ሳሙኤል የተሻወርቅ
“ትበላለህ ግን አትጠግብም” ነበር ያለችው ሴትየዋ። መቸም እንዲህ ዐይነቱ በሽታ አይጣል ነው። ገፈታቸው ካንዲት እንጀራ በላይ ያስተናግድ ይመስል ያለ ልክ ያግበሰብሱና በአደባባይ መትፋት እና መተፋትን ባህል አደረጉት። በመጨረሻም እነሆ በልተው የማይጠግቡ ፣ ጠጥተውም የማይረኩ ጉዶች በዚህች ታሪካዊ ምድር ላይ ተከስተዋል።
በርግጥም በሃገራችን መንግስታዊ ሌብነት አዲስ ክስተት አይደለም። ርግጥ ነው፣ በኢትዮጵያችን መንግሥታዊ ሌብነት ዛሬ የመጣ እንግዳ ክስተት አይደለም። የሩቁን እንኳ ትተን፣ ከዐፄ ኃይለሥላሴ ዘመን ጀምሮ ያለውን ብንመለከት፣ የንጉሠ-ነገሥቱን የረቀቀ ስግብግብነት ብቻ ሳይሆን፤ ጫፍ-የረገጠ የዘረፋ “ታሪክ”ንም በስፋት ለመዳሰስ የመረጃም የማስረጃም ችግር አይኖርም፡፡ (ይህን በተመለከተ ወደፊት የምመመለስበት መሆኑን ለማስታወስ እወዳለሁ፡፡)
በአዛውንቱ ንጉሥ የተተካው የደርግ ሥርዐትንም በወፍ-በረር ብንቃኘው ከሙስና እና ከአስተዳደራዊ ብልሹነት ነፃ እንዳልነበረ አያሌ ማሳያዎችን መጠቀስ አይቸግርም፡፡ ጉቦም ነበር። ጉቦው ከጥሬ ስጋና ከውስኪ ግን አያልፍም እንጂ፡፡
ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ሰራዊታቸውን በትነው ሊኮበልሉ ሰዓታት በቀራቸው ጊዜ እንኳ፣ ለጁቡቲ መንግሥት በዶላር ሲሸጥ የቆየው የጫት ገቢን፣ ተተኪዎቹ ተከታትለው እንዲያስከፍሉ ሰነዶችን ለመስጠት ያለማቅማማታቸው በበጎ የሚጠቀስ ታሪካቸው ነው፡፡ በግሌም፣ በዓለም ታሪክ አገር ለቆ ሲጠፋ፣ የአገር ገንዘብ የመለሰ መሪ ከመንጌ ሌላ ስለመኖሩ፣ አለመስማቴን ለመመስከር እወዳለሁ፡፡
በሟቹ መለስ ዜናዊ “ሌብነት ሥራ” እንደሆነ በአደባባይ መነገሩ ሰፊውን ህዝብ ያለማሰደንገጡን ያሰተውሏል። ፋይል በእግር ሳይሆን በእጅ ብቻ የመሄዱን ጉድ ግን ጠቅላዩ ባረዱን ግዜ ደነገጥን። ድንጋጤ የመጣው ምስጢሩ አደባባይ በመሰጣቱ እንጂ በእጅ የመሄዱ ጉዳይ እንደ ባህል ከዜጋው ጋር መቆራኘቱ እንግዳ አይደለም።
እነሆ እኔም የስንክሳሩን ሰበዝ አሃዱ ብዪ መቁጠር ከመጀመሬ በፊት ቀድሞ ካነበብኳት አንዲት አፈ-ታሪክ ልጀምር፡፡
