የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በ2017 በጀት ዓመት ከ3.1 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን በላይ በሚሆኑ ገቢ ምርቶች ላይ የጥራት ቁጥጥር ሥራ ማከናወኑን አስታውቋል ።
ሚኒስቴሩ በጉምሩክ ጣቢያዎችና ደረቅ ወደቦች በሚገኙ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቹ አማካይነት የ15,480 አስመጪዎችን ጥያቄዎች ተቀብሎ፣ በኢትዮጵያ አስገዳጅ ደረጃ የወጣላቸው ምርቶች ላይ የጥራት ቁጥጥር አከናውኗል።
በዚህም መሰረት የኢትዮጵያን ደረጃ የሚያሟሉ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዲገቡ ፈቃድ ሲሰጥ፣ እንደ ውሃ ፓምፕ፣ የሶላር ቴክኖሎጂ፣ የልብስ ማጠቢያ ማሽን፣ ፍሪጅ፣ ብሬከር፣ ጀነሬተር፣ ትራንስፎርመር፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ እና የመሳሰሉት ምርቶች ከሚመጡባቸው አገራት ዓለም አቀፍ የጥራት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት እያቀረቡ እንዲስተናገዱ ተደርጓል።
ይሁን እንጂ፣ በተደረገው የላብራቶሪ ፍተሻ እና ኢንስፔክሽን ከደረጃው በታች የሆኑ 1,504.85 ሜትሪክ ቶን የሚጠጉ የምግብ ውጤቶች (ሩዝ፣ የስንዴ ዱቄት፣ የምግብ ዘይት፣ የቴምር ምርትና ፓውደር ጁስ)፣ የኮንስትራክሽን ዕቃዎች (አርማታ ብረት፣ ቆርቆሮ) እና የኤሌክትሪክ ዕቃዎች (የኤሌክትሪክ ኬብል፣ ኤል ኢዲ አምፑል፣ ዲቫይደርና የሶላር ምርት) ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ መታገዳቸውን ሚኒስትሩ አስታውቋ።
