ወልቂጤ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የካንሰር ህክምና ከጀመረ ሁለት ሳምንት የሆነው ሲሆን በተወሰኑ ታካሚዎች የካንሰር ህክምና መስጠቱን ገልጿል:: ህክምናው ከመጀመሩ በፊት ወረፋ የያዙ ስለነበሩ ከተጀመረ ጀምሮ ለስምንት ሰዎች ህክምና መሰጠቱን ገልፀዋል::
የኬሞ አገልግሎት ለሁለት ሰው የተሰጠ ሲሆን ሁለት ዓይነት የኬሞ ቴራፒ ሂደት ሲኖር የአንዱ እጥረት እንዳለ በወልቂጤ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ሀምዛ እህመድ ጨምረው ለጣቢያችን ገልፀዋል::
አሁን ላይ ለሳምባ እና ለጡት ካንሰር ታካሚዎች ህክምና የሰጠው ሆስፒታሉ የቀረውን መድኃኒት ካገኘ 80 በመቶ በሚባል ደረጃ ለሁሉም ካንሰሮች ህክምና እንደሚሰጥ ዶክተር ሀምዛ ገልጸው ይሁን እንጂ የጎደለው መድሀኒት እያለም አሁን ላይ ለጡት ካንሰር ህክምና ሙሉ በሙሉ እየሰጠ እንደሚገኝ ነግረውናል፡፡
የካንሰር ህክምና ሶስት ዓይነት እንደሆነ የገለፁት ዶክተር ሀምዛ የቀዶ ፣ የኬሞ ቴራፒ ህክምና እና የጨረር ህክምና ሲሆኑ ሆስፒታሉ አሁን ላይ የጨረር ህክምና እንደማይሰጥ እና ከዛ ወጪ ያሉትን ህክምናዎች እንደሚሰጥ ገልፀዋል ::
የካንሰር ህክምና የረዥም ጊዜ ክትትል የሚወስድ ሲሆን እንደየደረጃው ከአምስት እስከ አስር ዓመት እንደሚወስድ ተናግረዋል:: በተለይ በአዳጊ ሀገራት የማህበረሰብ የካንሰር ግንዛቤን ለማሳደግ የሚሰሩ ስራዎች መጓደል እና እሱን ተከትሎ የሚኖር ደረጃው የገፋ የካንሰር ህመም ከፍ ያለ ነው ሲሉ በወልቂጤ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል በካንሰር ህክምና ስፔሻሊስት የሆኑት ዶክተር ሀምዛ እህመድ ጨምረው ለጣቢያችን ገልፀዋል::