ሞትን አጥብቆ የሚፈራ አንድ ሰውዬ ነበር፡፡ ከዕለታት አንድ ቀንም ‹ሞት ወደሌለበት አገር እሄዳለሁ› ብሎ ወዳጅ-ዘመዶቹን ተሰናብቶ መንገድ ጀመረ፡፡ ያችን የህልም አገር ፍለጋም እጅግ በጣም ርቆ ተጓዘ፡፡ አንድ ስፍራ ሲደርስ፣ ሰው ሞቶ ሲለቀስ ገጠመውና ‹ቼ ፈረሴ› እያለ ሽምጥ ጋለበ። እንዲህ እያለም በጣም ብዙ ማሰነ፡፡
በመጨረሻም ሰው ከሞተ በኋላ ሬሳውን ከመቅበር ይልቅ፣ ለአሞራ ሲሳይ የሚዳረግበት የምድር ዳርቻ ደረሰ፡፡ ይኼኔም አንዲት ዛፍ ሥር አረፍ ብሎ ሲያሰላስል፣ ወደ አገሩ መመለስ በማይችልበት ደረጃ ርቆ መጓዙ ገባው፡፡ ለዘመድ-ወዳጆቹም እንዲህ ሲል መልእክት ላከ፡- ‹‹ጎበዝ ከዚህም የከፋ አለና አገርህን አትልቀቅ!›› ባህል ከለምድ ይቀዳል። ነውራቱንም ቢሆነ እንደዋዛ እየለመድነው ሰንሄድ ባህል እናደርገዋለን።
የዚህ መጣጥፍ ገፊ-ምክንያት ‹በምሬት አገር ከመልቀቅ ይልቅ መፍትሄው ላይ መረባረብ ይበጃል› ከሚል ብርቱ እሳቤ መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ፡፡
‹ኢትዮጵያን የሚጠብቅ አያንቀላፋም ፤ ኢትዬጵያ እጆቻን ወደ እግዚሀብሔር ታነሳለች እንዲል ቃሉ አገራችን እየተመራች ያለችውም በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ ሳይሆን፣ በሰማዩ አምላክ ነው› ብዬ በጽኑ አምናለሁ፡፡ መሪዉ በሌቦች መከበባቸዉ ለዚህች ሃገር እድገት ጠንቅ ይሁኑ እንጂ መሽቶ አይቀርም።
አዎ፣ እግዚአብሔር ቢዘገይም፣ ማንም አይቀድመውም፡፡ በአገራችን ኀጢያት አንደ ደም ቢቀላም፤ አንደ በረዶ የመንጣቱን አይቀሬነት የሰናፍጭ ቅንጣት ያህል አልጠረጥርም፡፡ ሌባና ዘረኛ ባለሥልጣናትም ሆኑ የጨረባ ባለሀብቶች የዘሩትን አጭደው፣ እጃቸው ላይ ካቴና የሚገባበት ቀን እንደሚመጣም አምናለሁ፡፡
አያሌው ጎበዜን ሳስበው …
ዛሬ አምባሳደር ናቸው። አያሌው ጎበዜ የዐማራ ክልል ፕሬዚዳንት በነበሩት ዘመን፣ እንደስማቸው ‹እውነትም ጎበዜ¡› ያሰኛቸውን ጀብዱ ፈጽመዋል፡፡
ነገሩ እንዲህ ነው፣ አንድ ጀርመናዊ ኢንጅነር ብዙዎችን ጉድ ያሰኘ ቪላ በዱባይ ላይ መገንባቱ የተከታተሉ የጀርመን ሚዲያዎች በስፋት ዘግቡ፡፡ ይህ ፓላስ ከተገነባ በኋላ፣ 3 ሚሊየን ዶላር ዋጋ ወጥቶለት ለገበያ ቀረበ፡፡ “ዘ ይትገረም ሻሸመኔ” ያሰኘው ጉድ ይህ አይደለም። ‹የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት ቪላውን ለመግዛት ዱባይ ሊመጡ ነው› የሚለው ተከታይ ዜና እንጂ።
