የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ ላይ ከመጋረጃ ጀርባ ሊደረግ የነበረው የምስክር አሰማም ሂደት እንዲታገድ ትዕዛዝ ማስተላለፉን የተከሳሾች ጠበቃ ሰለሞን ገዛኸኝ ገለጹ።
ባሳለፍነው ሳምንት ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስቲያን ታደለ የሚገኙበት የክስ መዝገብ ላይ የዐቃቤ ሕግን ምስክር ለመስማት ችሎቱ ቀጠሮ ይዞ ነበር።
ሆኖም በወቅቱ አቶ ክርስቲያን ታመው እንደነበረና ይህንኑ ለችሎት ተናግረው ተለዋጭ ቀጠሮ እንዲሰጥ መጠየቃቸውንና ችሎቱም የመጨረሻውን ምስክር ለመስማት ረቡዕ ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል።
በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው ክስ የተመሰረተባቸው ተከሳሾች በወቅቱ ለችሎቱ በጽሑፍ ካቀረቧቸው አቤቱታዎች መካከል አንዱ ከአቃቤ ህግ የምስክር አሰማም ሂደት ጋር የሚገናኝ ነው።
ተከሳሾቹ በአቤቱታቸውም በክስ መዝገቡ ላይ አቃቤ ህግ አቀርባቸዋለሁ ያላቸው ምስክሮች 21 መሆናቸውን ነገር ግን በምስክር ማሰማት ሂደት መጨረሻ ላይ አንድ ምስክር ተለዋጭ እንዲሆንልኝ ሲል መጠየቁን አስታውሰው፤ በወቅቱ ሁሉም ምስክሮች በችሎት ፊት ቀርበው ቃላቸውን ፊት ለፊት የሰጡ ቢሆንም ተለዋጭ ተደርጎ የተጨመረው የአቃቤ ህግ ምስክር ግን ከመጋረጃው በስተጀርባ ማንነቱ ሳይታወቅ እንዲመሰክር ፍርድ ቤቱ “በተለመደው ወገንተኛነቱ” ሆኖ መወሰኑንና ይህም የተፈለገበት ምክንያት ራሱ አቃቤ ህግ ወይም የፍትሕ ተቋማት ሰዎች “ከሳሽ፣ መስካሪና ፈራጅ ሆነው ለመቅረብ እንዲያመቻቸው መሆኑ አያጠራጥርም” ብለዋል።
ጠበቆች ከመጋረጃ ጀርባ ምስክር እንዳይሰማ የይግባኝ አቤቱታውን ያቀረቡት ሐምሌ 8 ቀን 2017 ዓ.ም ነው። በወቅቱ ጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ለሐምሌ 29 ቀን 2017 ዓ.ም ቀጠሮ መስጠቱን ያስታወሱት ጠበቃው፤ ይሁን እንጂ እስከ ሐምሌ 29 የሚቆይ ከሆነ ከፍተኛው ፍርድ ቤት ከመጋረጃ በስተጀርባ ያለውን ምስክር ለመስማት ለትናንት ሐምሌ 16 ቀጠሮ በመያዙ በተከሳሽ ላይ “የማይተካ ጉዳት ያደርሳል” በሚል ሐምሌ 15 ቀን 2017 ዓ.ም በድጋሚ ደብዳቤ አቤቱታ ማቅረባቸውን አመልክተዋል።
በዚህም የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ ላይ ከመጋረጃ ጀርባ ሊደረግ የነበረው የምስክር አሰማም ሂደት እንዲታገድ ትዕዛዝ ማስተላለፉን አስታውሰው ይሄንኑ የእግድ ትዕዛዝ ይዘን ትናንት ሐምሌ 16 ቀን 2017 ዓ.ም ችሎት ላይ ምስክር ከመሰማቱ አስቀድሞ አቀረብን ብለዋል።
ከፍተኛ ፍርድ ቤቱም በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው የተላለፈውን የእግድ ትዕዛዙን ተመልክቶ የጠቅላይ ፍርድ ቤቱን ውሳኔ ለመጠባበቅ በማለት ለሚቀጥለው ዓመት ለጥቅምት 10 ቀን 2018 ዓ.ም ቀጠሮ መያዙን አመልክተዋል።
ከዚህ ቀደም በእነ አቶ ዮሐንስ ቧያለው መዝገብ ክስ የተመሠረተባቸው ተከሳሾች “በፍትሕ ስም የባርነት እና የጭቆና ቀንበርን ማስተናገድ የማንችልበት ደረጃ ደርሰናል” ሲሉ አቤቱታ ማቅረባቸውንና አቤቱታቸው ምላሽ ካላገኘ ጉዳያቸውን ለመከታተል ችሎት እንደማይቀርቡ መግለጻቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ተከሳሾቹ የጽሑፍ አቤቱታቸውን ያቀረቡት ረቡዕ ሐምሌ 9 ቀን 2017 ዓ.ም ጉዳያቸው ለሚታይበት ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ለሕገ መንግሥት እና ሽብር ወንጀል ጉዳዮች ችሎት ነው።
