገባል ብለን በተደጋጋሚ ያሳሰብን ቢኾንም ለጥሪያችን ተገቢው ትኩረት ተችሮ ምላሽ ባለመሰጠቱ አገር ዛሬም ከዳር እስከ ዳር በጦርነት ውስጥ ትገኛለች ”  ሲሉም ወቅሰዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጎንደር ከተማ በቅርቡ ባደረጉት ጉብኝት ከጎንደር እስከ ጎርጎራ ያለ አጃቢ መንቀሳቀስ አለመቻሉን መግለጻቸው የአገርን ነባራዊ ኹኔታ በግልጽ የሚያሳይ ሲኾን ለዚኽ የአገሪቱን ከፍተኛ የሥልጣን መንበር ከጨበጡ ሰው የላቀ ሌላ ተጨማሪ ምስክር አይሻም በማለትም አትተዋል፡፡

“ የእርስ በርስ ጦርነቱ እንዳለ ኾኖ በጋዜጠኞች ላይ በተለያዩ ጊዜያት የሚደርሰው ዛቻ፣ እስራትና አስገድዶ መሰወር ለምርጫው በነጻነት ሽፋን ሊሰጡ በሚገባቸው የመገናኛ ብዙኃን ላይ የፍርሓት ደመና እንዲያጠላና በዚኽም ምክንያት ከእይታ ውጭ በጓዳ የሚከናወን ምርጫ ሊኾን መቻሉ ጥርጥር የለውምም ”ብለዋል።

ከዚኽ በመነሳት የምርጫ የጊዜ ሠሌዳው በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ለሕዝብ ይፋ ከመደረጉ አስቀድሞ ወይም ደግሞ እስከ ኅዳር ወር መጨረሻ ሳምንት ድረስ (ከሁለቱ በቀደመው) መንግሥት ሦስት ጉዳዮችን ተግባራዊ በማድረግ ለምርጫው ምቹ መደላድል እንዲፈጠር አሳስበዋል፡፡ 

በተጠቀሰው የጊዜ ሰሌዳ መንግሥት እነዚህን ተግባራት ሊፈጽም ካልቻለ ጉዳዩን በመመርመር በቀጣይ  እርምጃ እንወስዳለን፤ ለህዝብም ይፋ እናደርጋለን ሲሉ በማስጠንቀቅም ሦስቱን ነጥቦች ዘርዝረዋል፡፡

አንደኛው “ በአገራችን እየተካሄደ ያለው የእርስ በርስ ጦርነት በአስቸኳይ እንዲቆም፤ ለዚህም የምርጫ ጊዜ ሰሌዳ ወደ ተግባር ከመሸጋገሩ ቀደም ብሎ በተግባር የተረጋገጠ እርምጃ በመውሰድ ለምርጫ አመቺ ኹኔታ መፈጠሩን መንግሥት ግልጽ እንዲያደርግ ተዋጊ ኃይሎችም ይህንኑ እንዲያረጋግጡና ሕዝብም ይህንኑ እንዲመሰክር ” አበክሮ አሳስቧል።

ሁለተኛው በየእስር ቤቱ ያለ ፍርድ ታጉረው ይገኛሉ ያላቸውና የፍርድ ሂደታቸው ሆን ተብሎ እየተራዘመ ያለው የፖለቲካ እስረኞች እንዲፈቱ እና በምርጫ ሂደቱ በነፃነት እንዲሳተፉ ጠይቋል።

በመጨረሻም  “  በየእስር ቤቱ ታጉረው የሚገኙ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈቱና በነጻነት እንዲዘግቡ ብሎም ሕዝብ ግብር እየከፈለ ያቋቋማቸው በመንግሥት ቁጥጥር ስር  ያሉ መገናኛ ብዙኃን ከሥርዓት አገልጋይነትና ግለሰብ አወዳሽነት ወጥተው የተቃዋሚውንም ድምጽ እንዲያሰሙ፣ ለምርጫውም ተገቢውን ሽፋን እንዲሰጡ እንዲደረግ በጥብቅ በማሰሰብ ” መግለጫውን ቋጭቷል።

(አዲስ ማለዳ)

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር የተዘጋጀው የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል ስቴት ኤግዘቢሽን ተከፈተ

በኢትዮጵያ ሪል ስቴት አልሚዎች ማህበር አዘጋጅነት የመጀመሪያው አህጉራዊ የሪል...

በሊባኖስ እና በእሰራኤል የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ተራዘመ

ትራምፕ በሊባኖስ እና በእሰራኤል መካከል የተደረሰው የተኩስ አቁም በሦስት...

ከ 50 ሚሊዮን በላይ መራጮች በማንዋልና በዲጂታል ተመዝግበዋል

ከየካቲት 28_መጋቢት 28 የመራጮች ምዝገባ ሲካሄድ እንደነበር ይታወቃል። በተለያዩ ጉዳዮች...

በኦሮሚያ ክልል የ4.5 ሚሊዮን ዶላር የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ፕሮጀክት ይፋ ተደረገ

ፈያ ኢንተግሬትድ ዴቬሎፕመንት ኦርጋናይዜሽን በኦሮሚያ ክልል የሚከሰቱ የበሽታ ወረርሽኞችን...