👉 በዓለም አቀፍ ደረጃ 103 ሚልዮን በላይ ሰዎች ለዓይን ጤንነት ምቹ ባልሆነ ቦታ ይኖራሉ ተ
ከአጠቃላይ የኢትዮጵያ ሕዝብ 66 በመቶ የሚሆነው ለዓይነ-ስውርነት ለሚዳርገው ‘ትራኮማ’ አጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች እንደሚኖር የኢትዮጵያ የዓይን ሕክምና ባለሙያዎች ማህበር አስታውቋል።
የማኅበሩ ሥራ አስፈጻሚ እና የኦርቢስ ኢትዮጵያ የኢትዮጵያ ዳይሬክተር ዶክተር ዓለማየሁ ሲሳይ፤ “ኢትዮጵያ ለዓይን ችግር ተጋላጭ የሆኑ ብዙ ሰዎች መኖሪያ ከሆኑ የአፍሪካ ሀገራት መካከል ከቀዳሚዎቹ ተርታ ትሰለፋለች” ሲሉ ለአሐዱ ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ ደረጃ በተቀመጠው የአሰራር መስፈርት መሰረት ኢትዮጵያ በየ5 ዓመቱ የዓይን ምርመራ ቅኝት ማካሄድ ቢኖርባትም፤ ቅኝቱ ከተካሄደ 20 ዓመታት ማለፋቸውን ያብራሩት ዶክተር ዓለማየሁ፤ ለዓይን ሕመም መባባስ በምክንያትነት ከጠቀሷቸው ጉዳዮች መካከል የአየር ንብረት መዛባት ይገኝበታል።
በተጨማሪም የንጹህ ውሃ አቅርቦት፣ በተለይ በገጠራማው የኢትዮጵያ ክፍል ያለው የግንዛቤ እጥረትም ችግሩን የሚያባብሱ ጉዳዮች መሆናቸውን ተናግረዋል።
ሌላኛው የዘርፉ ፈተና የዓይን ሐኪሞች ቁጥር ማነስ እንደሆነ ያነሱም ሲሆን፤ “በኢትዮጵያ ያሉት የዓይን ጠቅላላ ሐኪሞች ቁጥር ከ200 አይበልጥም። ከእነዚህ መካከል የስፔሻሊቶቹ ቁጥር ደግሞ 7 ብቻ ነው” ብለዋል፡፡
የሐኪሞቹ ቁጥር ከታካሚው ብዛት እና ከሕዝብ ብዛት ጋር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ፤ ጤና ሚንስቴር፣ ትምህርት ሚንስቴር እና ሌሎችም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩበትም አሳስበዋል።
በአውሮፓውያኑ 2025 ብሩንዲ፣ ጋና፣ ቻይና፣ ህንድ እና ሴኔጋልን ጨምሮ 25 ሀገራት ትራኮማን ሙሉ በሙሉ መግታት መቻላቸውን መረጃዎች ያሳያሉ።
(አሐዱ ሬዲዮ)
