ተስፋዬ እሸቱ(ረ/ፕሮፌሰር ) ከሳንፍራንሲስኮ፣ ካሊፎርንያ (አሜሪካ)
በአሜሪካ ሰው የሚባለው ትልቁ ፍጥረት ወደ ስራ ሲለወጥ አየሁ፤ ስራ ይሰራል አይገልጸውም። እኔ እንዳየሁት ነዋሪዎቹ ከሰኞ እስከ አርብ መዝናናት የሚባለውን ነገር አያውቁትም። በእነዚህ ቀናት ምናልባትም ካገኙህ ለሰላምታ ብቻ ነው። አርብ ከሰአት በኋላ አመሻሹ ላይ ግን ማበድ ይጀምራሉ። ተገቢ ነው። ሳምንቱን ወደ ስራ ተቀይረው አርብና ቅዳሜ ቢያብዱ የተገባ ነው።
ሳምንቱን በሙሉ ወገቡን ይዞ እንደሰራ ሰው እኔም አርብ ከሰአትን ወድጃታለሁ፤ ፈላጊዬ ይበዛላ!
ታዲያ ከለታት አንድ ቀን አርብ ከሰአት በኋላ እንዲህ ሆነ። በየአቅጣጫው ተደወለልኝ። አንዱ ቡድን ቀናው። ይዘውኝ ወደ ሳንፍራንሲስኮ ከተማ ሄዱ፤ ከሳንሆዜ 40 ደቂቃ የመኪና ጉዞ በኋላ ሳንፍራንሲስኮ ደረስን።
እኔ እንዳየሁት ከተማው አርብ ከሰአት በኋላ ያብዳል። የሚበላው፣ የሚጠጣው፤ የጎዳና ላይ ጨዎታው፣ ሰርከሱ፣ ሙዚቃው፣ ትርኢቱ፤ ቤተሰቡን ይዞ የሚያብደው፣ ካለምት የሚንቀሳቀሰው ዳንሰኛ፣ አይንህ ላይ ምግብ እየሰራ የሚሸጠው ምግበኛ፣ መጠጥ የሚቀዳው ብቻ አምላክ ይቁጠረው፤ ከተማው እያበደ ነው።
ከእብደቶች መካከል እንሆ አንዱን…
መንገድ ዳር ሰዎች ከበው የሆነ ትርኢት እያዩ ነበር። ተቀላቀልን። ትርኢቱ አለቀ። ተጨበጨበ።
“next”አሉ በጋራ።
“ተስፍሽ የአንተ ተራ ነው ሂድ” አሉኝ። ፈራ ተባ እያልኩ ተጠጋሁ።
“ታሪክህን ትነግረናለህ፤ እኛ ወደ ትያትር ቀይረነው እናሳይሀለን። ከወደድከው ትከፍላለህ” አለኝ።
“ትከፍላለህ?” ወደ ጎደኞቸ ዞርኩ። “no problem እኛ እንከፍለለን” አሉ
“ስምህን ንገረኝ”
“ተስፋዬ” አልኩት። ስሜ ሲለጠጥበት አየሁት። “ቴስ” ብዬ ስሜን ከረከምኩለት። በአዲሱ ስሜ ሲደሰት አየሁት። አምስት የሚጠጉ ተዋንያን ታሪኬን ሰምተው ወደ ትያትር ለመቀየር ማስታወሻ መያዝ ጀምረዋል።
ከየት እንደመጣሁ፣ ምን እንደሚያስደስተኝ፣ እንደሚያስከፋኝም ብቻ ብዙ ብዙ ነገር ተጠየኩ፤ መለስኩም። ጥያቄው እንዳለቀ የሰሙትን ታሪክ ወደ ትያትር ለመቀየር ተዋንያኑ መወያየት ጀመሩ። ከአፍታ ልምምድ በኋላ ታሪኬ ወደትያትር ተቀይሮ ለተሰበሰበው ታዳሚ ቀረበ። ተጨበጨበ። ከተዋንያኑ አንዱ፤”እንዴት ነው ወደዳችሁት” አለን። በጭብጨባ ገለጽንለት። በቲወሪ ብቻ የማውቀውን አንዱን የትርኢት አቀራረብ ዛሬ በተግባር በማየቴ ተደሰትኩ። አዲስ አበባ ቢሆን አንድ ትልቅ ሙክት የሚገዛ ዶላር ለትርኢት አቅራቢዎቹ ከፈልን፤ አይደለም ከፈሉልኝ።
“next” አለ ቅድም እኔን የጠየቀኝ። ሌላ ባለተራ ታሪኩን ተናገረ፤ በትያትር መልክ ታሪኩ ቀረበ። ተጨበጨበ። ከፈለ። ሌላ ባለታሪክ ቀጠለ።….
