አዝማሪዎች እና ባለ ዛሮች/የዛር መናፍስት ፈረሶች በጃፓናዊው አንትሮፖሎጂስት/ፕሮፌሰር ዓይን!!

Date:


እንደ መንደርደሪያ፤

ኢቲሹ ከዋሴ (ፕሮፌሰር) ይባላል። ኢትዮጵያውያን ወዳጆቹ “ጃፓናዊው ጎንደሬ” ብለው ይጠሩታል። በወጣትነት ዘመኑ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት ጎንደር ላይ ለዓመታት ከትሞ በአዝማሪዎች፤ በላሊበሎች (በአሚናዎች) እና የዛር መናፍስት የሰፈሩባቸው ሰዎች በሚካሄድ የአምልኮ እና የመካደም ሥርዓት ላይ የሦስተኛ/የዶክትሬት ዲግሪውን ያጠና የባህል ተማራማሪ፤ አንትሮፖሎጂስት፤ ገጣሚ እና የፊልም ባለሙያ ነው።

ከከዋሴ ጋር ትውውቃችን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በታሪክ እና በቅርስ አስተዳደር ትምህርት ክፍል /History and Heritage Management/ የቅድመ-ምረቃ /Undergraduate/ ተማሪ በነበርኩበት ወቅት ነበር።

ከዋሴ በአዲስ አበባ በነበሩት ቆይታዎች ለጥናቱ ሲል ከጎንደር አብረውት ከመጡ አዝማሪዎች ጋር በእነርሱ የምስጢር ቋንቋ/የወፍ ቋንቋ ዘዬ የሚያደርጉትን ጭውውት እና የአዝማሪ ምሽቶች በተለያዩ ጊዜያት አብሬያቸው የታደምኩበት አጋጣሚዎች ነበሩ። ከዋሴ ከጎንደር አማርኛና የአራዳ ቋንቋዎች ባሻገር የአዝማሪዎችን ምስጢራዊ የመግባቢያ ቋንቋ አቀላጥፎ ይናገራል።

የአንትሮፖሎጂስቱን ከዋሴን ገለጻ/Lecture በጨረፍታ፤ 

ትናንትና ጃን ሜዳ አካባቢ የሚገኘው “የፈረንሳይ የጥናት ማእከል ስለኢትዮጵያ” ይህን ጃፓናዊ ምሁር/ፕሮፌሰር ተናጋሪ እንግዳ አድርጎ ጋብዞት ነበር።

ከዋሴ በጎንደር ከተማና የገጠር ቀበሌዎች በአዝማሪዎች፤ በላሊበሎች/አሚናዎች እና የዛር መንፈስ የሰፈረባቸው ሰዎች/ባለ ዛሮች ዙሪያ ለረጅም ዓመታት ያደረገውን ጥናቱን በዘጋቢ ፊልም/ዶክመንተሪ ጭምር በታገዘ መልኩ ለ3 ሰዓታት የዘለቀ ገለጻ/Lecture አቅርቦ ነበር።

ከገላጻው ጋር ተገናዝቦ በቀረበው ዘጋቢ ፊልም/ዶክመንተሪ እንደተረዳሁትም ከዋሴ ከጥናቱ ጋር በተያያዘ፤ ከጎንደርና እንዲሁም ከመላኩ ፈንዲቃ የባህል ቡድን- አዝማሪዎችንና መሲንቆ ተጫዋቾችን ጃፓን ድረስ በመውሰድ በሚያስተምርበት ዩኒቨርሲቲ በተዘጋጀ ዓለም አቀፍ የባህል ሲምፖዚየም፤ ትርኢትና ዐውደ-ርእይ ላይ እንዲሳተፉ አድርጓል፤ ዕድሉን አመቻችቷል።

