‹‹ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከተልዕኳቸው አፈንግጠዋል››

Date:

ዶ/ር አማኑኤል ኤርሞ

(የኢዜማ ሊቀመንበር)

በሀገራችን የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት በሕግ ከተፈቀደ ወዲህ ያለው የሠላሳ ዓመቱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዞ በብዙ ስንክሳር ውስጥ ያለፈ ነው፡፡ ውስን በሚባሉ የምርጫ ወቅቶች ቀላል የማይባል ተሳትፎና ድል ማስመዝገብ የቻሉ ጥቂት ፓርቲዎች የመኖራቸውን ያህል፣ አብዛኞቹ ግን የቤተሰብ አክሲዮን እስኪመስሉ ድረስ ለነበረው አገዛዝ ‹‹ዴሞክራሲያዊነት›› ማዋዋቢያ ከመኾን የተሻገረ ሚና ሳይኖራቸው ኖረዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት ደግሞ አጠቃላይ የሀገሩ ፖለቲካ እና ደህንነት እጅግ አደገኛ ቅርቃሩ በገባበት ሁኔታ በሰላማዊ ትግል ‹‹እንንቀሳቀሳለን›› የሚሉ የፖለቲካ ኃይሎች ሚና እና ተሳትፎ አሳዛኝ በሚባል ሁኔታ ‹‹የለም›› የሚባልበት ደረጃ ደርሷል፡፡ ምንም እንኳን ጥቂት ፓርቲዎች ምርጫ 2013ን ተከትሎ ከመንግሥት ጋር ሥልጣን ተጋርተው መሥራት የመጀመራቸው እውነታ፣ በሀገሪቱ የመድብለ ፓርቲ ታሪክ ውስጥ ትልቅ እምርታ ተደርጎ በገዢው ፓርቲ በኩል ቢቀነቀንም፣ የእነኚህ ፓርቲ አንዳንድ ተወካዮች በተለያየ የፌዴራልና የክልል ኃላፊነት ወንበሮች ላይ መሠየም ግን የሀገሪቱን ማኅበረ ፖለቲካዊ ችግር መፍትሔ ከመሥጠት አንጻር ምን ጥቅም አስገኘ የሚለው አከራካሪ ነው፡፡ እንዲህ ባለው የመንግሥትና የተቃዋሚ ፓርቲዎች ግንኙነት እና ሚና ዙርያ ጥናት ካካሔዱት ከኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ሊቀ መንበር ዶ/ር አማኑኤል ኤርሞ ጋር የግዮን መጽሔት ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኅመወርቅ ተከታዩን ቆይታ አድርጓል፡፡ እንኾ፡-     

ግዮን፡- የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሀገራዊ የፖለቲካ ተሳትፏቸውን በአግባቡ እየተወጡ ነው?

ዶ/ር አማኑኤል፡- ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ዋና ሥራቸው ምንድን ነው የሚለውን መጀመሪያ ማየት ይኖብናል፡፡ በዲሞክራሲ ላይ ጥናትና ምርምር የሠራ አካል አንድ የሚለውን ነገር አለው፡፡ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ዋና ሥራ መቃወም ነው ብሎ ያስቀምጣል፡፡ በዚያ መሠረት በሀገራችን ያሉ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ አሁን ባለንበት ሁኔታ ሚናቸውን እየተወጡ ነው ለማለት ያስቸግራል፡፡ ምክንያቱም የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ዋናው ዓላማ ሀገሪቱ ውስጥ መድበለ ፓርቲን ማስፋፋት፣ ተጠያቂነት ያለበትን ሥርዓት ማስፈን፣ ሚዛናዊ  የሆነ ሁኔታ እንዲኖር ማድረግ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎችን ስንመለከታቸው አሁን ያሉ ፓርቲዎች የሚጠበቅባቸውን እያደረጉ ነው ማለት ያስቸግራል፡፡

ግዮን፡- ይህ ግን ለምን ሊሆን ቻለ?

