“በትግራይ እና ኤርትራ ህዝቦች መካከል እየተፈጠረ ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተጠናክሮ እንዲቀጥል እሰራለሁ” – ህወሓት

Date:

“ተመሳሳይ ግንኙነቶች ከሌሎች ጎረቤት ህዝቦች ጋር እንዲኖርም እጥራለሁ”

በትግራይ እና ኤርትራ ህዝቦች መካከል እየተፈጠረ ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት  ተጠናክሮ እንዲቀጥል” እንሰራለን ሲሉ በቅርቡ ህጋዊ ሰውነቱ በምርጫ ቦርድ የተሰረዘው የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ህወሃት) ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ገለፁ።

ደብረጺዮን፤ “ተመሳሳይ ግንኙነቶች ከሌሎች ጎረቤት ህዝቦች ጋር እንዲፈጸም ለማድረግ ትኩረት ሰጥተን አስፈላጊውን ጥረት እንደምናደርግ ልናረጋግጥ እንወዳለን” ብለዋል።

የህወሓት ሊመንበር ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ይህንን የተናገሩት የክልሉ ሰማዕታት ለ37ኛ ጊዜ ለማሰብ በሐውዜን ከተማ በተካሄደው ስነስርአት ላይ ባስተላለፉት መልዕክት ነው።

 “ህዝባችን ከሌሎች ህዝቦች ጋር የሚያጣላ ምንም ነገር የለውም” ሲሉ የተደመጡት ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) “ከአማራ፣ አፋር ኤርትራም ይሁን ሱዳን እንዲሁም ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች ጋር በሰላም መኖር፣ ከድህነት በመውጣት በልማት መኖር ነው የሚፈልገው” ሲሉ ገልጸዋል።

“ፓርቲያችን ህወሓት በአሁኑ ወቅት በትግራይ እና ኤርትራ ህዝቦች መካከል እየተፈጠረ ያለው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት  ተጠናክሮ እንዲቀጥል እና ተመሳሳይ ግንኙነቶች ከጎረቤት ህዝቦቹ ጋር እንዲፈጸም ለማድረግ አስፈላጊውን ጥረት እንደምናደርግ ልናረጋግጥ እንወዳለን” ብለዋል።

በሌላ በኩል የትግራይ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ ላለፉት አምስት አመታት ተለያይተው የቆዩት በዛላምበሳ የሚገኙ የኢትዮጵያ እና የኤርትራ መንደር ነዋሪዎች በድጋሚ መገናኘታቸውን ቢቢሲ በቪዲዮ አስደግፎ ባቀረበው ዘገባው አስታውቋል።

በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ ከመረብ ወንዝ ማዶና ባሻገር ያሉ ህዝቦች በተመሳሳይ መገናኘታቸውን ዘገባው አመላክቷል፡፡

ሊቀመንበሩ ደብረጺዮን በተጨማሪም በመልዕክታቸው “የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት በርካታ ጉዳዮች አልተፈጸሙ” ሲሉ በመግለጽ በአብነትም “የክልሉ ግዛታዊ አንድነት አልተከበረም፣ ከአንድ ሚሊየን በላይ የሚሆነውን የክልሉ ተፈናቃይ ወደ ቀየው አልተመለሰም” ሲሉ ጠቅሰዋል።

 “የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት በርካታ ጉዳዮች አልተፈጸሙም ብቻ ሳይሆን ስምምነቱ ጠቅልሎ የሚፈርስበት እንቅስቃሴዎች ከግዜ ወደ ግዜ እየተባባሰ እየሄደ ይገኛል” ሲሉም አሳስበዋል።

ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ለስምምነቱ አለመከበር “የብልጽግና መንግስት” እና “የክህደት ቡድን” ሲሉ የጠሩትን አካል ተጠያቂ አድርገዋል።

