የሶማሊላንዱ ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሀመድ አብዱላሂ (ኢሮ) የአሜሪካን ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕን ለኖቤል የሰላም ሽልማት በይፋ እጩ አድርገው አቀረቡ።
ኢሮ ትራምፕን ለሽልማቱ እጩ አርገው ያቀረቡትም በዓለማችን ላይ በጣም አሳሳቢ የሆኑ ግጭቶችን ለመፍታት ላደረጉት ጥረት ምስጋናቸውን በመግለጽ ነው።
የሶማሊላንድ ሁለተኛ ዋና ከተማ በሆነችው ቡሮአ ንግግር ያደረጉት ፕሬዝዳንት ኢሮ፤ በሩሲያና ዩክሬን መካከል ያለውን ጦርነት እንዲሁም በእስራኤልና በኢራን መካከል የነበረውን ውጥረት ጨምሮ አሜሪካ የተለያዩ ግጭቶችን ለማስቆም ላደረገችው ጥረት ምስጋናቸውን ገልጸው፤ ለፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲሰጥ ድምፃቸውን እንደሚያሰሙ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንት አብዲራህማን ሞሀመድ አብዱላሂ (ኢሮ) በንግግራቸውም “የሶማሊላንድ ሪፐብሊክን እውቅና ለመስጠት ላሰቡት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ምስጋናዬን ማቅረብ እፈልጋለሁ” ያሉ ሲሆን፤ “ዛሬ እኔ እንደ ሶማሊላንድ ፕሬዝዳንት ግጭቶችን ለመፍታት እና በመላው ዓለም ሰላምን ለማምጣት ላደረጉት ጥረት ዕውቅና በመስጠት ለፕሬዝዳንት ትራምፕ የኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲሰጣቸው ለመደገፍ ከዓለም አቀፍ መሪዎች ጎን መሰለፌን በይፋ አውጃለሁ” ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ኢሮ ይህን የገለጹት በትራምፕ አስተዳደር በቀጣናው በተለይም በሶማሊላንድ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ ለውጥ ይመጣል ተብሎ በሚጠበቅበት ወቅት ሲሆን፤ ሶማሊላንድም ከሶስት አስርት ዓመታት በኋላ ዓለም አቀፍ ዕውቅና ለማግኘት እየጣረች በምትገኝበት ወቅት መሆኑን ሆርን ዲፕሎማት ዘግቧል።