“VOX” የተባለው የጀርመን ቴሌቭዥን ጣቢያም ‹ፕሬዚዳንቱ ይመጣሉ› ከተባለበት ቀን አስቀድሞ፣ ጋዜጠኞቹን ወደ ዱባይ ልኮ ካሜራዎቻቸውን ደቅነው እንዲጠብቁ አደረገ፡፡ በተባለው ቀንም ሰውዬው መጡ፡፡ የቪላው ገዢ ግን የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት አልነበሩም። የዐማራ ክልል ፕሬዚዳንት አያሌው ጎበዜ እንጂ፡፡ የኩሪፍቱ ሪዞርት ባለቤት አቶ ታዲዬስ በለጠም አብረዋቸው ነበሩ። ለምን አብረው እንደሄዱ የሚያውቁት ሁለቱ ብቻ ናቸዉ።
የጀርመን ጋዜጠኞች ወደ አያሌው ጎበዜ ቀረብ አሉና “እንዴት ከአንድ ድሃ አገር እንደዚህ ዐይነት ውድ ቤት ሊገዙ መጡ? ገንዘቡንስ ከየት አመጡ?” የሚሉ ጥያቄዎችን አከታተሉባቸው፡፡ ባልጠበቁት አጋጣሚ የተደናገጡት አቶ አያሌው ጎበዜም ዐይናቸውን በጨው አጥበው፡- “የመጣሁት ቤቱን ልገዛ አይደለም፡፡ አገራችን በፍጥነት እያደገች ስለሆነ፣ ወደፊት ምን መግዛት እንደምንችል ጥናት ልናደርግ ነው፣” ብለው ለማሰቀየስ ሞከሩ፡፡
ይሄ ጥያቄና መልስ በዝነኛው የጀርመኑ “VOX ቴሌቭዥን” በቀጥታ የተላለፈ ሰለነበር የማይክዱት ሃቅ ነው። እነ ጌታቸው አሰፋ ከዚህ ከፍ ባለ ዘረፋ ተጠምደው ስለነበረ ሁኔታውን በደንብ የተከታተሉት አይመስለኝም፡፡ የዐማራ ክልል ጠርናፊዎች በረከት ስምኦን እና ዐዲሱ ለገሠም፣ ጊዜያቸውን ያባከኑት በዐማራ ክልል የትግራይ እንደራሴ ለመሆን ሲጋጋጡ ስለነበረ፣ የሕዝብ ሃበት መመዝበሩን ከቁብ አልቆጠሩትም፡፡ ያሁኖቹም ቢሆኑ ‹‹እከክ ከያዘው፣ እከክ የተጋባበት ባሰበት›› ዐይነት መሆናቸውን ከለውጡ ጀምሮ ስንታዘበው የቆየ ጥሬ ሃቅ ነው፡፡ በተለይ የደቡብ፣ የአፋር፣ የኦሮሚያ እና የዐማራ ክልሎቹን ዝርፊያ ፈጣሪ በዐደባባይ እንደሚያጋልጣቸው አልጠራጠርም፡፡
የሱማሌ ክልል አመራርም ለብሔራዊ ደህንነት ከራዳር ውጪ ቢመስልም በእጄ የገቡ መረጃዎችን ተንተርሼ ብዙ የማወጋቸው ጉዳዮች አሉ። ባናቱ ላይ ‹‹ጠቅላይ ሚንስቴሩ በገባኦን ልጆች ተከብበዋል›› በሚል ርዕስ ያሰናዳሁትን የባለስልጣናቱን ገበና በጥርዝ አስነብባችኋለሁ፡፡
