“አዲስ ነገር የመቀበል ፍላጎት ያላቸው ሚሊዮን ወጣቶች አሉ”

Date:

ልጅ ኤልያስ ጥላሁን
(የአማርኛ ሳይንስ ኮሌጅ መሥራች)

ኢትዮጵያ ውስጥ ‹‹የአማርኛ ሳይንስ ኮሌጅ›› ለመክፈት እንቅስቃሴ ውስጥ የገቡ ሰው ናቸው፡፡ ለመኾኑ እንዲህ ያለው መሻታቸው ከየት ተወለደ? ትልሞቻቸውና ግቦቻቸውን ወደ ተግባር ለመተርጎምስ ምን ዐይነት ምዕራፎችን አለፉ? የእንቅስቃሴያቸው አሁናዊ ቁመናስ ምን ይመሥላል? በሚሉት ጥያቄዎች ዙርያ የሚከተለውን ሰፋ ያለ ቆይታ ከግዮን ጋዜጠኛ ፍቃዱ ማኀተመወርቅ ጋር አድርገዋል፡፡ እንኾ! (ክፍል ሦስት )

ግዮን፡- ዩኒቨርሲቲውን እንደተቋም ስትከፍቱ ከመንግሥትና ከትምህርት ሚኒስቴር ጋር ተነጋግራችኋል?


ልጅ ኤልያስ፡- እኛ አሁን ገና ድርጅቱን እያዋቀርን ነው፡፡ አሜሪካ ውስጥ መሠረታዊ ፈቃዶች አውጥተን ጨርሰናል፡፡ ከፋይናንስ ጋር በተገናኘ ከፍ ሲል እንዳነሳሁት አሜሪካን ሀገር ብዙ አካላት እርዳታ ያደርጋሉ፡፡ ብዙ ሰዎች እርዳታ ሲያደርጉ ከታክሱ ላይ ተቀናሽ ይደረግላቸዋል፡፡ የሚረዱት አካል ደግሞ ሕጋዊ እውቅና ያለው ሊኾን ይገባል፡፡ ከዚያ አኳያ በአሜሪካ ከፈቃድ ጋር ተያይዘው ያሉ ነገሮችን ጨርሰናል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ስንመጣ ግን የያዝነው አዲስ ነገር ነው፡፡ ከእኛ ጋር በሥፋት የሚሠራው የትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡ ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ጋር ብዙ ሥራ ይጠበቅብናል፡፡ ያለፈቃድ የምንሠራው ሥራ አይደለም፡፡


በእርግጥ ሥራችን ለውጥ የሚያመጣና ከፍ ያለ በመኾኑ የሚያሳምን መኾኑ ባያጠራጥርም፣ አዲስ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ግን ብዙ ንግግር ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥትም ይሁን ሲቪል ማኅበራት፣ መንግሥትም ይሁን ግለሰቦች በዚህ ነገር ላይ ሊረዱን እንደሚችሉ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ቦታውንም ከመንግሥት የመረከብ ተስፋ ሰንቀናል፡፡ ምክንያቱም ተቋማችን ትውልድን ለአዲስ ልማትና ለውጥ የሚቀርፅ በመኾኑ አዎንታዊ ምላሽ ይጠበቅብናል ብለን እናምናለን፡፡


ግዮን፡- አሜሪካ የንግድ ፈቃዱን ስታወጡ በምን ዓይነት መንገድ ነው?


ልጅ ኤልያስ፡- አሜሪካ በቢሮ ደረጃ ከፍተን መሥራት ከጀመርን ሰንብተናል፡፡ ፈቃድ አውጣጡን በተመለከተ ማንኛውም ተቋም ፈቃድ እንደሚወስደው ነው ያወጣነው፡፡ የኮሌጃችን ስም ‹‹አምሀሪክ ኮሌጅ ኦፍ ሳይንስ›› ወይም ‹‹አኮሳ›› የሚባል ነው፡፡ ፍቃዱ ሳይወጣ ብዙ ሂደቶች አሉ፡፡ እየሠራን ነው ፈቃድ ያወጣነው፡፡ በኢትዮጵያ ደግሞ ፈቃድ ሰጭው የትምህርት ሚኒስቴር ነው፡፡

በሀገራችን እንዳሉ ሌሎች የግል ኮሌጆች ነው ከፈቃድ ጋር ተያይዞ ያለው አሠራር፡፡ ተሳክቶልን የኢትዮጵያን የትምህርት ሥርዓትም ልንቀይረው እንችላለን፡፡ አሁን ባለን ሁኔታ የራሳችንን ኮሌጅ በተማሪዎቻችን ብቃት ሠርተን በማሳየት እናሳምናለን፡፡ አዲስ ኮሌጅ ስለኾነ የምንከፍተው ሁሉንም ዓይነት ፈቃድ በአንድ ጊዜ ማግኘት ከባድ ነው፡፡ ሥራውን ለመጀመር የሚያስችለንን በአሜሪካ በኩል ያለውን ፈቃድ ግን ጨርሰናል፡፡


ግዮን፡- የፕሮጀክታችሁ ካፒታል ምን ያህል ነው? አሠራሩስ በአክስዮን ደረጃ ነው?


