ትምህርት ሚኒስቴር በአዲስ አበባ እና በክልሎች በሚገኙ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች 40 የሙያ ትምህርቶችን ለመስጠት እየሰራ መሆኑን ገልጿል።
ከእነዚህም መካከል 12ቱ የሙያ ትምህርቶች ከ2017 ጀምሮ እየተሰጡ ሲሆን ለ2019 የትምህርት ዘመን ደግሞ ተጨማሪ 11 የሙያ ትምህርቶችን ለማስተማር ዝግጀት መጠናቀቁ ተገልጿል።
በትምህርት ሚኒስቴር የሥራ እና ተግባር ሥርዓተ-ትምህርት ዴስክ ኃላፊ አቶ ማህተቤ ዓለምአየሁ እንደገለጹት፤ 40ዎቹን የሙያ ትምህርቶች ወደ ስርአተ-ትምህርቱ ለማስገባት ጊዜና ገንዘብ ይጠይቃል።
የብረታ-ብረት ቴክኖሎጂ፣ የአውቶሞቲቭ ቴክኖሎጂ እና የአልባሳት ቴክኖሎጂ ለአዲሱ የትምህርት ዘመን ከተዘጋጁት 11 የሙያ ትምህርቶች መካከል ይገኙበታል ተብሏል።
በአዲሱ ትምህርት እና ሥልጠና ፖሊሲ የሙያ ትምህርቶች 8 ሌቭሎች እንዳሏቸው አቶ ማህተቤ አስታውሰዋል።
እነዚህ ትምህርቶች መካተታቸው ተማሪዎች ሌቭል 1 የሚባለውን የሙያ ደረጃ እንዲያሟሉ እንደሚያስችል ገልጸዋል።
በተጨማሪም ተማሪዎች ተቀጥረው ወይም ሥራ ፈጥረው እንዲሰሩ እንዲሁም በዩንቨርስቲ ደረጃ ሊያሳድጉት ለሚፈልጉት መሠረት እንደሚሆንላቸው ተናግረዋል።
ከተግባርና ከሙያ የተነጠለ ትምህርትን ለማስቀረት የሙያ ትምህርቶች ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንዳላቸው አቶ ማተቤ አክለው ገልጸዋል።
(አሐዱ ሬዲዮ)
