በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአሪ ዞን በጋዘር የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዛሬ ከጠዋቱ 3:00 ሰዓት ላይ አንዲት እናት 4 ልጆችን በሰላም ተገላግላለች።
አራቱም ሕጻናት በመልካም ጤንነት ላይ እንደሚገኙ የጋዘር መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስት ሐኪም ዶ/ር ወንድሜነህ ካሳሁን ለኢቢሲ ዶትስትሪም ገልጸዋል።
ከመውለጃ ጊዜዋ ቀድሞ ምጥ የመጣባት እናት ወ/ሮ ደስታ፣ ለአንድ ሳምንት ያክል በሆስፒታሉ የሕክምና ክትትል ስታደርግ መቆየቷን የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስቱ ተናግረዋል።
በዛሬው ዕለትም በቀዶ ሕክምና ታግዛ መውለዷን ዶ/ር ወንድሜነህ ገልጸው፤ አራቱም ሕጻናት በሆስፒታሉ አስፈላጊው እንክብካቤ እየተደረገላቸው እንደሚገኝ ተናግረዋል።
አራት ልጆችን በአንድ ጊዜ የተገላገለችው እናት ከዚህ ቀደም ሁለት መንትያ ልጆች መውለዷን አስታውሰው፤ የዛሬውን አይነት ክስተት በሆስፒታሉ ታሪክ አጋጥሞ እንደማያውቅ የማህፀንና ፅንስ ስፔሻሊስቱ ተናግረዋል።