የትግራዮቹን የዘለልኳቸው ዘንግቼአቸው አይደለም፡፡ ለሌቦቹ የጡት አባት መሆናቸው በዐደባባይ ስለሚታወቅ፣ ከማደክማችሁ ብዬ ነው፡፡
ኦልማን በጨረፍታ…
“ኦሮሚያ ልማት ማኀበር (ኦልማ)” ከክልሉ ነጋዴዎች ጀምሮ፣ የድርጅት አባላት፣ የመንግሥት ሠራተኞች፣ ነዋሪዎች እና ደሃ ገበሬዎች መዋጮ ነው በግሩ የቆመው። ከአላማ አንጻር የሚመሰገን ተግባር ነው፡፡ ችግሩ ያለው በልማት ማኀበሩ ስም የሚዋጣው ገንዘብ የትኛው ቤርሙዳ ውጦ እንደሚያስቀረው ከዲያብሎስ በቀር የሚውቅ አለመኖሩ ነው፡፡ ከበዙት ዘረፋዎች ውስጥም ሁለቱን ለማሳያ እጠቅሳለሁ፡፡
በአዲስ አበባ የከተመው “ጄኔቫ ግሎባል” የተባለው የውጭ እርዳታ ተቋም በአንድ ወቅት አዘጋጅቶት በነበረው የገጠር የትምህርት አሰጣጥ ፕሮግራም ላይ የተፈጸመውን አሻጥር እናውሳው፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፣ ጄኔቫ ግሎባል በአገሪቱ በተለያዩ ችግሮች ትምህርት ቤት ሳይገቡ እድሜያቸው ያለፉ ታዳጊ ወጣቶች የመማር እድል ማግኘት የሚችሉበትን የባጀት እርዳታ ይመድባል፡፡ የእድሉ ተጠቃሚ ከሆኑት ክልሎች ደግሞ አንዱ ኦሮሚያ ነው። ይሁንና፣ ኦሮሚያን ከጀርባ ይዘውር የነበረው ሕወሓት፣ ለክልሉ ባለሥልጣናት ባጀቱን ‹አንቀበልም› ብለው እንዲመልሱ ቀጭን ትእዛዝ ይሰጣል፡፡ እነሱም የተባሉትን ያደርጋሉ።
ጌታዬ፣ አስቂኙ ቴያትር የሚጀምረው ከዚህ በኋላ ነው፡፡ ኦሮሚያ “አልፈልግም” ያለው የእርዳታው በጀት፣ በብርሃን ፍጥነት ወደ ትግራይ ክልል እንዲዘዋወር ይደርጋልና።
የሆነው ሆኖ ነገሩ ሲደጋገም፣ የጄኔቫ ግሎባል ኃላፊዎች ጉዳዩ እያሳሰባቸው ይሄዳል፡፡ በዚህ መሃል ነው፣ ከኃላፊዎቹ አንዱ ወዳጄ ስለነበረ በአጋጣሚ ክስተቱን ያነሳልኝ፡፡ በድርጊቱ በጣም ባዝንም፣ መፍትሄ ለመፈለግ ተስማምተን ተለያየን።
ከኖክ ነዳጅ ማደያ ዋና ሥራ-አስኪያጅ አቶ ታደሰ ጥላሁን ጋር ስለምንቀራረብ፣ ከወቅቱ የክልሉ ፕሬዚዳንት ለማ መገርሳ ጋር ቀጠሮ እንዲይዙልኝ ጠየኳቸው፡፡ እሳቸውም፣ በዚያው ሰሞን፣ ከፕሬዚዳንቱ ጋር አገናኝተውኝ እየተፈጸመ ያለውን ደባ አጫወትኳቸው፡፡ ችግሩ በአጭር ጊዜ ተፈትቶ አጥጋቢ ሥራ ለመሥራት ተቻለ፡፡ ኦቦ ለማን ጌታ ባሉበት ይባርካቸውና!
