የቻይና የጦር መርከብ የጀርመንን የስለላ አውሮፕላን በሌዘር ጨረር ቀይ ባህር ላይ መምታቱ ተነገረ ።
የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማክሰኞ እንዳስታወቀው የቻይና የጦር መርከብ በቀይ ባህር ውስጥ በግዳጅ ላይ የነበረን የጀርመን አውሮፕላን ላይ በሌዘር ጨረሮች ጥቃት አድርሳለች ስትል ከስሳለች።
ሚኒስተሩ እንደገለፁት የስለላ አውሮፕላኑ የአውሮጳ ኅብረት አስፒድስ ተልዕኮ አካል ሲሆን ይህም የሲቪል መርከቦችን በየመን የሁቲ አማፂያን ጥቃት ለመከላከል ታስቦ ነው። በዚህ ወር መጀመሪያ ላይም በቻይና የጦር መርከብ ተመሳሳይ ችግሮች አጋጥሞታል ሲል ገልጿል።
ሚኒስቴሩ በትዊተር ገፁ ላይ “የጀርመን ወታደሮችን ለአደጋ ማጋለጥ እና ኦፕሬሽኑን ማደናቀፍ በፍፁም ተቀባይነት የለውም”ያሉ ሲሆን የሌዘር ጥቃት የደረሰበት የስለላ አዉሮፕላኑ በጅቡቲ የሚገኘው የጦር ሰፈር በሰላም ያረፈ ሲሆን የአውሮፕላኑ ሰራተኞች በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኙም ተነግሯል።
አክለዉም በሲቪል የንግድ አገልግሎት ሰጪ የሚተዳደረው አውሮፕላኑ ግን ከጀርመን ጦር አባላት ጋር በመሆን በቀይ ባህር ከአውሮፓ ህብረት ተልዕኮ ጋር ስራውን እንደጀመረ ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
እሁድ እለት የየመን የሁቲ አማፅያን በቀይ ባህር ላይቤሪያ ባንዲራ የምታዉለበልብ የእቃ መርከብ ላይ ኢላማ ያደረገ የሰአታት የፈጀ ጥቃት ማድረሱንና ሌሎችም ላይ መቀጠሉን የገለፁት ባለስልጣናት የሁቲ ቡድኑ ወሳኝ በሆነው የውሃ መስመር ላይ ጦርነቱን እንደገና በማደስ እያደረገ ያለዉ ጥቃት ከባድ በሆነበት ወቅት ቻይና በአውሮፓ ህብረት የጋራ የደህንነት እና የመከላከያ ፖሊሲ ማዕቀፍ ውስጥ የሚገኝን የስለላ አዉሮፕላን ማጥቃቷ አካባቢውን ተጋላጭ ያደርገዋል ብለዋል ።
