ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ በ2028 የሚካሄደውን 96ኛውን የዓለም አቀፉ የፖሊስ ድርጅት ኢንተርፖል ዓመታዊ ጠቅላላ ጉnባኤ እንድታዘጋጅ ‘በሙሉ ድምፅ’ መመረጧን የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ።
ኢትዮጵያ የኢንተርፖልን ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ እንድታዘጋጅ የተመረጠችው በ #ሞሮኮ ማራካሽ ከተማ ሲካሄድ በቆየው 93ኛ የኢንተርፖል ዓመታዊ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ነው።
ከጉባዔው ጎን ለጎን ኢትዮጵያ እና ሞሮኮ የፀጥታ ትብብራቸው ለማጠናከር የሚያስችል የመግባቢያ ስምምነት ህዳር 15 ቀን መፈራረማቸውን አዲስ ስታንዳርድ ዘግቧል።
ስምምነቱን የፈረሙት የኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረሚካኤል እና የሞሮኮ ብሔራዊ ደኅንነትና የግዛት ክትትል ዋና ዳይሬክተር አብደላጢፍ ሀሙሺ ናቸው።
የስምምነቱ ዓላማ በሁለቱ አገራት የፖሊስ አገልግሎቶች መካከል ያለውን ተግባራዊ፣ መረጃዊ እና ቴክኒካዊ ትብብር በማሳደግ የጥቃት ወንጀልን፣ የተደራጀ ድንበር ተሻጋሪ ወንጀልን፣ የኮንትሮባንድ መረቦችን፣ ሕገወጥ ዝውውርን እና የሳይበር ወንጀልን መዋጋት ነው ተብሏል።
ከሦስት ወር በፊት እ. ኤ.አ 2025 በነሐሴ በደቡብ አፍሪካ ኬፕታውን ከተማ ተደርጎ በነበረው 26ኛው የኢንተርፖል አፍሪካ ሪጂናል ኮንፈረንስ ኢትዮጵያ ቀጣዩን በ2027 የሚካሄደውን 27ኛውን የኢንተርፖል አፍሪካ ሪጅናል ኮንፈረንስ እንድታዘጋጅ መመረጧን መረጃው አስታውሷል።