“ነገርን ነገር ያነሳዋል” እንዲሉ፤ ወዳጄ አቶ ታደሰ ጥላሁንን ካነሳን አይቀር፣ አንድ አስገራሚ ድርጊትን ሳልጠቅስ ማለፉ አይቻለኝም፡፡ እንደሚታወቀው አቶ ታደሰ ከኖክ ዋና ሥራ-አስኪያጅነታቸው ባሻገር፤ ባለድርሻም (Shareholder) ናቸው፡፡ (ለጠቅላላ እውቀት፣ ኖክን የመሰረቱት ሼኽ አላሙዲ፣ አቶ አብነት ገ/መስቀል እና አቶ ታደሰ ጥላሁን ናቸው፡፡)
አቶ ታደሰ ጥላሁን የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ አባልም ናቸው፡፡ እነዚህን እውነታዎች ይዘህ ደግሞ፣ ‹ለአየር መንገዱ ነዳጅ የሚያቀርበው ማነው?› ብለህ ጠይቅ፡፡
ሃሃሃ… ጋሽ ታዴ በሥራ-አስኪያጅነትም፣ በባለቤትነትም የሚያስተዳድሩት ኖክ ኩባንያ ነው፡፡ አያስቅም! የኢትዮጵያ አየር መንገድ እንደሆነ የማያሰማን ጉድ የለም?! “Conflict of interest” የቢዝነስ ትምህርት ‹ሀሁ…› መሆኑ ግን ጠፍቶት አይደለም፡፡ እያልኩህ ያለው፣ ‹የድርጅት ጥቅምን የማስጠበቅ ቀመርን ሰልቅጦ፣ ወደ Self-dealing ተሸጋግሯል› ነውና፡፡
በነገራችን ላይ፣ አቶ ታደሰን ሥልጣን በመደራረብ የሚበልጧቸው ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም ብቻ ይመስሉኛል፡፡ ከላይ ከጠቀስናቸው ኃላፊነቶች በተጨማሪ፤ የኢትዮጵያ የነዳጅ ድርጅቶች ፕሬዚዳንት፣ የአፍሪካ የነዳጅ አጣሪዎች እና አከፋፋይ ድርጅቶች የቦርድ አባልም ናቸው፡፡ የኢትዬጵያ ሰራተኞች ማህበር ፕሬዝደንትም ነበሩ፡፡ የኢትዬጵያ የንግድ ምክር ቤት (chamber of commerce) የክብር በጎ ፈቃድ አምባሳደር ሹመትን ጨምሮላቸዋል፡፡
እንግዲህ፣ የአቶ ታደሰ ኖክ፣ በአቶ ተወልደ ገ/ማርያም ዘመን በመቶ ሚሊዮኖች በሚቆጠር ገንዘብ ለኢትዮጵያ አቬሽን የነዳጅ ማጠራቀሚያ ማስፋፊያ ለመገንባት በይፋ የተፈራረመ “ጀግና” ድርጅት መሆኑ ሲገለጥልህ፣ ‹አዲዮስ Conflict of interest› ብትል ማን ይቃወምሃል?!
1. በመንጬ የተላፈው የሚስተር ጉንተር ችሮታ
ጀርመናዊው ሚ/ር ጉንተር ብሬማን ለአንድ ጥናት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ፣ አምቦ ላይ ከተመ፡፡ ፈረንጁ በከተማይቷ መኖር ከጀመረ ጊዜ አንስቶ አንድ ተማሪ ደብተሮቹን ይዞ ጠዋት በሩጫ ሲሄድ እና ከሰዓት በሩጫ ሲመለስ ያያል፡፡ ደጋግሞ ሲታዘብ ከቆየ በኋላም፣ አንድ ቀን ያስጠራውና ሁልጊዜ ለምን እየሮጠ አንደሚሄድና እንደሚመለስ በአስተርጓሚ ይጠይቀዋል፡፡ ልጁም የሚሮጠው ጠዋት ትምህርት ቤት እንዳይረፍድበት፣ ሲመለስ ደግሞ ቤተሰቦቹን ሥራ አግዞ ወደ ጥናት ለመግባት እንዳይመሽበት መሆኑን ይነግረዋል፡፡ ችግሩን የተረዳው ሚ/ር ጉንተር ጥራቱን የጠበቀ ት/ቤት በጉደር ከተማ አስገንብቶ አስረከበ፡፡ ትምህርት ቤቱም በሚ/ር ጉንትር ስም ተሰየመ፡፡