ልጅ ኤልያስ፡- አሁን በኢትዮጵያ በአክሲዮን ደረጃ ለማድረግ በጣም ከባድ ነው፡፡ በአሜሪካ ደረጃ ግን በተሻለ መሥራት ይቻላል፡፡ በእርግጥ አሁን ያለው የትራምፕ መንግሥት እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን አይጋብዝም፡፡ አሜሪካ ውስጥ የተቋቋመ የትኛው ኮሌጅ ማንኛውም በትምህርት ዙሪያ የሚሠራ ቢሮ የኾነ እርዳታ ያገኛል፡፡ ከመንግሥት ዋስትና አለው፡፡

ከተለያዩ ትላልቅ ተቋማት ጋር የመሥራት እድልም ይኖረዋል፡፡ አሁን ላይ በጊዜ መዳድበን ከገንዘብ አንፃር ያስቀመጥነው የሥራ ሂደት ባይኖርም ይህን ማሳካት የሚችል ትልቅ ማኅበረሰብ አሜሪካ ላይ አለን፡፡ ማኅበረሰቡን አነቃንቀን ብዙ ሥራ መሥራት እንችላለን፡፡ የመማሪያ ቁሳቁሶችንና የቴክኖሎጂ መሣሪያዎችን ለማግኘት አንቸገርም ብለንም እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ከማኅበረሰባችን ጋር ተጋግዘን ነውና የምንሠራው፡፡


ግዮን፡- የኢትዮጵያን ኮሚዩኒቲ ሰብስባችሁ ስለዚህ ጉዳይ አወያይታችኋል?


ልጅ ኤልያስ፡- አሁን ያለንበት ዘመን የዲጂታል ዘመን ነው፡፡ በፌስቡክ ከብዙ ሰው ዘንድ እንደርሳለን፡፡ ከብዙ ሰዎች ጋር ተነጋግረናል፡፡ የተለያየ መስክ ላይ ያሉ ሰዎችም ጋር በመገናኘት ተነጋግረናል፡፡ እስካሁን ካየሁት የማኅበረሰብ ስሜት ውስጥ 99% የሚኾነው አዎንታዊ አመለካከት ያለው ነው፡፡ በተለይ አሜሪካን ሀገር ያለ ማኅብረሰብ ውስጥ በቀላሉ ሰዎችን ሰብስቦ የማወያየት ነገር በጣም ከባድ ነው፡፡

የሥራው ሁኔታም አስቸጋሪ ስለኾነ አንድ ቦታ መሰብሰብ አይቻልም፡፡ ነገር ግን ባለን የሥራ ግንኙነት በእያንዳንዱ ከተማ ሰዎችን መድረስ የሚያስችሉ ብዙ መንገዶች አሉ፡፡ እስካሁን ብዙ ሰዎችን አነጋግረንም አዎንታዊ ምላሽ አግኝተናል፡፡ ስለዚህ በዚህ ረገድ ተግዳሮት የሚኾንብን ነገር የለም፡፡


ግዮን፡- ሐሳባችሁን ደግፈው በግንባር ወደእናንተ የመጡ ታዋቂ ሰዎች አሉ?


ልጅ ኤልያስ፡- አዎ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ይኼ ሥራ በአብዛኛው የሚሠራው በአዲሱ ትውልድ ነው፡፡ የትምህርት ሥርዓቱን በደንብ ስናየው፣ በተለይ በኢትዮጵያ ትምህርት ትውልዱን ወደተለየ አቅጣጫ የሚወስድ ቢኾን ኖሮ ቢያንስ የተለያዩ ሀገራት የሚሠሩትን ነገር በራሳችን ዲዛይን መሥራት በቻልን ነበር፡፡ ይኼ ግን ከአዲሱ ትውልድ ጋር የሚሠራ ሥራ ነው፡፡ አዲስ ነገር የመቀበል ፍላጎት ያላቸው ሚሊዮን ወጣቶች አሉ፡፡ ምክንያቱም የምንሠራው ሥራ አዲስ በመኾኑ ለዚያ የሚኾነው አዲስ ትውልድ ነው፡፡

