በሱዳኗ ስትራቴጂካዊቷ አል-ኦበይድ ከተማ ላይ የተሰነዘረ የድሮን ጥቃት የ23 ሰዎችን ሕይወት መቅጠፉን የሰብአዊ መብት ተሟጋች ቡድን እና የዓይን እማኞች አስታውቀዋል።
ክስተቱ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰበት ጊዜ ጀምሮ ከተማዋ ካስተናገደቻቸው የአየር ላይ ጥቃቶች መካከል እጅግ አስከፊው መሆኑ ተገልጿል።
በሱዳን ጦር እና በፈጣን ድጋፍ ኃይል (RSF) መካከል በሚያዝያ ወር 2015 ዓ.ም የተቀሰቀሰውን ግጭት ተከትሎ፣ የድሮን ውጊያ ከጊዜ ወደ ጊዜ በስፋት ጥቅም ላይ እየዋለ ይገኛል።
በከተማዋ ምስራቃዊ ክፍል በሚገኘው አል-ማታር ሰፈር የሚኖር አንድ ነዋሪ የደረሰውን አደጋ ሲያብራራ፤ «ክስተቱ እጅግ አሳዛኝ ነው፤ የቤቶች ጣሪያ በነዋሪዎቹ ላይ ተደርምሷል» ብሏል።
የአካባቢው የሕክምና ምንጭ ለኤኤፍፒ እንደገለጸው ከሆነ፣ ከተገደሉት መካከል ሁለት ሕፃናትና እናታቸው እንደሆነች የሚገመቱ አንዲት ሴት ይገኙበታል።
በጦርነቱ የሚፈጸሙ ጥሰቶችን እየሰነደ የሚገኘው «ኢመርጀንሲ ሎውየርስ» ቡድን፤ በደቡብ ኮርዶፋን ቀጠና ቁልፍ ማዕከል በሆነችው ከተማ ላይ የተሰነዘረው ጥቃት የተጀመረው ረቡዕ ምሽት መሆኑንና እስከ ሐሙስ ድረስ መቀጠሉን አስታውቋል።
ጥቃቱ የመኖሪያ አካባቢዎችን፣ የለቅሶ ሥነ-ሥርዓትና የምግብ ቁሳቁስ የጫነች የጭነት መኪናን ኢላማ ያደረገ ነበር።
እንደ ቡድኑ መግለጫ፤ ቢያንስ 19 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን፣ ለጥቃቱ ተጠያቂው የፈጣን ድጋፍ ኃይል (RSF) መሆኑን ጠቅሷል።
ይሁን እንጂ የቀረበው ክስ በተናጥል ሊረጋገጥ አልተቻለም፤ ከኃይሉም ወዲያውኑ የተሰጠ አስተያየት የለም።
