ከሰሞኑ በማህበራዊ ሚዲያ ተጽዕኖ ህይወቷ ያለፈው የ13 አመት ታዳጊ ፊዮሬላ ነብዩ መታሰቢያን በማስመልከት ቤተሰቦቿ ከአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን ጋር በመተባበር ወላጆች ልጆቻቸውን ከማህበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተጽእኖ እንዲጠብቁ ለማስተማር በቸርቸር ጎዳና የብስክሌት ውድድር አካሂደዋል።
በውድድሩ ማስጀመሪያ መርሀ ግብር ላይ ከተገኙት ቤተሰቦቿ መካከል ወላጅ አባቷ አቶ ነብዩ ሳሙኤል ፈረንጅ ባስተላለፉት መልእክት ” ማህበራዊ ሚዲያ እና አርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ታዳጊ ልጆች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ በማሳደር በራሳቸው ላይ ጉዳት እንዲያስከትሉ እየዳረገ ነው”
በማለት ልጃቸው በዚህ ተጽእኖ ምክንያት እራሷ ላይ ባደረሰችው የህይወት ማጥፋት ሰለባ መሆኗን ገልጸዋል። ወላጆች በተለይ ታዳጊ ልጆቻቸውን ከአሉታዊ የማህበራዊ ሚዲያ የመጠበቅ ግዴታ እንዳለባቸው አሳስበዋል።
የብስክሌት ውድድሩን ከፌዴሬሽኑ ጋር በመተባበር ያዘጋጁት መላው ኢትዮጵያዊ ወላጆች ከታዳጊ ፊዮሬላ ህልፈተ ህይወት ተምረው ልጆቻቸውን ከተጽኖው እንዲከላከሉ እና የቅርብ ክትትል እንዲያደርጉ ለማስገንዘብ መሆኑን ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን በትብብር ከቤተሰቦቿ ጋር ባዘጋጁት የመታሰቢያ ውድድር ላይ ታዳጊ ህጻናትን ያሳተፈ ውድድርን ጨምሮ የኮርስ ብስክሌት ውድድር ተካሂዷል።
የኢትዮጵያ ኦሎምፒክ ኮሚቴ ቴክኒካል ዳይሬክተር አቶ ቢልልኝ መቆያ በመታሰቢያ ስነስርአቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፡ የታዳጊ ፊዮሬላ ህልፈተ ህይወት ኢትዮጵያውያን ወላጆችን ሊያነቃ ይገባል ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
የታዳጊዋ አባት አቶ ነብዩ ሳሙኤል ፈረንጅ በኢትዮጵያ ስፖርት ላይ ከፍተኛ አስተዋጾ ያላቸው መሆናቸውን አንስተው በተለይ የመጀመሪያውን አገር አቋራጭ ብስክሌት ቱር (ከአዲስ አበባ እስከ ባህርዳር ) በማዘጋጀት የአገር ባለውለታ መሆናቸውን አንስተዋል።
ለ17 አመታትም የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን የበላይ ጠባቂ በመሆን ማገልገላቸውን ገልጸው በቅርቡ በልጃቸው ህልፈት የደረሰባቸው ሀዘን ሳይገድባቸው ወላጆች በማህበራዊ ሚዲያ ተጽእኖ ልጆቻቸው እንዳይቀጠፉ ለማስተማር ወደ አደባባይ መውጣታቸው እንደሚያስመሰግናቸው ተናግረዋል።
የአዲስ አበባ ብስክሌት ፌዴሬሽን እና የታዳጊ ፊዮሬላ ቤተሰቦች ባሰናዱት የመታሰቢያ ውድድር ላይ የተሳተፉ ተወዳዳሪዎች እንደየ ደረጃቸው የሜዳሊያ፣ የዋንጫ እና የገንዘብ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የታዳጊ ፊዮሬላ ቤተሰቦች በቅርቡ ኢትዮጵያዊ ወላጆች ልጆቻቸውን ከማህበራዊ ሚዲያ አሉታዊ ተጽእኖ መጠበቅ እንዲችሉ ለማስተማር በማሰብ “ፊዮሬላ ፋውንዴሽን” ለማቋቋም በዝግጅት ላይ መሆናቸውንም ገልጸዋል።
