አሜሪካ በኢራን ላይ “ኢኮኖሚክ ዲ-ዴይ” ስትል የጠራቸውን እርምጃ መውሰድ እንደጀመረች ካስታወቀች በኋላ፣ ኢራን ይህን ሰፊ ማዕቀብ ለመመከት የሚያስችል የሁለት ዓመት ዕቅድ ማዘጋጀቷን ገለጸች።
የአሜሪካ ግምጃ ቤት ኃላፊ ስኮት ቤሰንት [የገንዘብ ሚኒስትር] ትናንት በሰጡት መግለጫ፣ “እስካሁን ከተወሰዱት ትልቁ የሆነው የፋይናንስ ጥቃት” ኢራን ላይ እንደሚተገበር ተናግረው ነበር።
ለዚህ እርምጃ ምላሽ የሰጡት የኢራን የኢኮኖሚ ሚኒስትር አሊ ማዳኒዛዴህ፣ ቴህራን “ለአሜሪካ ማዕቀቦች ሙሉ በሙሉ ዝግጁ” መሆኗን ተናግረዋል። እርምጃው አሜሪካ ላይ ሌላ ሽንፈት እንደሚያመጣም አክለዋል።
አዲሱን የአሜሪካ እርምጃ ይፋ ያደረጉት ግምጃ ቤት ኃላፊው ቤሰንት፣ ከኢራን ጋር የፋይናንስ ግንኙነት የሚያደርግ የትኛውም አገር እንደሚገለል ተናግረዋል። ከኢራን ጋር የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉ ባንኮች እና ተቋማትም ግንኙነታቸውን ለማቋረጥ ፈቃደኛ ካልሆኑ መገለል እንደሚደርስባቸው ገልጸዋል።
የግምጃ ቤት ኃላፊው ይህ ከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እርምጃ ኢራን ላይ “ገመዱን የሚያጠብቅ እንዲሁም በሁሉም የገቢ ምንጭ የሚያግድ” እንደሆነ ተናግረዋል።
ኢራኑ የኢኮኖሚ ሚኒስትር አሊ ማዳኒዛዴህ ግን “መንግሥት ዝግጁ ነበር፣ ነውም። እነዚህን ክስተቶች ለማስተናገድም የሁለት ዓመት ዕቅድ አለው” ሲሉ ለአገሪቱ መንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያ ተናግረዋል። ኢራን “እነዚህን ዕቅዶች [ለመተግበር] ለረጅም ጊዜ ስትጠብቅ እንደነበረም” አክለዋል።
“እኛም የራሳችን መሣሪያዎች አሉን፤ ጨዋታውን እንዴት እንደምንጫወት እናውቃለን” ብለዋል።
አሜሪካ ኢኮኖሚያዊ እርምጃ የሚመሠረተው በኢራን የንግድ አጋሮች ላይ በመሆኑ፣ ውጤታማ የመሆኑ ጉዳይ ጥያቄ እንደሚነሳበት የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ተናግረዋል።
የኢራን ከፍተኛ ነዳጅ ገዢ የሆነችው ቻይና ከዚህ ቀደም አሜሪካ የጣለቻቸውን ማዕቀቦች ችላ በማለት ከቴህራን ጋር የንግድ ግንኙነቷን ቀጥላ ነበር።
በሌላ በኩል ሌላኛዋ የኢራን አጋር የሆነችው የተባበሩት አረብ ኤምረቶች ከአገሪቱ ጋር ያላትን ሁሉንም የፋይናንስ ግንኙነት እንደምታቋርጥ ባለፈው ሳምንት አስታውቃለች።
አሜሪካ እርምጃዋን ይፋ ካደረገች ከሰዓታት በኋላ ኢራን ከሌሎች አገራት ጋር የንግድ ግንኙነት ይቀጥላል የሚል መተማመን እንዳላት ገልጻለች።
የኢኮኖሚ ሚኒስትሩ ማዳኒዛዴህም ቻይናም ሆነች ሩሲያ የአሜሪካን እርምጃ እንደማይቀበሉ እንዲሁም ሌሎች አገራትም ይቃመዋሉ ብለው እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
ቻይና “ሕገ ወጥ የተናጠል ማዕቀብ” ስትል የጠራችውን የአሜሪካን እርምጃ በጽኑ ተቃውማለች። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባዩ ሊን ጂያንግ፣ ኢኮኖሚያዊ ታክቲኮች ችግሮችን እንደማይፈቱ እና ቤይጂንግ የራሷን ፍላጎት እንደምታስጠብቅ አስታውቀዋል።