“ከሁለት አመት ከስምንት ወራት በላይ ያስቆጠረው የፕሪቶርያ ስምምነት እንዳይከበር ዋነኛ እንቅፋት ሁነው ያሉት የብልጽግና መንግስት እና “የክህደት ቡድን” መሆናቸውን የትግራይ ህዝብ ብቻ ሳይሆን ስምምነቱ እንዲፈረም አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት ያደረጉ አለምአቀፍ እና ቀጠናዊ ተቋማት መሪዎች” በደንብ ያውቃሉ ሲሉ ተደምጠዋል።

የህወሓቱ ሊቀመንበር በንግግራቸው “የብልጽግና መንግስት” ፓርቲያቸውን ለመክፈል እና ለመበተን ሰርቷል ሲሉ ኮንነዋል፣ በተጨማሪም “የክልሉን ህዝብ እርስ በርስ ለማጨፋጨፍ” እየሰራ ነው ሲሉ ተችተዋል።

“የብልጽግና መንግስት የፕሪቶርያውን ስምምነት እንደፈለገ ለመዘወር ያስችለው ዘንድ ፓርቲያችን ህወሓትን ለሁለት ለመክፈል እና ለመበተን፣ ህዝባችን እርስ በርሱ እንዲጨፋጨፍ ጥረት ሲያደርግ ነበር አሁንም እያደረገ ነው” ብለዋል።

“ይህንን ተልዕኮ እንዲፈጽምለት በፓርቲያችን ውስጥ የተፈጠረውን የክህደት ቡድንን የተሟላ የአመራር እና ድጋፍ አድርጎለታል” ሲሉ ተችተዋል።

በተጨማሪም ደብረጺዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) “በህዝባችን ላይ የተፈጸመውን የዘር ማጥፋት አለም በስሙ እንዲጠራው፣ የእነ ጀነራል ሰዓረ መኮንን ግድያ እንዲሁም በህዝባችን ላይ ግፍ የፈጸሙት ላይ ተጠያቂነት አንዲሰፍን ፓርቲያችን ህወሓት በቀጣይነት እንደሚሰራ መግለጽ እወዳለሁ” ሲሉ ገልጸዋል።

“አለምአቀፉ ማህበረሰብ፣ የአውሮፓ ህብረት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ ኢጋድ እና አሜሪካ የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ተግባራዊ እንዲሆን የበኩላቸውን እንዲወጡ አሁንም ጥሪያችንን እናቀርባለን” ብለዋል።

በተመሳሳይ በአከባበሩ ላይ ንግግር ያደረጉት የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝዳንት ሌተናል ጀነራል ታደሰ ወረደ ባስተላለፉት መልዕክት “ቀዳሚ ምርጫችን ሰላም ነው” ሲሉ በመግለጽ “ከዚህ ውጭ ያለው አማራጭ ተገደን የምንገባበት እንጂ ፈልገን የምንገባበት አለመሆኑን አለም በሙሉ የሚገነዘበው ሃቅ ነው” ብለዋል።

“አሁንም የትግራይ ህዝብ ቀዳሚ ምርጫ ሰላም እና ሰላም ብቻ ነው፣ በመሆኑም የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ሳይሸራረፍ እንዲተገበር ሰላማዊ፣ ዲፕሎማሲያዊ፣ ህጋዊ ጫና ማድረግ ይገባናል” ሲሉ አሳስበዋል። አስ

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በከተማዋ ከ24 ሺህ በላይ ንቁ የግንባታ ፈቃድ ያላቸው ሳይቶች መኖራቸው ተገለፀ

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚደርሰውን የህይወትና የንብረት ጉዳት ለመቀነስ የቁጥጥርና የግንዛቤ...

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ለሕክምና በወሰደችው መድኃኒት ምክንያት ከውድድር ታገደች

የቀድሞዋ የሁለት ጊዜ የዓለየቀድሞዋፒዮኗ ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ፀጋይ ከውድድር በፊት...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እውቅና ሊሰጣቸው ነዉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እውቅና የሚያገኙት የጎርጎርጎረሳዉያኑ 2026 በሞሮኮ...