የትምህርት ሥርዓቱ አዲስ ነገር ማምጣት የሚችል ቢኾን ኖሮ ላለፉት ረጅም ዓመታት ለውጥ መምጣት ይችል ነበር፡፡ ለምሳሌ ብዙ ሰዎች ልጆቻቸውን አሜሪካን ስኩል፣ ሳንፎርድና በርካታ ትላለቅ ትምህርት ቤቶች ያስተምራሉ፡፡ ሲጨርሱ ግን ወደሌላ ሀገር ነው የሚሄዱት፡፡ ለእነርሱ የሚመጥን የኮሌጅ ትምህርት ኢትዮጵያ ውስጥ ስለማያገኙ ወደ ውጭ ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ ይህን ችግር የሚቀርፍ ነገር እንደአዲስ ልንጀምር ነው፡፡ ይሄ ነገር ለእኛም እንደ አብዮት ነው፡፡ ብዙ ሰዎች ገብተውበታል፡፡ ብዙ ሰዎችንም ይቀይራል ብለን እናምናለን፡፡ የእኛ ሐሳብ በጣም ብዙ ደጋፊ ያለው ነው፡፡


ግዮን፡- በአሜሪካ እርሶ ይኼ የሙሉ ጊዜ ሥራዎ ነው? ወይስ የሚያግዝዎት ሰዎች አሉ?

ልጅ ኤልያስ፡- ይህን ቢሮ ከከፈትን በኋላ ዋና ሥራዬ ይኼ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን በጣም ተጓዥ ሠራተኛ ነኝ፡፡ ከ30 በላይ የአሜሪካ ስቴቶችን እየነዳሁ የምሠራ ሰው ነበርኩ፡፡ ባለፈው ሦስት ዓመት ውስጥ ጥሩ ክፍያ እየተከፈለኝ ስሠራ ነበር፡፡ በሳምንት ሁለት ሺህ እና ሦስት ሺህ ዶላር እየተከፈለኝ ነበር የምሠራው፡፡ ይህ ድርጅት ከተመሠረተ በኋላ ግን በራሴ ተነሳሽነት በርካታ ወጭዎችን አውጥቻለሁ፡፡ ይኼም ኾኖ ከእኛ ጋር አብረው መሥራት ከሚፈልጉ ትላለቅ ተቋማት ውስጥ አንዱ ጎንደር ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ ከእነርሱ ጋር ተፈራርመን የምሠራበትን ሂደት በማመቻቸት ላይ እንገኛለን፡፡

ምናልባት አስቸጋሪ የኾነብን በኢትዮጵያ ያለው የትምህርት ሥርዓትና ቢሮክራሲ እንጂ በአሜሪካ ደረጃ ከኾነ ሲስተሙ በራሱ በቂ ነው፡፡ አሁን በግለሰብ ደረጃ ስሠራ እንኳን እንደ ትልቅ ኩባንያ ነው የሚያዩን፡፡ ምክንያቱም ብዙ ነገሮች ክፍት ናቸው ፤ ዝግ የኾነ ነገር የለውም፡፡ ድሮ በሳምንት 36 ሰዓት ሠርቼ ነበር እንደዚያ ሲከፈለኝ የነበረው ፤ አሁን ግን ከሰኞ እስከ አርብ ለ8 ሰዓት ያለ ዕረፍት ነው የምሠራው፡፡ ብዙ ነገሮችን እያጠናሁ ነው፡፡ የዲጂታል ዘመን በመኾኑ ብዙ መረጃዎች አሉ፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ ብዙ ነገሮች እየተስተካከሉ ሲመጡ ሁሉም ነገር ጥሩ ይኾናል፡፡

ማስታወሻ፡- ውድ አንባቢያን ከልጅ ኤልያስ ጋር ያደረግነው ቆይታ በዚህ አልተጠናቀቀም፡፡ ቀጣዩን ክፍል በሚቀጥለው ቀናት ይዘን የምንቀርብ ይኾናል፡፡

ያጋሩ!

መጽሔቶች

በብዛት የተነበቡ

ተጨማሪ ጽሑፎች
ተመሳሳይ

ለአድዋ ድል መታሰቢያ በአሜሪካ ቀን ተሰየመ

በአሜሪካ፣ የፔንሲልቪኒያ ግዛት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የአውሮፓዊያኑ 'መጋቢት...

ኢሎን መስክ የዓለማችን የመጀመሪያው ትሪሊዮነር ሆነ

ኢሎን መስክ የሀብት መጠኑ 1 ትሪሊዮን ዶላር ያለፈ የመጀመሪያው...

የእግር ኳስ ዳኝነት በኢትዮጵያ

ገነነ መኩሪያ (ሊብሮ) ግዮን መጽሔት :- እግር ኳስ...

ከ989 ሚሊዮን ብር በላይ የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

የጉምሩክ ኮሚሽን ከግንቦት 27 እስከ ሰኔ 3 ቀን 2018...