ዶ/ር አማኑኤል፡- ይህ የሆነው ሀገራችን አሁን ባለችበት ሁኔታ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተልዕኳቸው በመዛነፋቸው ነው፡፡ እያንዳንዱ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ ሲቋቋም የራሱ ማኒፌስቶ አለው፡፡ በተለይ በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ወደ 12 የሚጠጉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች  ከራሳቸውም ተልዕኮ ወጥተው የገዥው ፖለቲካ ፓርቲ ጉዳዩ አስፈጻሚ ኾነዋል፡፡ በሌላ አነጋገር አብዛኞቹ  ገዥው ፓርቲን እያገዙ ነው፡፡ ይህ በመኾኑ ከተልዕኮቿው አፈንግጠዋል፡፡

ግዮን፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን እንደመጡ ስማቸው ከተቋዋሚ ወደ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደሚቀየር ተናግረው ነበር፡፡ ‹‹ተቃዋሚ›› እና ‹‹ተፎካካሪ›› በሚለው ስም መካካል ያለው ልዩነት ምንድን ነው?

ዶ/ር አማኑኤል፡- እኛ የምናውቀው ተፎካካሪ ለአንድ ዓላማ የተነሱ አካላት የሚያደርጉት ፉክክር ነው፡፡ ተቃዋሚ የሚባለው ደግሞ የተለያየ አመለካከት፣ የተለያየ ዕቅድ፣ የተሻለ አማራጭ አለን ብለው የተሰለፉ አካላት የሚያደርጉት ግብግብ ነው፡፡ ስለዚህ በዓለም አቀፍ ተዛማጅ  ጽሑፍ  ላይ ስንመለከትም የምናውቀው ‹‹ኦፖዚት ፖለቲካል ፓርቲስ›› የሚባለውን እንጅ ‹‹ቴሲስ ሜከርስ›› የሚባለውን አይደለም፡፡ በመኾኑም ተቋዋሚ ፓርቲ የሚለውን ተፎካካሪ ፓርቲ የሚለው ስያሜ ሊወክለው አይችልም፡፡

ግዮን፡- እርሶ በጉዳዩ ጥናት እንዳደረገ ሰው፣ ስለ ልዩነታቸው በጥቂቱ ቢያስረዱን?

ዶ/ር አማኑኤል፡- ጥናቱን ያካሄድኩት በሀገር አቀፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች ላይ ነው፡፡ ጥናቱ ቀደም ሲል በዚህ ዙሪያ ተዳረጉ ጥናትን ምርምሮችንም ዳሷል፡፡ መረጃ አሰባሰብ ሂደቱም በቃለ መጠይቅ፣ በቡድን ተኮር ውይይት፣ በመረጃ ትንተና እና በመሰል ዘዴዎች የተከናወነ ነው፡፡ ከተገኘው መረጃ በመነሳትም ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከሚጠበቅባቸው ሚና አኳያ የት ነው ያሉት? የሚለውን ለማስቀመጥ ሞክሯል፡፡ ይህን ለማድረግ መጀመሪያ የተዛማጅ ጽሁፍ ቅኝት ከማድረግ ጀምሮ፣ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ይጠበቅባቸዋል? የሚለውን ለማየት ሞክሯል፡፡ በዚህ ሂደት ስናየው የመጀመሪያው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሥራ መንግሥቱን ተጠያቂ ማድረግ ኾኖ እናገኘዋለን፡፡ ይህን ሥራ በሀገራችን ያሉ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ሠርተዋል ወይ? የመንግሥት ፖሊሲና ተግባራት ላይ ተገቢውን ትችትና ክትትል አድርገዋል ወይ? የገዢው ፓርቲ ፖሊሲዎች ከሕዝብ ፍላጎትና ጥቅም አኳያ ተገቢ መኾናቸውን መርምረዋል ወይ? በኢኮኖሚ ላይ የሚፈጸመን በደል፣ የኑሮ ውድነትን፣ የሥራ አጥነትን፣ ሙስናን፣ ግልጸኛ አሠራርን ይተከታተላሉ ወይ? የሰብዓዊ መብት አያያዝና የዜጎች ነጻነት ተጠብቀዋል ወይ? የመናገርና የፕሬስ ነጻነት እንዴት እየጠበቀ ነው? የሚለውን መርምረዋል ወይ? ከብሔራዊ ደህንነት አኳያ መንግሥት ምን እየሠራ ነው? የሚለውን ተከታትለዋል ወይ፣… የሚለውን በሙሉ የሀገራችን የፖለቲካ ፓርቲዎች ምን ያህን እንዳከናወኑ ማየት ይገባል፡፡

