እግድ ከተጣለባቸው ዘጠኝ የ ዶቼ_ቬለ ዘጋቢዎች መካከል የሰባቱ ሲነሳ ሁለት ጋዜጠኞች በዘላቂነት መታገዳቸውን ጣቢያው አስታወቀ
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ኢትዮጵያ ከሚገኙት የዶይቸቬለ ዘጠኝ ዘጋቢዎች መካከል በሰባቱ ላይ የጣለውን እገዳ ማንሳቱን ጣቢያው አስታወቀ።
ሆኖም ጣቢያው ሁለቱ ሠራተኞቹ በዘለቂነት ከሥራ መታገዳቸውን ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን መስማቱን ገልፆ “እርምጃውን አጥብቆ አውግዟል”።
አያይዞም የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኀን ባለሥልጣን ስህተት አለባቸው ያላቸው ዘገባዎች አልያም የኢትዮጵያ ሕግን የሚጥሱ የሚላቸውን ማስረጃ እንዲያቀርብ ዶይቸ ቬለ በድጋሚ መጠየቁን ከጣቢያው የተገኘው መረጃ ያሳያል።
ከተለያዩ የኢትዮጵያ አከባቢዎች ለ ዶቸቬለ የሚዘግቡ ጋዜጠኞች ዘገባ እንዳይሰሩ ጊዜያዊ እግድ የተጣለባቸው ጥቅምት 13/2018 ዓ.ም ነበር።
ጣቢያው በወቅቱ በይፋዊ የፌስቡክ ገፁ ላይ ባወጣው መግለጫ “የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን በፃፈዉ ደብዳቤዉ ዶቼ ቬለና ወኪሎቹን የኢትዮጵያን ሕግና ደንብ ጥሰዋል፣ ሙያዊ ሥነ-ምግባርን አያከብሩም በማለት ወቅሷል” ሲል ገልፆ ነበር።
የዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን (IFJ) በበኩሉ ጥቅምት 22/2018 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የዶይቼ ቬለ አማርኛ ዘጠኝ ጋዜጠኞች በጊዜያዊነት ማገዱን በጽኑ ማውገዙ ይታወሳል። ውሳኔውም በአስቸኳይ እንዲቀለበስ ጥሪ አቅርቦ ነበር።
ፌዴሬሽኑ ይህንን እርምጃ የዶይቼ ቬለን ዘገባ “ዝም ለማሰኘትና በተለይም በአማራ ክልል ውስጥ ስላለው ግጭት ኢትዮጵያውያን ገለልተኛ መረጃ እንዳያገኙ ለመገደብ የታሰበ የማስፈራሪያ ድርጊት ነው” ሲል በወቅቱ ማስታወቁ አይዘነጋም።