በዚህም ጃፓናውያንና የሌሎች አገራት ዜጎች ስለኢትዮጵያ ባህል እንዲያውቁ ፕ/ር ከዋሴ የበኩሉን አስተዋፅዖ አድርጓል።

ከዋሴ ከዚህ በፊትም ይህን በዘጋቢ ፊልም የታጀበ ጥናቱን- በአገሩ ጃፓን የተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች፤ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ/የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም፤ በጀርመን ሀምቡርግ፤ በካናዳ ኒውዮርክ፤ በአሜሪካ ሀዋርድና ካሊፎርኒያ፤ በጣሊያን ፍሎረንስ፤ በፈረንሳይ ፓሪስ… ዩኒቨርሲቲዎች አቅርቧል።

በተጨማሪም ከዋሴ- በእወቁ ኢትዮጵያዊ የፊልም እና የታሪክ ተመራማሪ በሆኑት ፕሮፌሰር ኃይሌ ገሪማ በዋሽንግተን ዲሲ ባቋቋሙት ሳንኮፋ ማእከልም ይህን ጥናቱን ለማቅረብ ዕድሉን አግኝቶ ነበር።

የፈረንሳይ የጥናት ማእከል ስለኢትዮጵያ በተካሄደው የአርብ ከሰዓት በኋላ የፕ/ር ከዋሴ ገለጻ ላይ፤ ከኢትዮጵያውያን ባሻገርም በዜግነት ጣሊያን፤ ፈረንሳይ፤ አሜሪካ፤ ኖርዌይ፤ አውስትራልያ… የሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክ፤ ባህል፤ ቅርስ፤ ሙዚቃ… ወዘተ. ዙሪያ በስፋት ያጠኑና እያጠኑ ያሉ የታሪክ፤ የአንትሮፖሎጂ ምሁራን፤ የባህል ሙዚቃ ተመራማሪዎችና የፊልም ባለሙያ የሆኑ ወጣትና ጎልማሳ ምሁራን የታደሙበት ድንቅ ቆይታ ነበር።

ከገለጻው በኋላም የነበረው የጥያቄ እና መልስ ጊዜ በጣሙን የተሟሟቀ ነበር። በተለይ ፕ/ር ከዋሴ እንደ አንትሮፖሎጂ ምሁር- በዛር መናፍስት ዙሪያ ባሉ ባህላዊ፤ አምልኮዊ፤ ሥርዓታዊ፤ ትውፊታዊ… ክንውኖች ዙሪያ ያነሳቸው ሐሳቦች በርከት ያሉ ጥያቄዎች ያስተናገደና የተሟሟቀ ውይይትን የጫረ ዐቢይ ጉዳይ ሆኖ ነበር።

በውይይቱ ላይ ከዛር መናፍስት ባህላዊ አምልኮና ሥርዓት እንዲሁም ፈውስ ጋር በተያያዘ በተነሳው ጥያቄና ክርክር ላይ ከተነሱ የማዳበሪያ አስተያየቶች አንዱን ብቻ ላንሳ።

በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል Clinical Psychologist የሆነችው ሣራ፤ በኦሮምያ ክልል በቢሾፍቱና በፈረቀሳ የዛር መንፈስ ያደረባቸው ሰዎች ፈውስ በመስጠት ረገድ ያለውን ባህላዊና አምልኮዊ ተፅዕኖ በተመለከተም፤

“Lived Experiences of Individuals with the Zar and the Practices of Zar Helaers in Bishoftu and Fer, Ethiopia” 
በሚል አርእስት ለሁለተኛ ዲግሪዋ ማሟያ እየሠራችው ካለችው ጥናቷ በመነሳት በተለምዶ ባዕድ/ባህላዊ አምልኮ እየተባሉ የሚጠሩት እንደ ዛር፤ ውቃቢ፤ አውሊያ… የመሳሰሉ መናፍስቶች በሚቀበሏቸውና በሚከድሟቸው ሰዎች/ማኅበረሰብ ዘንድ ከባህል፤ ከእምነት፤ ከጤና፤ ከሀብትና ዕድል… ወዘተ. ጋር የተያያዙ ጥናቶች የሚፈልጉ ጉዳዮች እንዳሉ አንስታለች።

