የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ጋዜጠኞችን ያሉበት በማይታወቅበት ሁኔታ ከ10 ቀናት በላይ ሰውረው ያቆዩ አካላት በግልፅ እንዲታወቁ እና በሕግ ፊት እንዲቀርቡ ጠየቀ።
ማህበሩ በአሀዱ ኤፍ ኤም 94.3 FM ሬዲዮ የቅዳሜ ገበያ ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ አብዱሰመድ ከ12 ቀናት በኋላ፤ የሪፖርተር ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዮናስ ደግሞ ከ10 ቀናት ስወራ ነጻ ወጥተው ወደ ቤታቸው መመለሳቸውን ማረጋገጡን በይፋዊ የፌስቡክ ገጹ ላይ ባሰፈረው ጽሑፉ አስታውቋል።
ጋዜጠኞቹ ያሉበት በማይታወቅበት ሁኔታ ከ10 ቀን በላይ ተሰውረው መቆየታቸው “ሕገ ወጥ ተግባር ነው” ያለው ማኅበሩ፤ የድርጊቱ ፈጻሚዎች በግልፅ ታውቀው በሕግ ፊት ተጠያቂ እንዲሆኑ ጥሪ አቅርቧል።
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር ይህን ያስታወቀው የሪፖርተር ጋዜጣ ከፍተኛ አዘጋጅ ጋዜጠኛ ዮናስ አማረ እና በአሀዱ ኤፍ ኤም 94.3 FM ሬዲዮ የቅዳሜ ገበያ ፕሮግራም አዘጋጅ ጋዜጠኛ አብዱል ሰመድ መሀመድ እንደተለቀቁ መገለጹን ተከትሎ ነው።
