በኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ተጥሎበት የነበረው ግዜያዊ ዕገዳ፤ አሁን በሚሰራው ሥራ ላይ ተግዳሮት እየሆነበት እንደሚገኝ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) አስታውቋል፡፡
የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን በዚህ ዓመት ኢሰመጉን ጨምሮ ሌሎች 5 በሰብዓዊ መብቶች ላይ የሚሠሩ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ላይ፤ “ከተቋቋሙበት ዓላማ ውጪ ሲንቀሳቀሱ አግኝቻለው” በማለት ዕግድ መጣሉ ይታወሳል፡፡
ጉባኤው ከባለስልጣኑ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ጋር ባደረው ውይይት መሠረት፤ ከየካቲት 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ በሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶቹ ላይ ተጥሎ የነበረው ዕግድ በማስጠንቀቂያ መነሳቱ ተገልጿል።
በዚህም የሰብዓዊ መብቶች ጉባኤው በተደጋጋሚ በአመራሮቹና በሠራተኞቹ ላይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ የደረሰበት መሆኑ የገለጸ ሲሆን፤ የቀድሞ የጉባኤው ዋና ዳይሬክተር አቶ ዳን ይርጋ በዚህ ምክንያት ከሀገር መሰደዳቸውም መገለጹ አይዘነጋም፡፡
የአሁኑ የጉባኤው አዲሱ ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ ገመቹ አሁን ላይ ከባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ጋር በመነጋገር ወደ ሥራ መገባቱን የገለጹ ሲሆን፤ ነገር ግን ቀደም ብሎ ተጥሎበት የነበረው እገዳ በሥራው ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ እንዳሳደረበት ተናግረዋል፡፡
መታገዱም ብቻ ሳይሆን ዕግዱ የተነሳበት አካሄድም በተመሳሳይ ከፍተኛ የሆነ ጫና እንዳሳደረ ያነሱት ዋና ዳይሬክተሩ፤ “ኢሰመጉ የተፈረጀበት እና ዕግዱ የተነሳበት አካሄድ ከከፍተኛ ማስጠንቀቂያ ጋር ተደርጎ መነሳቱ ተፅዕኖው እንዲባበስ አድርጓል” ብለዋል፡፡
“የትኛውን ሥራ ስንሰራ ጥፋት ተብሎ እንደምንጠየቅ ግልፅ አይደለም” ሲሉ የተናገሩት ዋና ዳይሬክተሩ ተስፋዬ ገመቹ፤ ጉባኤው ግን ከዕግዱ በፊትም ሆነ በኃላ ሕግን አክብሮ እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በተደጋጋሚ ጊዜ የተለያ ሪፖርቶችን በሰብዓዊ መብት አያያዞች ላይ በማውጣት ትኩረት እንዲደረግባቸው የማሳሰብ ሥራ የሚሰራ ተቋም መሆኑ የሚታወቅ ነው።
(አሐዱ ሬድዮ)
