” ፓርታሉ ህብረተሰቡ በቤቱ በራሱ፣ በኮምፒዩተር ቤቶች ሆኖ አገልግሎቱን የሚጠይቅበት ይዟል! “
የከተማዋ ነዋሪዎች ለ14 ዓመታት ሲያገለገሉበት የነበረውን የወሳኝ ኩነት እና የነዋሪነት አገልግሎት አሰጣጥ ሲስተም በአዲስ ሲስተም መቀየሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲቪል ምዝገባ እና የነዋሪነት አገልግሎት ኤጀንሲ ገልጿል።
አዱሱ ሲስተም የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ በተገኙበት ዛሬ እንደተመረቀ፤ ከህዳር 29/2018 ዓ/ም ጀምሮ በአዲስ አበባ በ50 ወረዳዎች ነዋሪውን በመመዝገብ ተግባራዊ እንደሚደረግ የኤጀንሲው ዋና ዳይሴክተር አቶ ዮሴፍ ንጉሴ ገልጸዋል።
ለምን የቀድሞውን ሲስተም መቀየር አስፈለገ? አዲሱ ሲስተም ምን አካቷል ? አዱሱ ሲስተም ለ14 ዓመታት ከነበረው የሚለየው ምንድን ነው ? ለሚለው ጥያቄ አቶ ዮሴፍ ምን መለሱ ?
” ለ14 ዓመታት አገልግሎት የተሰጠበት ሲስተም ነበር በዲጅታል መታወቂያ። ግን የዛሬ 14 ዓመታት የነበረውና ዛሬ ያለው የአገልግሎት ፈላጊ ህዝብ ብዛት ተመሳሳይ አይደለም። ሲስተሙም ያን ለመሸከም ብቁ አይደለም። ሲስተሙ በዚያን ጊዜ በነበረው ነባራዊ ሁኔታ ነበር የተሰራው።
አሁን ዘመኑም የዲጅታል ነው፤ ሰው ቢሮ እየመጣ ተሰልፎ አገልግሎት የሚጠይቅበት ጊዜም አይደለም በሚል ነው አዲሱን ሲስተም ለማልማት የተነሳሳነው። ሌላው እንደ ሀገር የጀመርነው የብሔራዊ መታወቂያ ሥራም አንዱ ምክንያት ነው፤ ምክንያቱም የብሔራዊ መታወቂያ አሻራ እየተሰበሰበ ነው፤ ስለዚህ አገልግሎቶች ከፋይዳ ምዝገባ ጋር መተሳሰር ስላለባቸው ነው።
አዲሱ ሲስተም ያካተታቸውን ጉዳዮች በተመለከተ አገልግሎቱን ለመስጠት ሦስት ዓይነት ሁኔታዎች አሉ።
አንደኛው ፐብሪሊክ የሚባል ፓርታል አለ። ፓርታሉ ህብረተሰቡ በቤቱ በራሱ በራሱ ኮምፒዩተር፣ በኮምፒዩተር ቤቶች ሆኖ አገልግሎቱን የሚጠይቅበት ይዟል።
ሁለተኛው ሞባይልን መሰረት ያደረገ አገልግሎት ነው። በሞባይል የነዋሪነት መታወቂያውን ዲጂታሊ በሞባይል ይዞ መንቀሳቀስ ያስችላል።
ለምሳሌ ‘ሰዎች መታወቂ ፕሪንት ለመደረግ ዘገየብኝ’ ይላሉ፣ በዚህም መታወቂያ በእጃቸው አይኖርም። በአዲሱ ሲስተም ግን ዲጂታል መታወቂያው ሞባይል ላይ ይደርሳል። ከአፕና ፕሌይ ስቶር አፕልኬሽኑን (ፕሮሰስ ተደርጓል ሲጠናቀቅ) አውርደው መታወቂያቸውን ይዘው መንቀሳቀስ ይችላሉ። አገልግሎት ላይ ቅሬታ ካለም በአፕልኬሽኑ ጽፎ ለመላክ ያስችላል።
በሌላ በኩል፣ መታወቂያው/የልደት ካርዱ ከኤጀንሲው ነው የተወሰደው? የሚለውን ለማረጋገጥ የሞባይል ኦንላይን ኦተንትኬሽን አለው። ከአካላዊ ማረጋገጫ ውጭ በሞባይል ሲስተም ማረጋገጫ ይረገጥበታል የሚል አሰራር ይዟል።
ሦስተኛ በድግግሞሽ የሚሰጥን አሻራን ያስቀራል። በነበረው አሰራር የተገልጋዩን አሻራ፣ ፎቶ ተቀብለን እንመዘግባለን። ያ ለመመዝገብ ሰዓት ይወስዳል። የባዮሜትሪክ ድግግሞሽም ያስከትላል፤ ያ ማለት ለፋይዳ አሻራ የሰጠ ሰው እንደገና ለኤጀንሲው አሻራ እንዲሰጥ ይገደዳል። ስለዚህ አንድ ሰው ሁለት ሦስት ጊዜ አሻራ እየሰጠ መቀጠል የለበትም።
ስለዚህ ተገልጋዩ አንድ ጊዜ ፋይዳ ላይ አሻራ ሰጥቷል፤ ከዚያ የፋይዳ ቁጥሩን ብቻ አስገብቶ አገልግሎቱን ማግኘት የሚችልበት ነው አዲሱ ሲስተም። ጊዜ ይቆጥባል፣ አሻራው እንኳ እምቢ ቢለን ወደ ማኑዋል እንዳንመለስም ሙሉ ጂዲታል ያደርገናል” ብለዋል።
የአዲሱ ሲስተም ስራ ሲጀመር፣ ቢሮ ተሰልፎ አገልግሎት ሲጠይቅ የነበረው የተገልጋይ ብዛት ለመቀነስ እንደሚያስችል፣ በአንድ ጊዜ ሁሉም ሰው አገልግሎቱን መጠቀም ይጀምራል ማለት ባይቻልም፤ ሰውን በሂደት ግንዛቤ እንደሚሰጥ፣ ሲስተሙ ለጊዜው ይፋ የተደረገው ለአዲስ አበባ ነዋሪዎች ብቻ እንደሆነ፣ ወደ ክልሎችም እንደሚዘረጋ አቶ ዮሴፍ አስረድተዋል።
@tikvahethiopia
