በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የእርሻ መሬት ለማዘጋጀት እና የወርቅ ማዕድን ለማውጣት በሚፈጸመው የመሬት ምንጣሮ ሳቢያ ተደጋግሞ የሚነሳው የሰደድ እሳት በመኖሪያ ቤቶች እና በእንስሳት ላይ ጉዳት ማድረሱን የክልሉ አካባቢ፣ ደን እና አየር ንብረት ለውጥ ባለሥልጣን ገልጿል።
የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሉቅማን አብዱልቃድር የወርቅ ቁፋሮ በሚከናወንባቸው አካባቢዎች የሚነሳው የሰደድ እሳት ከአቅም በላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ቆላማ የአየር ንብረት ስላለው፣ የሰደድ እሳቱ በበጋ ወቅት በሚከሰትበት ጊዜ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እንደሚያደርገውም ገልጸዋል።
በዚህ መንገድ የሚነሳው የሰደድ እሳት በመኖሪያ ቤቶች እና በእንስሳት ላይ ጉዳት አድርሶ እንደነበር አስታውሰዋል።
በዘንድሮ ዓመት በክልሉ በአንድ ወረዳ ላይ ተመሳሳይ የሰደድ እሳት አጋጥሞ፣ የከፋ ጉዳት ሳያደርስ በቁጥጥር ሥር ሊውል እንደቻለም እንደ አብነት ጠቅሰዋል።
ለእርሻ እና ወርቅ ለማውጣት በሚል በሰው ሰራሽ ምክንያት የሚነሳው የሰደድ እሳት እንዲቀንስ ክልሉ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል።
