የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሰው ሠራሽ ሐይቅን የሚጠብቅ በሀገሪቱ የመጀመሪያ የሆነ ‘የባህር ፖሊስ’ መደራጀቱን የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አስታወቀ፡፡
የግድቡ መሰረተ ድንጋይ በመጋቢት 24 ቀን 2003 ዓ.ም ከተጣለበት ዕለት ጀምሮ የፌደራል ፖሊስ በቦታው ያለው ሰላም እና የደህንነት ዋስትና እንዲረጋገጥ የማድረግ ተልዕኮን እየተወጣ መሆኑን ረዳት ኮሚሽነር ሰለሞን ከበደ ለኢቢሲ ዶትስትሪም ተናግረዋል፡፡
ሐይቁ 256 ኪሎ ሜትር ያክል የሚሸፍን በመሆኑ መደበኛ ሳይሆን ‘ኮስታል ፖሊስ ጋርድ’ በማቋቋም መጠበቅ ስላለበት ኃይሉ መደራጀቱን ገልፀዋል፡፡
በዚህም ከመከላከያ ኢንጅነሪንግ ጋር በመተባበር ጀልባዎችን የማዘጋጀት፣ የሰው ኃይል አደረጃጀቱን የማጠናከር እና የማሰልጠን ስራ እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአካባቢው ላይ ስጋት እንደሌላ የገለፁት ረ/ኮሚሽነሩ ቅድመ መከላከል ስራ እንዲሁም ለግድቡ የሚውሉ ቁሳቁሶችን ማጀብ እየተከወነ ያለ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም ከመንግሥት በሚሰጠው ተልዕኮ መሠረት ሥራውን በብቃት እንደሚወጣ ገልፀዋል።