የኦሮሚያ ልማት ማኀበር ‹እኔ ነኝ የማስተዳድረው› በማለት ትምህርት ቤቱን ከሚ/ር ጉንተር ተረክቦ ወሰደው፡፡ በዚህ አላበቃም። የወቅቱ የማኀበሩ ዳይሬክተር ዶ/ር ሙሉጌታ ደበበ፣ ለሚ/ር ጉንተር ባለቤትን ስልክ ደውሎ፣ “ለትምህርት ቤቱ ለሥራ ማስኬጃ ገንዘብ ያስፈልገናልና፤ በኦሮሞ ሕዝብ ስም ለመነሻ ያህል 150 ሺሕ ዩሮ እንድትረዱን እለምናችኋለሁ?” ሲል ተማጸነ፡፡ መልካሙዋ ሴትም፤ የባንክ ቁጥራችሁን ብላ ጠየቀች፤ ዶ/ር ሙሉጌታ ደበበ የግል ባንክ ቁጥራቸው ላኩ፡፡ በልማት ማኀበር ስም ለተለገሰው ገንዘብ፣ በግል አካውንት የገባበት በማስረጃ ይገኛል።
የጉንተሩ ት/ቤት ሥራውን በመጀመሩ፣ የአዳማው አዳሪ ት/ቤት መስፋፍያ ቁጥር ሁለት ተባለና ጉደር ወደ ተከፈተው አዳሪ ት/ቤት ተዛወረ፡፡ የ2ኛ ደረጃ ተማሪዎችንም ለጥቂት ዐመታት ሲያስተምር ቆየ። ከዚያ ግንችግር መጣ። የአምቦ ነዋሪዎች ‹የኦሮሚያ ልማት ማኀበር እያመጣ የሚያስተምረው የኦሕዴድ ካድሬ ልጆችንና ቤተሰቦችን ነው፡፡ ለእኛ ልጆች ምንም አልጠቀመም፡፡ ለቃችሁ ውጡልን?!” ብለው አመጹ፡፡
በዚህ የተረበሹት የማኀበሩ መሪዎችም ካድሬዎችን ጉድር ድረስ ልከው ሕዝቡን ለማሳመን ሞክረው ስላልተሳካላቸው፣ ት/ቤቱን ለቀው ወጡ፡፡ በመጨረሻም የአካባቢው ት/ም ቢሮ ተረከበው፡፡ ነገር ግን፣ ማኀበሩ በቋጠረው ቂም ይሁን ወይም በሌላ ምክንያት ት/ቤቱን ዞር ብሎ ለማየት ባለመፍቀዱ፣ ዛሬ በሚያሳዝን ሁኔታ ላይ መገኘቱን ስናገር ሀዘን በተጫነው ስሜት ነው፡፡
የልማት ማኀበሩ ቦርድ ዋና ሊቀ-መንበር አባዱላ ገመዳ፣ ምክትል ደግሞ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ናቸው፡፡ ከንቲባዋ፣ ዶ/ር ሙሉጌታ በግል አካውንቱ የወደሰውን 150 ሺሕ ዩሮ እንዲመልስ አንዲያደርጉ ተጠየቁ። አዳነች አቤቤ ዶክተሩን አስጠርተው ገንዘቡን እንዲመልስ አሳሰቡት፡፡ ጉድና ጅራት ከበስተኋላ ነውና ይህቺን ልብ በሉ። ዶ/ር ሙሉጌታ ደበበ የወሰደው 150 ሺሕ ዩሮ ሲሆን የመለሰው ግን 150 ሺሕ ብር ነበር። ከዚያም ‹ፋይሉ ተዘጋ›፡፡ መቼም፣ ጉዳዩን በዚህ የቋጩት የቦርዱ ኃላፊዎች የዘረፋው ተካፋይ ካልሆኑ በስተቀር፤ በድንጋይ ዳቦ ዘመን እንኳ 150 ሺ ዩሮ፣ በ150 ሺሕ ብር ተመንዝሮ እንደማያውቅ ጠፍቷቸው አይደለም፡፡
የዚህች ምስኪን አገር ስላቅ ማለቂያ የለውምና፤ እንቀጥል፡፡