በሌላ በኩል የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ፖሊሲዎችንም ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የፖሊሲ ፕሮግራም ማቅረብ፣ ገንቢ ትችቶችን ማቅረብ፣ ድክመቶችን አጉልቶ ማሳየት እንዲሁም የተለያዩ የሕብረተሰብ ፍላጎቶችን ማቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡ለምሣሌ በአሜሪካ ‹‹ቼክ ኤንድ ባላንስ›› የሚባል ነገር አለ፡፡ ተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች መንግሥት ምን እየሠራ ነው የሚለውን የሚያረጋግጡ ናቸው፡፡ የሕግና የሕገ መንግሥት ጉዳዮችን እንዴት እንዴት ተግባራዊ እያደረገና ሥልጣኑን እንዴት እየተጠቀመ እንደኾነ ይገመግሙታል፡፡ ከተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ያለው ግንኙነት ምን ይመሥላል የሚለውንም ያዩበታል፡፡ በፓርቲዎችና በሕዝብ መካከል መስተጋብር ይመለከቱበታል፡፡ የዴሞክራሲው ሒደት ከየት ወዴት እየተሻለ እንደኾነ ይገመግሙበታል፡፡ መንግሥትን በመገናኛ ብዙኃን ተጠያቂ የማድረግ ሂደቱ ምን ደረጃ እንደደረሰ ይገመግማሉ፡፡

ከእነዚህ ነገሮች በመነሳት በሀገራችን ያሉ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ደረጃ ምን ይመሥላል ብለን ማየት ይኖርብናል፡፡ በግልባጩ ደግሞ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ከፍ ሲል የተዘረዘሩትን ተግባራት ለማከናወን ሲንቀሳቀሱ የሚያጋጥሟቸው ተግዳሮቶችና እንቅፋቶች ምን ምን ናቸው የሚለውንም ማየት ይገባል፡፡

አሁን ባለው የፖለቲካ ምሕዳር የፖለቲካ ፓርቲዎች ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ከሕብረተሰቡ ጋር ተገናኝተው የሕዝብ ድምጽ ኾነው እየሠሩ ነው ማለት አይቻልም፡፡ ምክንያቱም ሀገራችን በማንነት ተወጥራለች፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከክልል ክልል ተንቀሳቅሰው ከሕዝብ ጋር መገናኘት አይችሉም፡፡ ይኽ በመኾኑም ተሸማቅቀው ይገኛሉ፡፡ በሌላ በኩል የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከመንግሥት ጋር ተቀራርበው መሥራታቸው የራሱ ችግር ያለበት መኾኑም መረሳት የለበትም፡፡

ግዮን፡- አሁን ላይ በሀገራችን የተቃዋሚ ፓርቲ አለ ማለት ይቻላል?

ዶ/ር አማኑኤል፡- በቁጥር ደረጃ በርካታ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ በተግባር ግን የሕዝብ ድምጽ ኾኖ መንግሥትን መገዳደር የሚችል ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲ የለም፡፡ ስለዚህ የሀገራችን ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙ ሥራ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ከመንግሥት ጋር የሚሠሩ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም፣ በችሮታ ሥልጣን ወስደው እንጂ ተባብረው ሕጋዊ ሂደትን ተከትለው ሥልጣን የያዙ አይደሉም፡፡ ይህ በራሱ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲችን አቅም ያሳነሰ አሠራር ነው፡፡ በመንግሥት ችሮታ ስልጣን ይዞ ከመንግሥት ጋር መስራት የተቃዋሚ የፖለቲካ  ፓርቲዎችን ከመጉዳቱም በላይ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓትን እጅግ ያቀጭጫል፡፡

ግዮን፡ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሥልጣን ከመንግሥት የመቀበል ፖሊሲን በማኒፌስቷቸው ያካትታሉ?

