በኢትዮጵያ 12 የሚደርሱ የግል አየር መንገዶች አገልግሎት እየሰጡ ይገኛል፡፡ እነዚህ አየር መንገዶች የግል የበረራ ዘርፉን ለማጠናከር ስላላቸው ሚና እና ቁጥራቸውን ለማሳደግ ምን መደረግ አለበት በሚለው ዙሪያ ኤፍ ኤም አዲስ 97.1 የሚመለከታቸውን ኃላፊ አነጋግሯል፡፡
በኢትዮጵ ሲቪል አቬዬሽን ባለስልጣን የህዝብ ግንኙነት እና ኮሚኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አቶ እንዳለ አሰፋ እንደገለጹት፤ በኢትዮጵያ ያሉ የግል አየር መንገዶች በዋናነት ለንግድ አገልግሎት የሚውሉ ናቸው፡፡
ሸቀጦችን ወደ ምስራቅ አፍሪካ በማመላለስ አገልግሎት እየሰጡ ሲሆን በዚህም የሀገሪቱን ኢኮኖሚ ከማገዝ አኳያ ከፍተኛ ጠቀሜታ እያስገኙ መሆኑን ነው የጠቆሙት፡፡
የግል አየር መንገዶቹ ያሏቸው አብዛኞቹ አውሮፕላኖች ቀላል በመሆናቸው፣ የኢትዮጵያ አየርመንገድ በማይደርስባቸው እና ለትራንስፖርት ምቹ ባልሆኑ አካባቢዎች በመድረስም ለቱሪዝም መስፋፋት የበኩላቸውን ሚና እያበረከቱ መሆኑንም አክለው ገልጸዋል፡፡
የአቬዬሽን ኢንዱስትሪው ብዙ መዋዕለ ንዋይ የሚፈልግ በመሆኑ እንዲሁም ስለ ዘርፉ በቂ እውቀት አለመኖሩ በኢትዮጵያ የግል አየር መንገዶች ቁጥር አነስተኛ እንዲሆን እንዳደረገው ነው አቶ እንዳለ የሚገልጹት፡፡
በኢትዮጵያ የአቬዬሽን ዘርፉ ገና ያልተሰራበት በመሆኑ ፍላጎት ያላቸው ባለሀብቶች ወደ ዘርፉ ቢቀላቀሉ ራሳቸውን ከመጥቀም ባሻገር ሀገራቸውን መጥቀም እንደሚችሉ ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን ከዚህ ቀደም ሀገር በቀል የአየር ትራንስፖርት ኦፕሬተሮች እየሰጡት ካለው የቻርተር በረራ በተጨማሪ፣ መደበኛ የመንገደኞች እና የጭነት በረራ አገልግሎቶች መስጠት እንዲችሉ መፍቀዱ ይታወሳል፡፡
