ብፁዕን አባቶች አርሲ-አቦምሳ ወረዳ ተገኝተዉ ምዕመናንን አጽናኑ ጊዜያዊ እርዳታም አበረከቱ

Date:

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቋሚ ሲኖዶስ በአርሲ ዞን አንዳንድ ወረዳዎች የተከሰተውን ችግር ተከትሎ
በብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁና በብፁዕ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊው የሚመራ የቤተክርስቲያናችን ልዑክ በሥፍራው በመገኘት ተጎጂዎችን እንዲያጽናና ጊዜያዊ ርዳታም እንዲያደርግ ያስተላለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ዛሬ ማለዳ ወደ አርሲ ዞን አቦምሳ ወረዳ በመጓዝ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች አጽናንቷል፤ ጊዜያዊ እርዳታም አበርክቷል።

በአቦምሳ ወረዳ የትንሣኤ ብርሃን ደብረ ገነት መድኃኔዓለም ቤተክርስቲያን በመገኘት ተጎጂ ኦርቶዶክሳዊያንን ያጽናኑት
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ፣የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት

ቅድስት ቤተክርስቲያን በኦርቶዶክሳዊያን ልጆቿ ላይ በደረሰው ጉዳት እጅግ በጣም ማዘኗን ገልጸው እግዚአብሔር አምላክ ለሞቱት ወገኖቻችን መንግስተሰማያትን እንዲያወርስልን፣ ለቤተሰቦቻቸው መጽናናት እንዲያድልልን የዘወትር ጸሎታችን ነው።በርቱ፣ጠንክሩ እግዚአብሔር ከእናንተ ጋር ይሁን ብለዋል።

አያይዘውም ቋሚ ሲኖዶስ በአካል ተገኝቶ እናንተን ለማጽናናትና ጊዜያዊ ድጋፍ ለማድረግ በመካከላችሁ ተገኝተናል ያሉት ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ችግሩን ከመሰረቱ ለመፍታትና የተቃጠለውን ቤተክርስቲያን ለመሥራት የሚያስቼል አቢይ ኮሚቴ በጠቅላይ ቤተክህነት ተሰይሞ ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ የምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ባስተላለፉት አባታዊ መልዕክት ቅድስት ቤተክርስቲያን በተከሰተው ችግር ጥልቅ ኃዘን የተሰማት መሆኑን ገልጸው

ምዕመናን በሃይማኖታቸው እንዲጸኑ፣በፈተና ሁሉ እንዲታገሱ አደራ ካሉ በኋላ እግዚአብሔር አምላክ ኃዘንተኞችን እንዲያጽናና ከዳግም ኃዘን እንዲሰውርልን ዘወትር እንጸልያለን በማለት ቃለ ምዕዳንና ቃለ ቡራኬ ሰጥተዋል።

በመጨረሻም ብፁዕ ጠቅላይ ሥራ አስኪያጁ ለተፈናቀሉ ወገኖች የተዘጋጀውን ርዳታ ለሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለብፁዕ አቡነ ኤልሳዕ አስረክበዋል።

በዚሁ ጊዜ የአቦምሳ ከተማ የሀገር ሽማግሌዎችና አባ ገዳዎች ብፁዓን አባቶችን እንኳን ደህና መጣችሁልን በማለት በሀገሩ ባህል መሰረት የሰንጋ ስጦታ ካበረከቱ በኋላ የደረሰውን ጉዳት በመኮነን ሕዝቡ በስምምነት፣በአንድነትና በመቻል የኖረና ወደፊትም የሚኖር ሕዝበብ መሆኑን ጠቅሰው የተፈጠረውን ችግር ሃይማኖታዊ መልክ ለማስያዝ የሚደረገው ጥረት ተገቢነት የሌለው ነው ብለዋል።ለብፁዓን አባቶች የተበረከተው የሰንጋ ስጦታም ለተፈናቀሉ ወገኖች እንዲደርስ ተደርጎ የመርሐ ግብሩ ፍጻሜ ሆኗል።
EOTCTV

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

በከተማዋ ከ24 ሺህ በላይ ንቁ የግንባታ ፈቃድ ያላቸው ሳይቶች መኖራቸው ተገለፀ

በኮንስትራክሽን ዘርፍ የሚደርሰውን የህይወትና የንብረት ጉዳት ለመቀነስ የቁጥጥርና የግንዛቤ...

አትሌት ጉዳፍ ፀጋይ ለሕክምና በወሰደችው መድኃኒት ምክንያት ከውድድር ታገደች

የቀድሞዋ የሁለት ጊዜ የዓለየቀድሞዋፒዮኗ ኢትዮጵያዊቷ ጉዳፍ ፀጋይ ከውድድር በፊት...

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ እውቅና ሊሰጣቸው ነዉ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ እውቅና የሚያገኙት የጎርጎርጎረሳዉያኑ 2026 በሞሮኮ...