ዶ/ር አማኑኤል፡- በፖሊሲ ደረጃ ከመንግሥት ጋር ሥልጣን መጋራት የሚል ነገር የለም፡፡ እኔ በኢዜማ ፕሮግራም ውስጥ ይህን የሚደግፍ ማዕቀፍ አላየሁም፡፡ የኢዜማ ሰዎችም ከመንግሥት ጋር የሚሰሩት የሥጦታ ሥልጣን  ይዘው ነው፡፡

ግዮን፡- እንዲህ ዓይነቱ አሠራር እንደሀገር ያለው ጥቅም ምንድን ነው?

ዶ/ር አማኑኤል፡- ጥቅም የለውም፡፡ ጥቅም የሚኖረው በመንግሥት ፕሮግራም ውስጥ የራሳችን ፖሊሲና ፕሮግራም ተካቶበት ቢሆን ኖሮ ነበር፡፡ ያ ሲሆን በመጠኑም ቢሆን የራሳችንን ፖሊሲ በመንግሥት ላይ ለማስፈጸም በረዳን ነበር፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ፣ ፓርቲዎች ተለጣፊ ኾነው የሚቀጥሉ ከሆነ ግን ጉዳት ይኖረዋል፡፡ የትኛውም ፓርቲ የራሱን ፕሮግራም ይዞ ማስፈጸም ይኖርበታል እንጂ ጥገኛ መሆን የለበትም፡፡

ግዮን፡- የእርሶ ጥናት ምን ያህል ጊዜ ፈጀ? አስፈላጊነት ምን ነበር?

ዶ/ር አማኑኤል፡- ጥናቱን ለማዘጋጀት ግማሽ ዓመት ፈጅቷል፡፡ የጥናቱ አስፈላጊነት፣ እንደሚታወቀው የተቃዋሚ ፓርቲዎች በከፍተኛ  ቀውስ ውስጥ ነው ያሉት፡፡ በመጀመሪያ ጥናቱን ለመሥራት የተነሳሳሁት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ሚናቸውን ሲወጡ አለማየቴ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ የተወሰኑ ሰዎችን ሳናገር ጥናት ባደርግ የተሻለ እንደሚሆን ጠቆሙኝ፡፡ በዚህ ጥናት ውስጥ እኔ የማየው የተቀዋሚ ፓርቲዎች ችግር አንዱ ውስጠ ዲሞክራሲያቸውን አለማጠናከር ነው፡፡ ብዙ አመራር ፈጥረው ደጋፊ የማሰባሰብ ሥራቸውም ደከማ ነው፡፡ ግልጸኝነት በፓርቲያቸው ውስጥ ማስፈን አለባቸው፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ግን የሀገራችን ተቃዋሚ ፓርቲዎች ገዥው ፓርቲን መገዳደር የሚችል አቅም የላቸውም፡፡

ግዮን፡- አሁን ላይ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ችግሮች ሲፈጠሩ ፊት ለፊት ወጥተው ሲናገሩ አይታዩም፡፡ ይህ ለምን ኾነ ይላሉ?

ዶ/ር አማኑኤል፡- አንድ ፓርቲ የሚቋቋመው ለትግል ነው፡፡ መታገል ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም፡፡ መንግሥትም የሚታገሉትና ኃይላት ላይ የራሱን ጫና ይፈጥራል፡፡ ነገር ግን  የሕዝብ ድምጽ በመሾን መብቶች ይከበሩ ዘንድ በተቻለ መጠን መታገል ያስፈልጋል፡፡

ግዮን፡- በሌላው ዓለም የተቃዋሚ ፓርቲዎች ከመንግሥት ያላቸው መስተጋብር ምን ይመስላል?

ዶ/ር አማኑኤል፡- በየትኛውም ሀገር ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሕዝብ ድምጽ ናቸው፡፡ ተጠያቂነንት ለማስፈን ይሰራሉ፡፡ የመንግሥትን ሚዛናዊነት ለማስጠበቅ ይንቀሳቀሳሉ፡፡

ግዮን፡- እንዳሉበት የፖለቲካ ፓርቲና አመራር ማስተላለፍ የሚፈልጉት መልዕክት ምንድን ነው?

