ኮምሽነር ሌሊሴ ዱጋ የኢትዮጵያ የሕፃናት ደም እና ካንሰር ሕክምና ማኅበር የክብር አምባሳደር ሆነዋል።
በኢትዮጵያችን በየዓመቱ ከ6 ሺህ እስከ 8 ሺህ የሚሆኑ ሕፃናት በካንሰር በሽታ ይጠቃሉ።ይሁን እንጂ ወደ ሕክምና ማዕከላት መጥተው ሕክምና የሚያገኙት ሕፃናት ቁጥር ከ2 ሺህ አይበልጥም።
በአደጉ ሀገራት የሕፃናት ካንሰር ታማሚዎች የመዳን ምጣኔ ከ85% በላይ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ግን በምርመራ መዘግየት፤ በህብረተሰቡ ዘንድ ባለው የግንዛቤ ውስንነት፣ በዘርፉ በተሰማሩ ባለሙያዎች እጥረት፣ ምክንያት ውጤቱ አሁንም እጅግ ዝቅተኛ ነው።
ይህን ችግር በዘላቂነት ለመፍታትና የተቀናጀ ሙያዊ ምላሽ ለመስጠት 35 መደበኛ አባላትን እና ከ150 በላይ ተባባሪ አባላትን ይዞ ጥር 4 2018 ዓ.ም “የኢትዮጵያ የሕፃናት ደም እና ካንሰር ሕክምና ማኅበር” በይፋ ተመስርቷል።
በዚህ የማኀበሩ ምስረታ ማብሰሪያ ዝግጅት ላይም በከፍተኛ የስራ ኃላፊ ደረጃ የጤና ሁኔታ ለሕዝብ ማጋራት ባልተለመደበት ማኅበረሰብ ውስጥ የካንሰር ሕክምና እየተከታተሉ መሆናቸውን ፎቷቸውን ጭምር አያይዘው በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩትና በበርካቶች ዘንድ መነጋገሪያ የሆነው የሰንበቱት የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሌሊሴ ዱጋ ህክምናቸውን ከሚከታተሉበት ጆርዳን አማን በቪዲዮ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
ኮሚሸነሯ በመልዕክታቸው”አላስፈላጊ ስቃይን የምናስቆምበት አዲስ የታሪክ ምዕራፍ መጻፍ አለብን” ያሉ ሲሆን በተጨማሪም የዚህ ማኅበር የክብር አምባሳደር በመሆናቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል።
