በምስራቅ አፍሪካ ቀዳሚ መሆኑ የተነገረለትና በቀን 3ሺ የፖስ ማሽኖችን መገጣጠም የሚያስችል ፋብሪካ በኢትዮጵያ ተመርቆ በይፋ ሥራ ጀምሯል፡፡
በምረቃ መርሀ ግብሩ ላይ የተገኙት የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዶ/ር በለጠ ሞላ ባደረጉት ንግግር፤ እንደ ሀገር ዲጅታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አያሌ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናችውን ገልጸው፣ የፖስ ማሽኖችን መገጣጠም የሚችል ፋብሪካ ተገንብቶ ወደ ስራ መግባቱ እንደ ሀገር ዲጅታል ሥርዓትን ለመገንባት የሚደረገውን ጥረት የሚያግዝ ነው ብለዋል።
ፋብሪካው በቀን ከ3ሺ በላይ የፖስ ማሽኖችን መገጣጠም የሚችል ግዙፍ ፋብሪካ መሆኑን የገለጹት የሳንቲምፔይ ፋብሪካ መሥራችና ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ትንሳኤ ደስአለኝ በበኩላቸው፤ ፖስ ማሽኖቹ በሀገር ልጅ የሚገጣጠሙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህም ለበርካታ ዜጎች የስራ እድልን የሚፈጥርና ከሀገር ውስጥ ገበያም ባሻገር ለአፍሪካ ሀገራትም ገበያ ተደራሽ ያደርጋል ብለዋል።