ዶ/ር አማኑኤል፡- እያንዳንዱ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ሲቋቋም የራሱ ፖሊሲና ፕሮግራም አለው፡፡ በዚህም ፓርቲዎች ፖሊሲና ፕሮግራማቸውን መነሻ አድርገው መንግሥትን ተጠያቂ የሚያደርግ ሥራ መስራት አለባቸው፡፡ በትግል የሕዝብ ችግር ለመፍታት እስከተዘጋጁ ድረስ ዘርፉ የሚጠይቀውን ሁሉ በመከወን መሥራት ይኖርባቸዋል ፤ ለሕዝባቸው ድምጽ መሆን ይገባቸዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ ገዢው ፓርቲ እየገነነ የመጣበት ወቅት በመሆኑ ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ተገዳዳሪ እየኾኑ መምጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡ ምክንያቱም ቀጣይ ዓመት ምርጫ ስላለን ሁሉም ተቃዋሚ ፓርቲዎች እራሳቸውን አብቅተው ለሕዝባቸው አማራጭ ሐሳብ ይዘው መቅረብ ይኖርባቸዋል፡፡

ግዮን፡- በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ስለፓርቲዎች እንቅስቃሴ መቀዛቀዝ የሚያነሱት ነገር አለ?

ዶ/ር አማኑአል፡- በፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት በአንድ ወቅት እድሉን አግኝቼ ነበር፡፡ ያኔ ግን አሁን ያለንበት ደረጃ ላይ አልነበረም፡፡ ወደፊት ግን ይህን ጉዳይ እንደ አጅንዳ ይዞ መነጋገርና መወያየት ይቻላል፡፡

ግዮን፡- የእናንተ ፓርቲ ኢዜማ እንደ ፓርቲ ያለበትን የመቀዛቀዝ ስሜት ገምግሟል?

ዶ/ር አማኑኤል፡- ግምገማ ለማካሄድ በሂደት ላይ እንገኛለን፡፡ ፓርቲያችን ከመንግሥት ጋር በመሥራቱ ያገኘው ጥቅም ምንድን ነው የሚለውን ለሕዝብ ለማሳወቅ ገና በጥናት ላይ ነው ያለነው፡፡ ስንጨርስ ውሳኔያችንን የምናሳውቅ ይሆናል፡፡ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲነት ብዙ መስዋዕትነት  ይጠይቃል፡፡ በጊዜ፣ በገንዘብ፣ በጉልበት፣… ከዚያ ያለፈ ዋጋንም ይጠይቃል፡፡ ሰዎች  እዚህ ውስጥ የሚገቡት ለሰዎች ብለው ነው፡፡ በተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ የሚያጋጥም ተግዳሮት ለራስ ክብርና ጥቅም ተብሎ የሚከፈል ዋጋ አይደለም፡፡ ስለዚህ ፖለቲካ በሀገራችን   የዜግነት እንዲኾን፣ ዲሞክራሲ እንዲጎለብት፣ ዜጎች በሰላም ወጥተው እንዲገቡ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲኖረን፣ የኢኮኖሚ እድገትና ፍትሕ እንዲሰፍን፣… የሚሰራበት መሆን ይኖርበታል፡፡ ከዚህ አንጻር የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲዎች ብዙ መሥራት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ግዮን፡- ስለነበረን ቆይታ በአንባቢያን ሥም ከልብ እናመሰግናለን፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከ989 ሚሊዮን ብር በላይ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የጉምሩክ ኮሚሽን ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3 ቀን 2018...

“እኔ እስካለሁ ድረስ ኢራን የኑክሌር መሣሪያ ባለቤት አትሆንም!”

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት ሰኔ 5 ቀን...

አገር እንዲህ ዓይንህን ለአፈር ይባላል?

በተጀመረው የአለም ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ በሜክሲኮ መሸነፏን ተከትሎ አፍሪካ...

አሜሪካ እና ኢራን የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት በ24 ሰዓት ውስጥ እንደሚፈራረሙ ፓኪስታን አስታወቀች

ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን በሰላም ድርድሩ ማዕቀፎች ላይ መስማማታቸውን...