2. ተጠያቂነት ደህና ሰንብት
ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ከኦሮሚያ ማኀበር ጀምሮ የነበረው ሹፌራቸው አቶ ግርማ ይባላል፡፡ ይህ ሰዉ ገቢዎችም፣ ጠቅላይ ዐቃቢ-ሕግም አብሯቸው ዘልቋል፡፡ ዛሬም በከንቲባ ቢሯቸው እያገለገለ ነው፡፡ በርግጥ፣ ለታማኝነቱም፣ ለጥንቃቄውም አንድ ሹፌር መጠቀማቸው ክፋት የለውም፡፡ ክፋት የሚሆነው ደሞዝ የሚከፈለው ከከንቲባ ጽፈት ቤት ሳይሆን፤ ከኦሮሚያ ልማት ድርጅት ካዝና መሆኑ ነው፡፡ ይህን ተራ የሚመስል፣ ነገር ግን ትልቅ ተጠያቂነት የሚያስነሳ አሠራር በሰማሁ ጊዜ፣ በለሆሳስ ‹Transparency› እና ‹Accountability› ነፍስ ይማር ማለቴን አስታውሳለሁ፡፡
የኦሮሚያ ልማት ማኀበርን የተመለከተ ወጋችንን ከመቋጨታችን በፊት፣ ለምዝበራው ማሳያ አንድ እንመርቅ፡፡ “ማኀበሩ ብዙ የባንክ ቁጥሮች ስላሉት፣ አላስፈላጊ ባለመሆኑ ይዘጉ፡፡ የተወሰነ የባንክ አካውንት ብቻ ይበቃዋል፣” ተብሎ በመወሰኑ፣ አብዛኛዎቹ የባንክ ሂሳቦች ተዘጉ፡፡ ይሁንና፣ እንደተዘጉ ሪፖርት የተደረገባቸው ሁለት የባንክ ቁጥሮች በድብቅ ሳይዘጉ እንዲቀጥሉ ተደረገ፡፡ እነዚህን አካውንት የሚያውቁት ደግሞ የቦርዱ ኃላፊዎች ብቻ ናቸው፡፡ ፋይናንስ ክፍሉ እንኳ በጭራሽ አያውቅም፡፡ በኋላ፣ በወሬ-ወሬ የሰሙት የፋይናንስ ኃላፊ ተደናገጠው በራሳቸው ፈቃድ ሥራቸውን መልቀቃቸውን ሰምቻለሁ፡፡
“ቀጣዩዋ ጠቅላይ ሚንስትር ሴት ትሆናለች”
ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ልማት ማኀበሩን እንደ መሰላል ተንጠላጥውና በተለያዩ የሥልጣን እርከን አልፈው ለአዲስ አበባ ከንቲባነት በቅተዋል፡፡ ከዚያም አዝማሪው እንዳለው አሸብርቀዋል። የሰው ልጅ ፍላጎት ወሰን-የለሽ ነውና፤ ከዚህም ከፍ ለማለት ቢመኙ አይደንቅም፡፡
ነገሩን አጀንዳ እንዳደርገው ያስገደደኝ፣ ከሰሞኑ በነብያቸው የተነገረው ትንቢት ነው።
በእሳቸው ቤት ተሰባስበው በሚጸልዩ የዘመኑ ነብያት ትንቢት ነግረዋቸዋል። (ከቅዱስ መንፈስ ይሁን ከርኩስ መንፈስ ለይቼ ባላውቅም) እሳቸው ግን አሜን ብለው ተቀብለው “የመጀመሪያዋ ሴት ጠቅላይ ሚንስትር እኔ አሆናለሁ፣” የሚል ብርቱ የሰልጣን ጉምዥት እንዳደረባቸው ከጸላዩቹ መሀል አንዱ ሹክ ብሎኛል፡፡
በበኩሌ፣ ሥልጣን በዘር፣ በሃይማኖት፣ በጉልበት የሚዘውር ቢመስለንም፣ ‹ከአንድ ከአምላክ የሚሰጥ ነው› ብዬ ስለማምን፤ ለእሳቸውም ፈጣሪ ከፈቀደላቸው “አሜን!” ከማለት ውጪ የምለው የለኝም፡፡