ከንባቤ እንደተረዳሁትም በተለይ የውጪ ሀገራት አጥኚዎች በዚህ ጉዳይ ላይ ሰፊ ጥናት የሠሩ ሲሆን፤ እንደ ዛር ያሉ የመናፍስት አምልኮ በእኛ አገር ብቻ ሳይሆን በሌላው ዓለም ጭምር ያለ ነው። በክርስትና፤ በእስልምና በአይሁድ እምነትም እንዲህ ዓይነቱ ከመናፍስት አምልኮ ጋር የተያያዙ ክንዋኔዎች እንዳሉ የምሁራኑ ጥናቶች ያሳያሉ። ለአብነት ያህል ጥቂቶቹን ልጥቀስ፤

J. Boddy: A Scholarly Overview of Zar Spirit Possession as a Cultural System Extending to Ethiopia, Sudan, Arabia, and beyond —

Grisaru, Budowski & Witztum (1997) — Possession by the “Zar” among Ethiopian Immigrants to Israel: Psychopathology or Culture-bound Syndrome?

Ben-Gurion University Research Portal
PubMed (1995) — Mental Disease Related to Belief in Being Possessed by the “Zar” Spirit.

Messing (1958) — Group Therapy and Social Status in the Zar Cult of Ethiopia (American Anthropologist).

የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና ትምህርት ክፍል ባልደረባ የሆነው ሰጥአርገው ቀናው (ዶ/ር)፤ በዛር መናፍስት ዙሪያ፤ “Knowledge Production and Spiritual Entrepreneurship in Zar: A Study of Spirit Mediumship in Northeastern Ethiopia” በሚል አርእስት የጻፈው ዝነኛ የጥናት ሥራው በመጽሐፍ መልኩ ታትሞ አማዞን ላይ እየተሸጠ መሆኑን ልብ ይሏል።

እንደ መውጫ፤

ፕ/ር ኢቲሹ ከዋሴ በኢትዮጵያ በተለይም በጎንደር ለጥናት በቆየባቸው ዓመታት የያየውንና የታዘበውን በመጽሐፍ አሳትሞ ለንባቡ አብቅቷል።

ይህ መጽሐፉ በመጀመሪያ በአገሩ ቋንቋ በጃፓንኛ የቀረበ ሲሆን፤ ጄፌሪ ጆንሰን፤ “Mischief of the Gods: Tales from the Ethiopian Streets” በሚል ወደ እንግሊዝኛ ቋንቋ ተተርጉሟል። ፍልስፍናዊና ምጡቅ የሆኑ እሳቤዎችን በተከታታይ ድርሰቶቹ በማንሳት የምናውቀው ደራሲ ያዕቆብ ብርሃኑ እና ዓለማየሁ ታዬ፤ “የፒያሳ ቆሌዎች” በሚል የፕ/ር ከዋሴን መጽሐፍ ወደ አማርኛ ቋንቋ መልሰውታል።

ፕሮፌሰር ከዋሴ ይህንኑ ጥናቱ በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ ለማቅረብ ቅዳሜ ረፋድ ወደ ትግራይ የተጓዘ ሲሆን፤  የፊታችን ማክሰኞ ደግሞ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ለማቅረብ ቀጠሮ ተይዞለታል። 

ሰላም 🕊

© Dn. Terefe Worku

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ከ989 ሚሊዮን ብር በላይ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የጉምሩክ ኮሚሽን ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3 ቀን 2018...

“እኔ እስካለሁ ድረስ ኢራን የኑክሌር መሣሪያ ባለቤት አትሆንም!”

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ትናንት ሰኔ 5 ቀን...

አገር እንዲህ ዓይንህን ለአፈር ይባላል?

በተጀመረው የአለም ዋንጫ ደቡብ አፍሪካ በሜክሲኮ መሸነፏን ተከትሎ አፍሪካ...

አሜሪካ እና ኢራን የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነት በ24 ሰዓት ውስጥ እንደሚፈራረሙ ፓኪስታን አስታወቀች

ዩናይትድ ስቴትስ እና ኢራን በሰላም ድርድሩ ማዕቀፎች ላይ መስማማታቸውን...