አዲስ ስታንዳርድ በወቅቱ በተመለከተው አቤቱታ ላይ ተከሳሾቹ “ከህግ አግባብ ውጭ በእስራትና በመንግስታዊ እገታ ፍትሕ ተነፍገን ከቆየን ሁለት አመታትን አስቆጥረናል” ብለዋል።
“ከነገ ዛሬ የፍትሕ ሂደቱ ይሻሻል ይሆናል ብለን ብንጠብቅም ከጊዜ ጊዜ ሂደቱ ከድጡ ወደ ማጡ እየሆነ በእኛ በተከሳሾች ላይ ሰፊ የመብት ጥሰትና በደል እየተፈጸመብን ይገኛል” ሲሉ አቤቱታቸውን አቅርበዋል።
“ችሎቱ ሙሉ በሙሉ ለመንግስትና ለገዢው ፓርቲ ወግኗል” ያሉት ተከሳሾች፤ አክለውም “ያልተቋረጠ ጫናና ይሉኝታ ቢስ ውሳኔዎችን በተደጋጋሚ ፈጽሞብናል” ሲሉ አቤቱታ አቅራቢዎቹ በፍርድ ቤቱ ተፈጸሙ ያሏቸውን አስር “ኢ-ፍትሐዊ ውሳኔዎች” በዝርዝር በአቤቱታቸው ላይ አስፍረዋል።
ስለሆነም “በፍትሕ ስም የባርነት እና የጭቆና ቀንበርን ማስተናገድ የማንችልበት ደረጃ ላይ በመድረሳችን” እንዲሁም “ፍርድ ቤቶችና ዳኞች አጠቃላዩም የፍትሕ ስርዓት ተፈትነው የወደቁ መሆናቸውን በበቂ ሁኔታ በተግባር በማረጋገጣችን የጠቀስናቸው ችግሮች እስካልተቀረፉ ድረስ በዚህ ችሎት ቀርበን ለመዳኘት ዝግጁ አለመሆናችንን እንገልጻለን” ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዚህ ወቅት የችሎቱ ዳኞች አቤቱታውን ካነበቡ በኋላ “አቤቱታው ችሎት አንቀርብም የሚል ነው፤ ይሄንን አንቀበልም፤ በዳኞች ላይ ተቃውሞ ካላችሁ ዳኞች ይነሱልን ማለት ትችላላችሁ” ሲሉ መግለጻቸውን ጠበቃ ሰለሞን ከአዲስ ስታንዳርድ ጋር በነበራቸው ቆይታ አብራርተዋል።
በምላሹ አቶ ዮሐንስ ቧያለው “አቤቱታችን፤ ያቀረብነውን ቅሬታ እንድትፈቱልን ነው። ችሎት አንቅርብም ያልነውም ቅሬታችን የማይፈታ ከሆነ ነው” ማለታቸውን አክለው ገልጸዋል።
አቶ ዮሃንስ ቧያሌው እና አቶ ክርስትያን ታደለን ጨምሮ 52 ግለሰቦች በአማራ ክልል በተከሰተው የፀጥታ ችግር ምክንያት ከታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጋር በተያያዘ በቁጥጥር ውለው የሽብር ወንጀል ክስ እንደተመሰረተባቸው ይታወቃል።
የአማራ ክልል ምክር ቤት አባል የሆኑት 1ኛ ተከሳሽ አቶ ዮሃንስ ቧያሌው በሆኑበት በዚህ የክስ መዝገብ ሥር፣ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የሆኑት አቶ ክርስትያን ታደለ፣ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል የሆኑት ዶክተር ካሳ ተሻገር፣ አቶ እስክንድር ነጋ ፣ አቶ ዘመነ ካሴ እና ዶክተር ጫኔ ከበደ ይገኙበታል።
ለተከሳሾች እና ጠበቆቻቸው የደረሰው የክስ ዝርዝር ተከሳሾች “የፖለቲካ ርዕዮትን በኃይል ለማስፈፀም በማሰብ የአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤትን ዓላማ ለማስፈፀም” ተሰባስበው መምራት የሚል ክስ ነው።
የፌደራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ ክሱን አስመልክቶ ያወጣው መረጃ እንደሚያመለክተው ግለሰቦቹ ክስ የተመሠረተባቸው “የፖለቲካ ርዕዮትን በኃይል ለማስፈጸም በማሰብ ከአማራ ፋኖ አንድነት ምክር ቤት ጋር በመደራጀት” ነው።
አዲስ እስታንደርድ