እኔና ጎደኞቸ ግን ወደሌላ ቦታ ተንቀሳቀስን። አሁንም እየተዟዟርኩ ባያኋቸው ጎዳናዎች፣ ፓርኮች ሰው እያበደ ነው። ትንሽ ከተማ ሲያብድ ሀገር ይሆናል እንዴ!? አበደች! አበድን። ሰው እንዴት መንገድ ላይ ያብዳል። ሰው እንዴት መንገድ ላይ ይጨሳል። ደስታ ብቻ። ፈገግታ ብቻ።
ለማበድ ገንዘቡን ሆጭ አድርጎ ይችን ትንሽ ከተማ የሚጎበኘው ከከተማው ህዝብ ቁጥርና ከስፋቷ ይበልጣል።
ለምሳሌ ያህል በእነሱ አቆጣጠር በ2024 ሳንፍራንሲስኮን ከሀያ ሶስት ሚሊዮን በላይ ቱሪስቶች ጎብኝተዋታል። መጎብኘት ብቻ አይደለም፣ ጎብኝዎቹ ከኪሳቸው ከዘጠኝ ቢሊዮን ዶላር በላይ አፍሰዋል። ካፈሰሱት ላይ በታክስ መልክ ከተማው ስድስት መቶ ሚሊዮን ዶላር አፍሷል።
በከተማው ሌላ የተለየ ነገር አላየሁበትም። ግን በየጎዳናው፣ በየፓርኩ አዳሜ እንዲያብድ የሚያስችል ወጥመድ አበጅተውለታል።ማለፍ አትችልም፤ እንድታብድ ያመቻቹሀል፤ ደስ እያለህ ታብዳለህ፤ ትከፍላለህ፤ አለቀ። ከብዙ ማበድ በኋላ ” ይሄ ከተማ ግን ተመልሶ ከተማ ይሆናል?” አልኳቸው። ” ዕሁድ ከሰአት እዚህ ብትመጣ ያየኸው እብደት ወደየቤቱ ይከተታል” አሉኝ። ማመን ስላልቻልኩ ዕሁድ ከሰአት በኋላ፣ አመሻሹ ላይ ያበድንበትን ቦታ ካላየሁ አልኳቸው፤ አመጡኝ።
ሌላ ከተማ፣ ሌላ መንገድ ነው።
“ፋራ ነው ብላችሁ ነው ሌላ ከተማ ይዛችሁኝ የመጣችሁት” ተናደድኩባቸው። እድሜ ለቴክኖሎጂ ስናብድ የተነሳናቸውን ፎቶ እየገላለጡ አሳዩኝ። እራሱ ከተማው ነው። አርብ ከሰአት ያበደ ከተማ እሁድ አደብ ገዝቷል። አርብ ሌላ፣ ቅዳሜ ሌላ። እሁድ የከተማውን ነዋሪ ለሰኞ ስራ እያመቻቸው ነበር።
እና ምን ለማለት ነው…..
የአለም ቱሪስት አገር አቆራርጦ ለጉብኝት የሚመጣው አንድም ከታካች የህይወት አዙሪት ለመውጣት ነው።
እናሳ….አዲስ በተገነቡ የአዲስ አበባ ፓርኮች በሳምንት አንዴ እብደት ግድ የሚል ይመስለኛል።
አዲስ አበባ በሳምንት አንዴ ማበድ አለባት።
በየፓርኮቻችን በሳምንት አንዴ ሰዓሊያን መንገዱንም በቀለም እንዲያቋሸሹት ይሁን። በቀለም ያሳብዱን። ገጣሚያን በተለመደው የአቀራረብ ስልት ሳይሆን፣ ተመልካችን በአሳተፈ መልኩ ይቀኙ። ድምጻዊያን ሙዚቃ ማቅረብ ሳይሆን ጎብኚውን ድምጻዊ ያድርጉት። ሌላም ሌላም።
ህጻናትን በሳምንት አንዲ እንዲስሉ፣ እንዲዘፍኑ፤ አይናችን ላይ እየተሰራ የሚበላ ምግብ እንዲከናወን መሆን አለበት የሚል ሀሳብ አለኝ።
በየፓርኩ፣ በተመረጡ መንገዶች የአገራችን ምግብ ይሸጥ፣ ዳንሳችን ይቸብቸብ፣ ጌጣችን ለገበያ ይዋል። ለምሳሌ ቱሪስቱን የተዘጋጀ ክትፎ አናቅርብለት። ክትፎ ሰርቶ እንዲበላ እናድርገው።
ከተለመደው የፓርኮቻችን የጉብኝት ስርዓት ላይ እብደት እንጨምርበት። ከተማ ያበደ ቀን ጎብኝን ትስባለህ። በከተማችን፣ በየፓርኮቻችን በሳምንት አንዴ እንደ አሜሪካኖቹ ሳይሆን እኛን የመሰለ እብደት ያስፈልገናል።
ያኔ የውጭ አገር ቱሪስት ጨርቄን ማቄን ሳይል አዲስ አበባ ይመጣል፤ ከቱሪዝም ዶላርም ይታፈሳል።
ስለይሄ በሳምንት አንዴ አዲስ አበባችን ማበድ አለባት!
መልካም ጊዜ
