በሰሜን ምስራቅ ኬንያ ማንዴራ ካውንቲ ውስጥ ለበርካታ አስርት ዓመታት በንግድ፣ በቤት ሰራተኛነት፣ በግብርና እና ሞተር ሳይክል ታክሲ ስራ ተሰማርተው የሚኖሩ ከ300 በላይ የወላይታ ማህበረሰብ አባላት አካባቢውን ለቀው እንዲወጡ ተወሰነ።
ይህ ድንገተኛ ትዕዛዝ ባለፈው ጥር 11 ቀን 2018 ዓ.ም. በማህበረሰብ ተወካዮች የወጣ ሲሆን፣ በአንዳንድ የአካባቢው ተመራጭ መሪዎችም ድጋፍ አግኝቷል።
መሪዎቹ ለውሳኔው መነሻ ያደረጉት ዋነኛው ምክንያት ቡድኑ በማንዴራ እየተባባሰ ከመጣው የወንጀል ድርጊት ጋር ግንኙነት አለው የሚል የጸጥታ ስጋት ሲሆን፣ በተጨማሪም አብዛኞቹ የማህበረሰቡ አባላት ህጋዊ የመኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው “ሰነድ አልባ” መሆናቸውንና የማህበረሰቡ አኗኗር ከአካባቢው ነባር ባህልና ሞራል ጋር አይጣጣምም የሚሉ ምክንያቶችን ጠቅሰዋል።
ይሁን እንጂ የወላይታ ማህበረሰብ ተወካዮች የቀረበባቸውን የወንጀል ተሳትፎ ውንጀላ ሙሉ በሙሉ ውድቅ አድርገዋል።
በኬንያ ማንዴራ ለረጅም ጊዜ የኖሩት እነዚህ ኢትዮጵያውያን ለካውንቲው ኢኮኖሚ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ መሆኑን በመጥቀስ፣ ውሳኔው ያለ በቂ ቅድመ ዝግጅት በድንገት መውጣቱ በርካታ ቤተሰቦችን ለከፋ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግር እንደሚዳርግ ገልጸዋል።
በኢትዮጵያ በግብርና ስራቸው የሚታወቁት የወላይታ ተወላጆች፣ በአሁኑ ወቅት ባለው ኢኮኖሚያዊ ጫና ምክንያት በርካታ ወጣቶቻቸው ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደው በጉልበት ስራ ለመተዳደር እንደሚገደዱም ይነገራል።
ይህ የማስወጣት እርምጃ በኢትዮጵያ እና በኬንያ ድንበር አካባቢ ለዘመናት በቆየው ማህበራዊ ግንኙነት ላይ ጥላ ሊያጠላ እንደሚችል ከፍተኛ ስጋት ተፈጥሯል። ጉዳዩ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾችን ትኩረት የሳበ ሲሆን፣ ሁኔታው ወደ ከፋ ግጭት ወይም የሰብአዊ መብት ጥሰት እንዳያመራ በቅርበት እየተከታተሉት እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል።
