የመንግሥት አስፈጻሚ መስሪያ ቤቶች እና የልማት ድርጅቶች የሚሰጧቸው አገልግሎቶች ልዩ ትኩረት የሚሹ የሕብረተሰብ ክፍሎችን መብቶች ባከበረ መልኩ መፈጸማቸውን ለማረጋገገጥ፤ በ191 የክልልና የፌደራል ተቋማት ላይ ቁጥጥር ማድረጉን የኢትዮጵያ የሕዝብ እንባ ጠባቂ ተቋም አስታውቋል።
በዚህም በተደረገው ቁጥጥር በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ ምክንያቶች ለተፈናቀሉ ዜጎች የወሳኝ ኩነት ምዝገባ አገልግሎቶች እስካሁን አለመጀመሩ፤ የውጭ ሀገር ስደተኞችን በሀገር አቀፍ የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ሥርዓቶች ውስጥ ተሳታፊ ለማድረግ እንዲሁም ግልጽ መረጃ ለመያዝ እንዲቻል የዲጂታል መታወቂያ ተግባራዊ አለመደረጉ አሉታዊ ተጽእኖ ስለማሳደሩ መረጋገጡን ገልጿል።
ለቡሳ ጎኖፋ ስርዓት ፈንድ የሚሰበሰቡ እና ገቢ የሚሆኑ ክፍያዎች በሙሉ በደረሰኝ እንዲሆኑ ሕጉ የሚያስቀምጥ ቢሆንም፤ በአንዳንድ ቦታዎች ያለ ደረሰኝ የሚሰበሰቡበት ሁኔታ መኖሩ ከፋዮች ለበደል እንዲጋለጡ ማድረጉን የተቋሙ የሕዝብ ግንኙነት እና የኮሙኒኬሽን ሥራ አስፈፃሚ አንለይ ወርቄ ለአሐዱ ተናግረዋል።
በተመሳሳይ በበጎ ፈቃድ በአይነት የሚሰጡ መዋጮዎች የእቃውን አይነት እንጂ ተመጣጣኝ የዋጋ ግምታቸው በግልጽ እንዲመዘገብ በሕጉ ተደግፎ አለመቀመጡ፤ አፈጻጸሙ ለአስተዳደር በደልና ብልሹ አሰራር የሚዳርግ መሆኑን አንስተዋል።
በታዳጊ ክልሎች ተማሪዎች በአፍ መፍቻ ቋንቋ እንዲማሩ በየትምህርት ዘርፉ የሰለጠኑ መምህራን በጣም አናሳ ከመሆኑም በላይ፤ ቋንቋውን በመናገራቸው ብቻ ባልሰለጠኑበት የትምህርት መስክ እንዲያስተምሩ በመደረጉ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩንም ጨምረው ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም አንዳንድ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ውስጥ የሴት ሠራተኞችንና የአካል ጉዳተኞች ቅጥር፣ ዝውውር እና ድልድል በተሟላ መልኩ እየተተገበረ አለመሆኑን እንዲሁም፤ ቅሬታ ያለባቸው ሠራተኞች ያለ ፍርሃት ቅሬታ የሚያቀርቡበት አማራጭ እና የቅሬታ ሰሚ ኮሚቴ ያልተዋቀረ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሆኖም የተለዩ የሕግና የአሰራር ክፍተቶች ለሚመለከታቸው አካላት እንዲቀርቡ ተደርጎ ክፍተቶቹ ላይ ተገቢው ማስተካከያ እንዲደረግባቸው ምክረ ሃሳብ መሰጠቱን ተቋሙ ገልጿል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
