የሮተሪ ኢንተርናሽናል ፕሬዚዳንት ዶ/ር ፍራንስኮ አሪዞ በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከልን በዛሬው ዕለት ጎብኝተዋል። በጉብኝታቸውም ወቅት በሮተሪ ኢንተርናሽናል አማካይነት ሕክምና ካገኙ ታካሚዎች ጋር ውይይት አድርገዋል።
በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል የሚሰጠውን አገልግሎት እንዲያከናውን ድጋፍ ከሚያደርጉ ተቋማት መካከል አንዱ የሆነው ሮተሪ ኢንተርናሽናል፣ ከ1955 ጀምሮ በኢትዮጵያ ውስጥ ረዥምና ንቁ ተሳትፎ ሲያደርግ መቆየቱ ተገልጿል፡፡
ሮተሪ ኢንተርናሽናል በጤናው ዘርፍ ላይ ትኩረት በማድረግ በተለይም በበሽታ መከላከል፣ በእናቶችና ሕጻናት ጤና እና በንጽሕና አጠባበቅ (Sanitation) ዘርፎች ላይ እየሰራ እንደሚገኝ ተነግሯል።
በአሁኑ ወቅትም በኢትዮጵያ 21 የሮተሪ ክለቦች እንዲሁም የሮተሪ እና ኢንተርአክት (Interact) ክለቦች ያሉት ሲሆን፣ እነርሱም ከኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴርና ከሌሎች አጋሮች ጋር በመተባበር በትልቅ ደረጃ የጤና ፕሮጀክቶችን ለመፈጸም እየሰሩ እንደሚገኙም ነው የተገለጸው።
በኢትዮጵያ የልብ ሕሙማን ሕጻናት መርጃ ማዕከል ላለፉት 36 ዓመታት ከ9 ሺሕ በላይ ለሆኑ ታካሚዎች የነጻ የልብ ቀዶ ሕክምና አገልግሎቶችን ሲሰጥ የቆየ አገር በቀል ለትርፍ ያልተቋቋመ ተቋም ነው። ተቋሙ ከሁሉም የአገሪቱ አካባቢዎች ለሚመጡ ሁሉንም ያካተተ የልብ ሕክምና አገልግሎት ከክፍያ ነጻ በሆነ መልኩ በመስጠት ላይ ይገኛል::