ባይሆን፣ ከጠቅላይነቱ በፊት፣ በአዲስ አበባ በየመንገዱ ሰው እና እንስሳት እየገቡ የሚሰበርበትን ጉድጓድና ትቦ ቢያስደፍኑ፤ በየሰፈሩ “ብሬከር” እየተባለ ከመኪና በተጨማሪ፣ አዛውንትና አካለ-ስንኩላን ማለፍ እንዳይችሉት ተደርጎ የተሠራውን መሰናክል አስፈርሰው በሕጉ መሰረት ቢያስገነቡ፤ ሺሻና ሀሺሽ ቤቶችን ጨምሮ፣ በ“ማሳጅ ቤት” ስም በየመንደሩ ተስፋፍተው ህጻናት እተበላሹ ያሉባቸውን የወሲብ መቸርቸሪያ ቤቶች ቢያዘጉ… ለአራት ኪሎ መንደርደሪያ እንደሚሆናቸው ወንድማዊ ምክሬን እለግሳለሁ፡፡
መንፈሳዊ ትንቢቱ ከሙዚቃ ቃና ጋር የመዋሀዱ ተቃርኖ ግን ብዙ ያስብላል። መድመቁ እና ማሸብረቁ አንድ ነገር ነው። ጉዳዩ ከሃገር አልፎ ወደ አፍሪካ አህጉር የመሻገሩ ነገር እቺ ጎንበስ ጎንበስ ምን ለማንሳት ማሰኘቱ አልቀረም። እርግጥ እንከን አልባ አመራር ሊኖር አይችልም። የአንድ መሪ ብቃት የሚመዘነው በአዝማሪዎች ሙገሳ እና ውደሳ ሳይሆን በህዝቡ ትንፋሽ ነው። ወደ መሬቱ ቀረብ የሚል መሪ የሰፊውን ህዝብ የልብ ትርታ ያደምጣል። ዝቅ ፣ ጎንበስ በሉ ለማለት እንጂ ጥሬ ቃሉን እንዳልሆነ የሚገባው ይገባዋል።
የመሬትን ነገር ሳነሳ ግን አንድ የሚታወሰኝ ነገር አለ። ለሚ ኩራ። በወ/ሮ አዳነች አቤቤ ዘመን ለአዲስ አበባ 11ኛው ክ/ከተማ ለሚኩራ ተፈጠረ። የክፍለ ከተማው የመሬት ልማትና አስተዳደር ጽፈት ቤት ሀላፊ ሆነው ተሹመው የነበሩት ወ/ሮ ሀቢባ ኡመር ነበሩ። በመገናኛ ብዙሃን እሰኪጋለጥ ድረስ በእነ ሀቢባ ህዝቡ ተበዘበዘ የሚለዉ ቃል አይገልጸውም። ወ/ሮ ሀቢባ ኡመር ዘረፋቸውን ከግለሰብ አልፈው የመንግሰት የልማት ተቋማትንም ለማድማት ሞክረዉ ነበር።
ከኢትዬጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ተጨማሪ የመኖሪያ ቤቶችን ለመስራት በለሚኩራ የተሰጣቸዉን ቦታ ሲጠይቁ ወ/ሮ ሀቢባ ቀለል አድርገው 300 ሚሊየን ብር ነበር የጠየቁት። በመርህ የማይደራደር አመራር ገጠመ እንጂ የድፍረቱ ጥግ ጣርያው ሰማይ ነበር።
በመጨረሻም እንዲህ ሆነ። ወ/ሮ ሀቢባ ኡመር በሙስና ተጠርጥረው ዘብጥያ ወረዱ የሚለዉ ዜና ገና ከኢቲቪ ሳይወርድ ከእስር ተለቀቁ። ሙስና የዋስትና መብት የማያሰጥ ወንጀል ነዉ ብለውን ነበር። ሾርት ሜሞሪ በሚባል ህመም የተመታ ህዝብ እንደሆነ ሰላመኑ ይቀልዱብናል።
ቀልዳቸዉ የማይጠገበው ከንቲባችን ወ/ሮ ሀቢባ ከአጋሮቻቸው ጋር ሆነዉ ከአገር አምልጠው እንደኮበለሉ በሚዲያ ሲናገሩ ሰማን። “አንቺው ታመጪው አንቺው ታሮጪው ፡፡” አሉ አበዉ። ወ/ሮ ሀቢባ ከለሚ ኩራ ሹመት በፊት ለአመታት በእስር ላይ የነበሩ በሙያው የተካኑ ሰዉ ነበሩ። የቅጥራቸው ምሰጢርም ከዚያ መስፈርት መሆኑ ይሆን?
ጉዱ ይቀጥላል…
